SermonsTeachingsUncategorized

min litayu

“ምን ልታዩ መጣችሁ?”

(ማቴ 11፡2-15 )

ባለፈው ሳምንት ስለየመጥመቁ ዮሃንስ ስብከትና አገልግሎት አይተን ነበር፡፡ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እያገለግ እንደነበረ አይተናል፡፡ የዮሃንስ አገልግሎት የእግዚአብሄር መንግሥት መቅረቧን ሃጢአተኞች ለሆኑት ለሰዎች ልጆች በሙሉ መናገር ነበረ፡፡ ይህንን ሲያደርግ ወታደሮቹን፣ ቀራጮቹን፣ ፈሪሳዊያኑን፣ ሳዱቃውያኑን፣ ሀገረ ገዢውንም ሊሰሙት የሚያስፈልጋቸውን የእግዚአብሄር ቃል ሳይሸቃቅጥ ይናገር ነበረ፡፡

በዚህ መንገድ የእግዚአብሄርን ቃል ለሰዎች ሁሉ መናገር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ያንን የሚያደርግ ሰው እግዚአብሄርን ከሁሉም አብልጦ የሚፈራና የቃሉንም ሥልጣን ከሰዎች ስልጣን አስበልጦ የሚያከብር ሰው ብቻ ነው፡፡

ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘመናችን ያሉ የብዙ ታማኝ መልእክተኞች መልእክት በሰሚዎቹ ልክ የሚቀያየር ሳይሆን እግዚአብሄር እንድናገሩ በሚፈልገው ልክ ነበረ፡፡ እንደነ ኤሊያስ እና ኤርሚያስ ያሉ ነቢያት በሚያስጨንቅ ጊዜ ውስጥ ያለ ምንም ማመቻመች የእግዚአብሄርን መልእክት ለታላላቆችና ለታናናሾች አስተላለፉ፡፡ ከዚያም የተነሳ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ ተቀበሉ፡፡

መጥመቁ ዮሃንስም ለ400 ዓመታት የቆየውን የዝሚታ ዘመናት ሰብሮ ህያውና ግልጽ ዓላማ ያለውን መልእክቱን ለሕዝብ ለመናገር ሲነሳ መጀመሪያ ራሱ በማዘጋጀት ጀመሬ፡፡ ሌሎችን ለእግዚአብሄር ለማንበርከክና ወደ መንግስቱ ለማምጣት ራሱን፣ ምቾቱንና ክብሩን ለእግዚአብሄር ክብር ያንበረከከ ይመስላል፡፡

ዮሓንስ ረዥም የአገልግሎት ዘመን አልነበረውም (ዕድሉን አላገኘም) ። ነገር ግን በወሳኝ ጊዜ ተጽዕኖ አምጪ አገልግሎት ነበረው። ይህም በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው ሆኖ እንድመሰከርለት አድርጎታል።

በምድረ በዳ ሆኖ የጌታን ድምጽ በደንብ ከተቀበለ በሃላ መልእክቱን በፍጹም ግልጽነትና ታማኝነት ለሰዎች ሁሉ ማድረስ ጀመረ፡፡

ይህንን የሚመስል አገልግሎት እያገለገለ ነው ሀገረ ገዢውን “ወንድምህን ገድለህ ምስቱን መውሰድ አይገባህም” ብሎ ስለገስጸው ወደ ወይኒ የወረደው፤ ምስቲቱም የጥፋት ወጥመድ መዘርጋት የጀመረችው፡፡

ሀገረ ገዢውም በወይኒ አኖረው፡፡ መልእክቱ ትክክለኛ እንደሆነ አውቆአል፡፡ ድፍረቱንና ታማኝነቱንም ተረድቶአል፡፡ በዮሃንስ ላይ እርምጃ መውሰድ ደግሞ ህዝቡን እንደሚያስነሳበት አሰበ፣ ፖሌቲካውንም እንደሚያበላሽበት ስለተረዳ፣ አስሮት በነበረበት ወይኒ ቤት እየሄዴ ይሰማው ነበረ፡፡

ዮሃንስ ተስፋ ነበረው፡፡ ተስፋው ግን በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሠረተ፣ በልጁም በእየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ላይ ነበረ፡፡ ይሁንና በዚያን ጊዜ ዮሃንስ ባለው መረዳት፣ መስሂው ሲመጣ ሙሉ ሥልጣኑን ይዞ እንደሚነሳ ነበረ፡፡ በእርግጥ ይህ አስተሳሰቡ ሲህተት ነው ማለት አንችልም፡፡ ኢየሱስ ስልጣን ነበረው፡፡ ሆኖም ግን የስልጣኑን አጠቃቀም ደግሞ ፈቅዶ ገድቦት ነበር እንጂ፡፡ ስለዚህ በሃይል ሂዶ ዮሃንስን ከእስርቤት ማውጣት አልፈለገም፡፡ እርሱ ራሱ ጀምሮት ያለውን የመስዋዕትነት ጉዞ ጠንቂቆ ያውቅ ነበርና፡፡

ዮሃንስም የጠበቀው ሳይሆን ሲቀር፣ ከሄሮድስም እጅ ሊያወጣው የሚችል ሌላ እንዳልተገኘ ባወቀ ጊዜ፣ መልእክተኞችን ወደ ኢየሱስ ላከ፡፡መልእክተኞቹም ሂደው የዮሃንስን ጥያቄ ለኢየሱስ አቀረቡ፡፡ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” (ቁ 2-3)፡፡

ከዚህ አንድ ነገር መማር እንችላልን፡፡ ታላላቅ አገልጋዮችም ጥያቄ አላቸው፡፡ እነርሱም እምነታቸው በየደረሱበት ቦታ ይፈተናል፡፡ ብሆንም ግን ማንን እንደሚጠይቁ ያውቁበታል፡፡ ስለዚህ በአይምሮአችሁ ውስጥ ጥያቄ ሲፈጠር፣ ብቸኛ ተጠራጣሪ፣ ብቸኛ ሃጢአተኛ አድርጋችሁ ራሳችሁን መኮነን አትጀምሩ፡፡ ግን በጌታ ፊት ጥያቄአችሁን አቅርቡ፡፡ እርሱ ትክክለኛ መልስ አለውና፡፡

ለዚህ ጥያቄ ኢየሱስ አጠር ያለ መልስ “እኔ ነኝ” ብሎ መመለስ ይችል ነበር፡፡ ይህ ግን ዮሃንስን በነበረበት ሁኔታ ውስጥ የሚረዳው አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ብዙ ጥያቄዎችን ጨምሮ እንዲጠይቅ፣ እምነቱም የባሴ እንዲጎዳ ያደርግ ይሆናል እንጂ፡፡ኢየሱስ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይሆን የቀረበበትን ሁኔታና ምክንያት በደምብ ተረድቶአል፡፡ ጌታ ይረዳሃል ወዳጄ።

ስለዚህ “በእምነትህ ጽና፣ አትጠራጠር” የሚል መለእክት በውስጡ ያዘለን ነገር ነገረው (በመልእክተኞቹ)፡፡የዮሃንስ አገልግሎት የተመሰረተው በእግዚአብሄር ቃል ላይ ነበረ፡፡ ለሌሎችም ሲሰብክ የነበረው የእግዚአብሄርን ቃል ነው፡፡ በተለይ የነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት የዮሃንስ ጥሪና አገልግሎት ውስጥ ትልቅ ተጽእኖ ነበረው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስም ዮሃንስን ወደዚያው የእግዚአብሄር ቃል ሊመልሰው ፈለገ፡፡ የዮሃንስ ጥያቄ መሲህው ሲመጣ “የታሰሩት ይፈታሉ” እኔስ አንቴ በዚህ እያለህ ለምን ታስረ እቆያለሁ? የሚል ነው። ቃሉ ለምን አልተተገበረም? እያለ ነው።

እግዚአብሄር በቃሉ ካወጣህ በቃሉ ደግሞ ይመራሃል፡፡ በቃሉም ያቃናሃል፡፡ በቃሉም ያጸናሃል፡፡ ቃሉ አይለዋወጥምና፡፡ ሰው ሰምቶ የወጣ፣ ሰው ሰምቶ ይመለሳል፡፡ ሰው አድንቆት የወጣ ሰው ንቆት ይመለሳል፡፡ ሰው ዛሬ “ሆሳይና” ካሌ ነጌ ደግሞ “ስቀለው” ይላል፡፡ ቃሉ ግን አይለዋወጥም፡፡ስለዚህ ኢየሱስ በኢሳይያስ 61 መሠረት በእርሱ የተደረገውን ነገር መልእክተኞቹ አይተው፣ ሰምተው ህዴው ለዮሓንስ እንዲነግሩት አደረገ፡፡ ኢየሱስና ዮሃንስ በቃል ይግባባሉ ማለት ነው፡፡

የእግዚአብሄር ቃል ለእውነተኛ አገልጋይ (ቢሮው ምንም ይሁን ምን) መሠረቱ፣ መለኪያውና መመዘኛው እንዲሁም መመሪያው ነው፡፡

የክርስቲና ህይወታችን በሚመጣብን የመከራ ብዛት እና ትንሽነት፣ ወይም በሰዎች ዘንድ በምናገኘው ተቀባይነት ወይ መገፋት ወይም ደግሞ በምድራዊ ነገሮቻቸንን በሚኖረን ስኬት ልክ የሚታይ አይደለም፡፡ መመዘኛው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡

የእግዚአብሄር ሃሳብ በአንተ ላይ መኖሩ በጤንነትህ ሁኔታ፣ በሀብትህ ብዛት፣ ወይም በሚታገኘው ተቀባይነት አይለካም፡፡ በአንቺም ላይ እንዲሁ። ምክንያቱም ብዙ እውነተኞች የእግዚአብሄር ሰዎች በመከራ፣ በሃዘን፣ በመገፋት፣ በበሽታ፣ በስዴት፣ በድህነት ወዘተ. ውስጥ እያለፉ ጌታን በዘመናቸው አስከብረውታልና፡፡ ይህ ማለት ግን ካልተቸገርን፣ መከራ ካልደረሰብን እኛ የእግዚአብሄር ሃሳብ የለብንም ማለት ደግሞ አይደለም፡፡

ብቻ የእግዚአብሄር እውነተኛ መልእክተኞች ብከብሩም በቃሉ፣ ብናቁም በቃሉ፣ ብቸገሩም ቃሉን ለማድረስ፣ ብሳካላቸውም ቃሉን አድርሰው ወይንም ለማድረስ ነው፡፡

ስለዚህ ኢየሱስ ዮሃንስ የገባበትን መከራ በመቃወም ወይም ደግሞ እሰየው በማለት አልሄደም፡፡ ነገር ግን ዮሃንስ የቆመለት የእግዚአብሄር ሃሳብ እየተፈጸሜ እንደሆነ እርግጠኛ እንዲሆን ማረጋገጫን ሰጠው፡፡ዛሬም ስለእምነታችንና አገልግሎታችን እግዚአብሄር ማረጋገጫን የሚሰጠን እኛን ወደ ቃሉ በመመለስ ነው፡፡ ወደ ቃሉ ስንመለስ እምነታችን መጽናትንና መጽናናትን ያገኛል፡፡

የዮሃንስን ደቄ መዛሙርት መልዕክት ሰጥቶአቸው ከሰደዳቸው በኋላ ስለ መጥመቁ ዮሃንስ ሲናገር ኢየሱስ እንድህ አለ:- “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም” (ቁ11) አለ፡፡

ይህም የሚያሳየው ሰዎችና ጌታ ሰውንና አገልግሎቱን የሚመለከቱበት መንገድ የተለያየ መሆኑን ነው፡፡ ሰው ሲንቅ፣ ጌታ ያከብራል፡፡ ሰዎች ሲያከብሩም ጌታ ሊንቅ ይችላል፡፡ ጌታ የራሱ ሚዛን አለው፣ ፍርዱ ደግሞ እውነተኛ ነው፡፡

ዮሃንስ የዓላማ ሰው ነው፡፡ ዮሃንስ ጥሪውን በትክክል ያውቃል፡፡ ጥሪውንም ሲያብራራ በቃሉ ውስጥ ሆኖ ነበረ፡፡ ሰዎች ስለማንነቱ ብዙ ያወሩ ነበረ፡፡ አንዳንዱ አሉታዊ ሌላው ደግሞ ያለ ልክ ከፍ የሚያደርገው ነበረ፡፡

እርሱ ግን “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፣ እኔ በምድረበዳ ውስጥ የሚጮህ ድምጽ ነኝ” ብሎ ነበር ራሱን ያስረዳ የነበረው፡፡ “አጋንንት አለበት” ስላሉትም ግራ አልተጋባም፡፡

ኢየሱስ እየተናገራቸው ያሉ ሰዎች ግን ግራ የተጋቡ ይመስሉኛል፡፡ ለዚያ ነው ኢየሱስ ደጋግሞ “ምን ሊታዩ ወጣችሁ?” ብሎ የሚጠይቃቸው፡፡ ጊዜያዊና ዘለቀታ የለሌውን ነገር ፈልገው፣ ምናልባት ስምና ዝናን ፈልገው የሄዱ፣ ምናልባት በጊዜያቸውን ትንሽ ልዝናኑበት አድስ ነገር ለማየት የሄዱ ሰዎች ልሆኑ ይችላሉ፡፡ ብዙዎች የሚፈልጉትን እንኳ አያውቁትም።

ኢየሱስ ሰዎች እንደ ዮሃንስ በእውነት ቃል ላይ የተመሠረተ ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚገባ በዚህ ክፍል ጠቁሟል፡፡

ኢየሱስ ዛሬም “ምን ልታዩ መጣችሁ?” ቢለን መልሳችን ምን ይሆን?የእግዚአብሔር ቃል የህይወታችን መሠረት ቢናደርገው መልእክቶቻችንን እና ተልእኮአችንን እንድንፈትሽ ይረዳናል። ጌታን ለመስማትና ከእርሱም ጋር ለመስማማት ይረዳናል።

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

ማቴ 11፡2-15

2 ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና፦

3 የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው።

4 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤

5 ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ

6 ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።

7 እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ፦ ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ?

8 ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ።

9 ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።

10 እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና።

11 እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።

12 ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል።

13 ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።

15 የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።

3 thoughts on “min litayu

  1. May the Lord bless you for the powerful message that the Lord brought to us through you, brother Teklu! Keep doing the good work of God’s kingdom!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *