SermonsTeachingsUncategorized

Go home justified

Go home justified

ጻድቅ ሆነህ ወደ ቤትህ ተመለስ (ሉቃ 18፡9-14)

9 ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ 10 እንዲህ ሲል፦ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። 11 ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፦ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ 12 በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። 13 ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። 14 እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።


በዚህ ክፍል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለአንድ ትልቅ ጉዳይ ተናገረ። እርሱም በእግዚአብሄር ፊት ስለመቅረብ ዘዴ፡፡

እኛ ሰዎች ሲንሆን ለተለያዩ ጉዳዮች የተለያዩ የአቀራረብ ዘዴዎችን ለምደናል፡፡ በርግጥ ልምዱ በራሱ ጎጂ አይደለም፡፡ ግን ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብ ብዙም አያዋጣም፡፡ ለሥራ ውድድር፣ ለንግድ፣ ለጉርብትና ለትዳር ፍለጋ፣ ወዘተ በምንሄድበት መንገድ ብንቀርብ ከጌታ ፈቃድ ጋር እንተላለፋለን። ያዕቆብ የበግ ጠጉር ለብሶ እና ድምጹን ቀይሮ መቅረብ የቻለው በሕስያቅ ፊት እንጂ በጌታ ፊት አይደለም።

በንጉስ ፊት በሚቀረብበት ጊዜ ተቀባይነት ያለው የአቀራብ ዘዴ አለ፡፡ በገዥዎች፣ በባላንጣዎች፣ በፍቅረኞች፣ በጓደኞች፣ በጎረበቶች፣ በፖሌትከኞች፣ ወዘተ. ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ወይም የተለመዱ ወይም የሚጠበቁ የተለያዩ የአቀራረብ ዘዴዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውስጥ የተለመዱት፣ ራስን ከፍ፣ ጥሩ ወይም መልካም አድርጎ የማቅረብ ዜደ ነው፡፡ ገዢውን አክባሪ፣ ትሁት፣ ለጋሽ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ ለዚህም ዓላማ የተከሸኑ ቃላት እና አጋላለጾች አሉን፡፡ የተለመዱ የአክብሮት ቃላትና ሓረጎች በአብዛኛው ሰው በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

“ጌታዬ፣ አባቴ፣ ጋሼ፣ ጋሽዬ፣ እምዬ፣ እትዬ/እህትዬ፣ ልጄ፣ ወንድሜ”፣ ወዘተ. እየተባሌ ይወራል፡፡ አነጋገር ብቻም ሳይሆን፣ አቀራረብ፣ አለባበስ፣ አቋቋም፣ አቀማመጥ፣ ወዘተ. ግንዛቤ ውስጥ ይገባል፡፡

አንዳንዴም ልብን የሚያማልሉ ሥጦታዎችን፣ ህዝብን/ፍርድን የሚያስቀይር፣ ክብርን የሚያሳይ፣ ፍቅርን የሚገልጥ የሚመስሉ ስጦታዎችም ይታከሉበታል፡፡

እንግዲህ በሰዎች መካል የተለመዱት እነኚህን ተግባራት ሰዎች በእግዚአብሄርም ዘንድ ይዘው ይሄዳሉ፣ ይዘን እንሄዳለን፡፡ ስናደርገውም እግዚአብሄር የማይቀበለው መሆኑንና ከእግዚአብሄር ልንቀበል የሄድነውን ነገር ሳናገኝ እንደሚመልሰን ጌታችን በምሳሌው ውስጥ አበክሮ ተናግሮአል፡፡

በምሳሌው ውስጥ ሁለቱም ሰዎች ፈልገው የሄዱት ለእግዚብሄር ጸሎትና ምስጋናቸውን ይዘው ነበር፤ ጽድቅ ለማግኘትም ነው፡፡ ሆኖም ግን አንደኛው ወደ ጸሎቱ ቦታ የሄደው ያለውን ጽድቅ፣ ሠርቶና ደክሞበት ያገኘውን ጽድቅ ለማሳዬት ሲሆን ሌለኛው ግን የሌለውንና በራሱ ማግኘት የማይችለውን ጽድቅ ከእግዚአብሄር ለመለመን ነበር፡፡

ሁለቱም በጸሎት ቦታ ናቸው፡፡ ሁለቱም በእግዚአብሄር ፊት ሆነው እግዚአብሄርን እያነጋገሩት ነው፡፡

አንደኛው ለራሱ በደምብ መመስከር የሚችል፣ በሥራውና በአሠራሩ የሚኮራ፣ የጽድቅ ሥራ ነው ብሎ የሚያምንበትን ጠንቅቆ የተገበረ ሰው ነበረ፡፡ “በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ” (ቁ 12)፡፡

ስለዚህ ራሱን በእግዚአብሄር ፊት ሲያቀርብ ይዞት የነበረው በራስ መተማመን ከፊተኛ ነበረ፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው የመነጋገር ጊዜ በሰዎች እና በጌታ ፊት የራስን ጽድቅ በመናገር ጨረሰው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሰውዬው “የወንድሞች ከሳሽ” ሆኖ ራሱን አቅርቦአል፡፡ ሌሎችን ከሥራቸው እና ከሓጢአታቸው የተነሳ፣ የሚወቅስና ራሱን ከሌሎች ሁሉ የተሻሌ አድርጎ የሚያቀርብ ሰው ነበረ፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ” ይላልና፡፡ ስለዚህ ከቀራጩ ሰውዬም ሆነ በአከባቢው ከነበሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥበት ነገር እንደነበረው ያምን ነበረ፡፡

የሰማይን ሥርዓትም ሆነ አሠራር እንዲሁም በሰውን ልብ ያለውን የሚያውቀው ኢየሱስ ግን ይህ ፈሪሳዊ ሰው ምንም ሳይቀበል የተመለሰ መሆኑን ገለጸ፡፡

ሰውዬው የያዘውን ሓጢአት ተናዝዞ ከእግዚአብሄር ዘንድ ምህረትን ከማግኘት ይልቅ ጽድቁን ብቻ ተናግሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ያ ማለት መጽደቅ የሚችልበትን አጋጣሚ ባለመጠቀሙ፣ እርሱ ጽድቅ የሚለውን ጌታ ደግሞ ሳያደንቅለት አለፈና ከነበደሉ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡

እግዚአብሄር ያልሰጠንን ጽድቅ ለራሳችን ብንቆጥር ራስን መሸንገል እንጂ ድነት አናገኝበትም፡፡ በሕይወት የሚያኖረው ግን እግዚአብሄር ራሱ በምህረቱ የሚሠጠው ጽድቅ ነው፡፡

“ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። (ገላ 2፡16)

“እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤ በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን። (ሮሜ 5፡1-2)

አንቴ፣ የምትኮራበት ጽድቅ የትኛው ነው? አንቺስ በየትኛው ጽድቅሽ ይሆን የምትኮሪው? በጌታ ምህረትና በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተ ጽድቅ ወይስ በራሳን ለራሳችን በምንሠጠው ጽድቅ? በጸጋው ወይስ በሥራችን?

ሰው በሰው ፊት ሊለዋወጥ፣ መልኩንና ቃሉን ሊቀያይርና ሊያሳምር ይችላል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ግን ይህ አይነቱ ዘዴ አይሠራም፡፡ ተሰምነት ያለውን ጸሎት መጸለይ የምንችለው እንደሓሳቡ ስናደርገው ብቻ ነው፡፡ “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።” (1ዮሃ 5፡14)፡፡

ስለዚህ ነው ጌታችን ከብበውት ለነበሩት እና “ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ” ይህን ምሳሌ የነገራቸው፡፡

ወገኖቼ፣ ዛሬም እግዚአብሄር ሕይወታችንን እንድንመለከት ይፈልጋል፡፡ በራሳችን ግምት፣ ወይም ሰዎች በሚሰጡን ቦታና ሓሳብ ላይ ተመሥርተን ከእግዚአብሄር ጽድቅ ራሳችንን እንዳናጎድል ጌታ ይርዳን፡፡

ጌታ ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የጠቀሰው ቀራጭ ራሱን በአግባቡ የሚያውቅና የእግዚብሄርንም ፅድቅ የተረዳ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ጸሎቱን ለማቅረብ ሲሄድ እግዚአብሄርንና ራሱን እንጂ ስለሌሎች ግድ አልነበረውም፡፡ ማለቴ አላስታወሳቸውም፡፡ “ሪቆ” ነበር የቆመው፡፡ “አይኑን አላነሳም”፡፡ ደረቱን ይደቃ ነበር፡፡ በበደል መኖሩን ያውቀዋል ግን አልወደደውም፡፡ ያዝንበታል፣ ያለቅስበታል፡፡ ከዚህ የተነሳ ራሱን ከሌሎች ጋር የሚያስተያይበትና በእግዚአብሄር ፊት የሚመጻደቅበት ጊዜም ልብም አልነበረውም፡፡

በመጨረሻውም ቀን በልዑል እግዚአብሄር ፊት ስንቀርብ፣ ስለራሳችን እንጂ ስለሌላው ሰው መልስም ሆነ ሃሳብ መስጠት አንችልም፡፡

ቀራጩም ሰውዬ (እንደ ሌለኛው) ብዙ መልካም የሆኑ ነገሮች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ለእርሱ እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው ምህረት ነበርን። ዳዊት “ምህረት ከህይወት ይሻላል” ይላልና። የሚያውቀው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እርሱ ሃጢአተኛ መሆኑንና እግዚአብሄር ብቻ ሊያጸድቀው እንደሚችል ፡፡

ከጌታ ጋር ሲነጋገርም፣ “አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።” ጸሎቱን ጨርሶ ወደቤቱ ሲሄድም የእግዚአብሄርን ይቅርታ እና ምህረት ተቀብሎ ተመለሰ፡፡ ሸክሙን ጥሎ ተመለሰ ማለት ነው።

በሰው አይን ሁለቱ ሲታዩ ፈሪሳዊው ጻድቅ ቀራጩ ሃጢአተኛ ነበሩ፡፡ በጌታ አይን ግን ሲታዩ ቀራጩ የጸደቀ ኃጢአተኛ ፈሪሳዊው ደግሞ ራሱን በራሱ ያጸደቀ እና ከነሃጢአቱ የሚኖር ሃጢአተኛ ነበረ፡፡

ይህንን ምሳሌ ኢየሱስ ሲናገር አድማጮች ሰምተው የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንዲቀበሉ ነው፡፡ ሰሚዎቹ ኢየሱስ ከጎናቸው ሆኖ እየለመናቸው ያለጽድቅና ምህረት እንዳይመለሱ ነው፡፡ ሰሚዎቹ የራሳቸውን ጽድቅ ትተው የእግዚአብሄርን ጽድቅ እንዲቀበሉ ነው፡፡ የምህረትንና የጉብኝታቸውንም ጊዜ እንዳይንቁ ነው፡፡

ኢየሱስን ለማየትና ለመስማት መምጣታቸው ካልቀረ፣ ለምንድር ነው ከነ ኃጢአታቸው የሚኖሩት? ኢየሱስ በእግዚአብሄር ፊት ራሱን ስላዋረደው ሰውዬ ሲናገር “ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ” አለ፡፡

ለእኛም፣ ዛሬ የእግዚብሄር እጅ ለምህረት ተዘርግቶ አለ፡፡ ሌላ ዝባዝንኬ ትተን፣ ከመሃሪው ምህረትን ለመቀበል እንቅረብ፡፡ ሃይማኖተኝነትና የሃይማኖትን ሥርዓት ብቻ ስለያዝን ራሳችንን መደለል የለብንም፡፡

ወገኖቼ፣ ዛሬ ጻድቅ ሆነን ወደ ቤታችን እንመለስ ወይስ ራሳችንን በከንቱ እየካብን ያለእግዚአብሄር ጽድቅ እንሂድ?

እግዚአብሄር ሰው አይደለም፡፡ እርሱ ከፍ ያደርጋል፡፡ እርሱም ዝቅ ያደርጋል፡፡ እርሱ እውነተኛ ፈራጅ ነው፡፡ እርሱ ኃጢአትን ይቅር ይላል፡፡ በደልንም ይከድናል፡፡

መዝሙረኛው ዳዊት ሲዘምር (32፡1-2) “መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው።” ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ሊፈጸም የሚችለው ንስሃና በክርስቶስ ደም መታጠብ ሲኖር ነው፡፡ ራስን ዝቅ አድርጎ በእግዚአብሄር ፊት መቅረብ ለእውነተኛ ከፍታ ያዘጋጃል፡፡

ሲለዚህ ኢየሱስ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።” አለ፡፡ በጌታ ፊት ተዋርዶ እርሱ ከፍ ሲያደርግ ምንኛ መታደል ነው? “ኑ!” ብሎ ሲጠራን አሁን እንስማው፡፡ በእግዚአብሄር ምህረት ጻድቅ ሆነን ወደየቤታችን እንመለሳለን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *