SermonsTeachingsUncategorized

prepare the way

ማቴ 3፡1-12 የጌታን መንገድ አዘጋጁ

መጥመቁ ዮሃንስ የኖረውም ያገለገለውም በበረሃ እንደሆነ እናነባለን፡፡

ይህ በረሃ በአንድ በኩል፣ እንጨትና ውሃ በሌለበት ባዶ መሬት/ድንጋያማ ቦታ ላይ መሆኑን እንረዳልን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ልምላሜ ከራቃቸውና ምድረ በዳ በሚመስል (በዝምታ ዘመን) ሕይወት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የእግዚአብሄርን መንግስት ነገር እየተናረ፣ ባዶነታቸውን በፊሬያማነት እንዲቀይሩ እየመከራቸው መሆኑን እናስተውላለን፡፡

በዚህ ክፍል ዮሃንስ ለራሱ ስለሚኖርበት ምድረ በዳ ወይም በረሃማ ሕይወት ሲያጉረመርም አናይም፡፡ ነገር ግን ይህ ጥሪው ስለመሆኑ ማረጋገጫ አድርጎ እየተጠቀሜ፣ ዋናው መልእክቱ ላይ ያውጠነጥናል (ቁ ፫)። እርሱም “የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውንም አቅኑ” የሚል ነው፡፡

በዘመናችንም ሆነ፣ ምናልባት በጥንትም፣ አብዛኞች አገልጋዮች ወይም ሕዝባዊ አገልግሎትን የሚሠጡ ሰዎች ልብ ከሚሉአቸው ነገሮች አንዱ አለባበሳቸው ነው፡፡ ስለ ልብሳቸው ያስቡበታል፣ ድሬስንግ ኮዶችም አሉ፡፡ የዮሃንስን ሕይወት ስንመለከት ግን “የግሜል ጠጉር ይለብስ ነበር”፡፡ ይህ አይነት አለባበሱ፣ በሕዝብ ፊት ቆሞ የተሠጠውን መልእክት ከመናገር አልከለከለውም፡፡ አመጋገቡም ቢሆን፣ እንኳንስ ለመመገብ፣ ለአንዳንዶቻችን ለመስማትም የሚቀፍፍ ይመስላል፡፡ ዮሃንስ ግን ለራሱ እንዲመቸው ሳይሆን የእግዚአብሄር ፈቃድ እንዲሆን ራሱን ስለለዬ እንደችግር ያልቆጠረው ይመስላል፡፡

ሰውም የአለባበሱን መልካምነት አይቶ ወደ እርሱ አልሄደም፡፡ ሆኖም ግን ይዘቱ ሰማያዊ የሆነ፣ በሚሰሙት ላይ በጎ ተጽእኖ ማምጣት የሚችል መልእክት ይዞ ነበር የቀረበው፡፡ ስመስለኝ፣ ዮሃንስ ከሰዎች ጋር የሚቀላቀለው መልእክቱን ለማድረስ ብቻ ነበረ፡፡ ሌላው ሕይወቱ ከአምላኩ ብቻ ጋር የሚነጋገርበት የበረሃ ሕይወት ነበረው፡፡

የእርሱ አኗኗርና ስብከት ጥያቄ የፈጠረባቸው ሰዎች ሁሉ እየሄዱ ይሰሙት ነበረ፡፡ ከሰሙም በውሃላ ንስሃ ይገቡ ነበር። ወታደሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ፖሌትከኞች፣ ህዝቡም ከእያሉበት ቦታ ሁሉ ተነስተው እየሄዱ “እኛስ ምን እናድርግ” እያሉ ይጠይቁት ነበረ፡፡

የዮሃንስን ስብከት ሲሰሙም የሚሰማቸው/የሚታያቸው የየራሳቸው ሓጢአት ነበረ፡፡ ስለዚህ የየራሳቸውን ሃጢአት እየተናዘዙ ይጠመቁ ነበር፡፡

ዮሃንስ የእውነትን ቃል ከመናገር ራሱን የማይቆጥብ አይነት ሰው ነበረ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅና ምህረትን ማግኜት የሚፈልጉ ሰዎች ስብከቱን ይሰሙታል፡፡ ያልፈለጉትም ትተው መሄድ ይችላሉ፡፡ እርሱ የሚሰብከው የበረሃን ሕይወት ጠልቶ ወይም ብቸኝነቱን ጠልቶ ሰዎች እርሱ ወዳለበት እንዲመጡ ወይም እርሱን ከብበውት እንዲቀመጡ አልነበረም፡፡ ዓላማው፣ ሰዎች ስብከቱን ሰምተው ለሚመጣው ታላቁ የጌታ ቀን እንዲዘጋጁ ነበረ፡፡ የቀረቡበት ሕይወትና በረከት እንዳያመልጣቸው፣ የእግዚአብሄር መንግስት ሲገለጥ የበረከት ተካፋዮች እንዲሆኑ ለማዘጋጀት ነበረ፡፡

በአገልግሎቱ መጀመሪያ አከባቢ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃውያን አገልግሎቱን ንቀውት ሲያጣጥሉበት ነበረ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች እንኳ ወደ እርሱ ሄደው የእግዚአብሄርን ቃል እንዳይሰሙ ለማድረግ በሕዝብ መካከል መልካም ያልሆነ ወሬ እያሰራጩ ህዝቡን ግራ ያጋቡ ነበረ፡፡ እነርሱ በሕዝቡ መካከል የሚያሠራጩትን ወሬ ዮሃንስ በእባብ “መርዝ” ያስመስለዋል፡፡

እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እየከለከሉትም ቢሆን ሕዝቡ እየጎረፈ፣ ነፍሳቸው የሚትጠማውን የእግዚአብሄርን ቃል ለመፈለግ ዮሃንስ ወደ ተገኜበት የዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ይሰበሰቡ ነበረ፡፡ ልፋታቸውም ስላልተሳካላቸው አሁን የተለወጡ በመምሰል፣ በአካል ሄደው የዮሃንስን አገልግሎት ለማስቆምና ሕዝቡን ወደ ራሳቸው ጉያ ለመመለስ ፈሪሳዊያኑና ሰዱቃውያኑ ወደ ዮሃንስ ሲሄዱ እናያለን፡፡

ሲመጡም ዮሃንስ በግልጽ እንዲህ አላቸው፡- “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?”

እፉኝት በጣም መርዛማ ከሆኑት የእባብ ዘሮች አንዱ ነው፡፡ በብሉህ ክዳን እባብ በሰይጣን ተመስሎአል፡፡ ስለዚህ እነዚህም በሥራቸውና በዓላማቸው ከሰይጣን ጋር በመተባበር የእግዚአብሄርን ሕዝብ ከእግዚአብሄር መንግስት ስለሚከለክሉ፣ ዮሃንስ የእባብ ልጆች ብሎ ጠራቸው፡፡

ይህንን የሚመስል አባባል ኢየሱስም በሃላ ሲጠቀም ከዮሃንስ ወንጌል(8:44) እናነባለን፡፡ “የድያብሎስ ልጆች” ብሎአቸው፡፡ ራስንና ሌሎችን ከእግዚአብሄር መንግስት ከመከልከል የበለጠ፣ ሰዎችን የዲያብሎስ ልጆች የሚያስብል ሌላ ምንም የለም፡፡

እንግዲህ ዮሃንስ ሰዎቹን ባዬ ጊዜ የሰጣቸው ማስጠንቀቂያ፣ “ፍሬ አድርጉ” የሚል ነበረ፡፡ ወሬና ትምክህት(ቁ 9) አያድንም፡፡ ስምና ዝና ወደ እግዚአብሄር መንግስት አያስገባም፡፡

ሌሎችን ለመምሰልና ለመቀላቀል ተብሎ የሚሆነው የሃይማኖተኝነት ሥርዓትና ቋንቋም እውነተኛውን ንስሓ አይገልጥም፡፡ “የንስሃ ፍሬ” ከንስሃ ገቢው ሕይወት መታዬት አለበት ይላል ዮሃንስ፡፡

የፈሪሳዊያኑ የሳዱቃውያኑ አስተሳሰብ: አብርሃም እኮ ከእኛ ውጪ ሌላ የቃል ክዳን ልጆች የሉትም የሚል ነበረ፡፡ መጥመቁ ዮሃንስ ግን “እግዚአብሄር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያደርግ ይችላል” ባይ ነው፡፡

ጥያቄው መሆን ያለበት ስለአብርሃም ወይም ስለሌሎች ሰዎች ሳይሆን፣ ስለግል ነፍሶቻቸው ነው፡፡ ለአብርሃም ከመጨነቅ ይልቅ ዛሬ ያገኙትን እድል ተጠቅመው ወደ እግዚአብሄር ራሳቸውን መመለስ ነው፡፡

እኛም ዛሬ ከዚህ መማር አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስንሰማ፣ ስለሰዎች፣ ስለሃይማኖት ቤቶች፣ ስለሰባኪዎች እና ስለሽማግሌዎቹ ሳይሆን በግል እግዚአብሄር ምን እየተናገረኝ ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡

ልክ ያኔ ዮሃንስ “ቀርቦአል” ብሎ ከተናገረው የበለጠ፣ ለእኛም የእግዚአብሄር መንግስት ቀርባለችና፡፡ ከእኔና ከእናንተ እግዚአብሄር ዛሬ የሚፈልገው፣ ቶሎ ብለን ወደ ምህረቱ እንድንጠቀለል ነው፡፡ ቶሎ ብለን ንስሃ እንድንገባ፣ ቶሎ ብለንም ከእርሱ ጋር እንድንታረቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ እጅግ አስደናቂ የሆነ የምህረት እጅ ዛሬ ለሚመለሱ ሁሉ ተዘርግቶ አለ፡፡ “ኑ!” እያሌ ይጣራል፡፡ “ኑ!”

በሌላው አንጻር ደግሞ የምህረት እጁን መሰብሰብ ብቻ የሚጠብቅ ለመቁረጥ የተሳሌ ምሳር ደግሞ ከእያንዳደንዱ “ዛፍ ሥር ተቀምጦአል”፡፡ አምልጬ እና ሸውጄ እገባለው ብሎ ለሚያስቡ ደግሞ “መንሻ” ተዘጋጅቶአል፡፡ መንሻው ገለባንና ስንዴን ለመለየት ሲባል ለንፋስ የሚሰጥ መሳሪያ ነው፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ለስንዴ የተዘጋጄ ጎተራ እና ለገለባ የተዘጋጄ እሳት አለ ይላል ዮሃንስ፡፡

ቀጣዩ ዘመን እንደዛሬው ሁሉም ተቀላቅሎ የሚኖርበት፣ ስንዴና ገለባ ተሰባጥሮ የሚቀመጥበት ጊዜ አይደለም፡፡ የሚወሰደው እርምጃም እንደዛሬው የማባበልና የርህራዬ አይደለም፡፡ ጎተራውም እሳቱም ሁለተኛ ስንዴውና ገለባው ላይቀላቀሉ ለመለዬት የተዘጋጁ ቦታዎች ናቸው፡፡

ስለዚህ ‹ራሳችሁን ለማባበል፣ መልካም ሆናችሁም በዓይናችሁ ፊት ለመታዬት ምክንያቶችን አታብዙ› ይላል ዮሃንስ፡፡ ‹ንስሃ ግቡ፡፡ ንስሃ መግባታችሁ ደግሞ እውነተኛ መሆኑን የሚያሳይ ፍሬ አፍሩ› ይላቸዋል፡፡

ለማጠቃለል

  1. ዮሃንስ ታማኝ መልእክተኛ ነበረ፡፡ ለጥሪው ራሱን የለዬ፣ እለት ተእለት ከሚያጋጥሙት የበረሃ ሕይወት ተግዳሮት ይልቅ እግዚአብሄርን በመፈለግና ተልዕኮውን በአግባቡ ለመፈጸም የተጋ አገልጋይ ነበረ፡፡ እኛም ከእርሱ ተምረን፣ እግዚአብሄርን በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችንም መውደድና መከተል አለብን፡፡ ከምቾቶቻችን ይልቅ ለእግዚአብሄር ፍላጎት ቦታ እንስጥ፡፡
  2. በሙሉ ልባቸው የእግዚብሄርን ቃል የተጠሙና የፈለጉ ሰዎችን እናያለን፡፡ ቃሉን ስለፈለጉ ብቻ ከሰፈርና ከመንደር ወጥተው፣ ከምኩራብና ከቤተ መቅደስ ወጥተው በምድረበዳ የሚጮኽ ድምጽ ለመስማት ሄዱ፡፡ በዚያም ምክር እየተቀበሉ፣ ንስሃ እየገቡ የሚጠመቁ ነበሩ፡፡ ዛሬም በቅን ልብና በእውነተኛ መጸጸት ወደ እግዚአብሄር የሚመለሱ ኃጢአተኞችን ሁሉ ለመቀበል፣ ለመምከርና ይቅር ለማለት የእግዚብአብሄር እጅ ተዘርግቶ አለ፡፡ ስለ ሌሎች ሳይሆን ስለራሳችን ብለን እግዚአብሄርን መከተል ይኖርብናል፡፡ እስቲ ትንሽ ጊዜ ወስደን እናስብ፣ እግዚአብሄር ዛሬ ንስሃ እንድንገባ የሚፈልገው ከምንድን ነው?
  3. በንባቡ ውስጥ፣ በእግዚአብሄር ቤት የተቀመጡ ነገር ግን ራሳቸውንና ሌሎችን ሰዎች ከእግዚአብሄር የሚያሪቁ ሃይማኖተኞች ነበሩ፡፡ እነርሱን ዮሃንስ ሲጠራቸው “የእፉኝት ልጆች” ብሎአቸው ነው፡፡ እነርሱም ቢሆኑ አሁን የንስሃ እድል አላቸው፡፡ አሁን መናዘዝም መተውም ይችላሉ፡፡ እነርሱንም ቢሆን እግዚአብሄር ለመቀበል እጁን ዘርግቶአል፡፡ ሆኖም ግን በለመዱት መልኩ መሄድ ከፈለጉ፣ ይህንን የንስሃ ጊዜ ወይም እድል በማስመሰል ብቻ ማለፍ የሚፈልጉ ከሆነ፣ ትልቅ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በመናገር ዮሃንስ ያስጠነቂቃቸዋል፡፡ እኛም ብንሆን ዛሬ፣ በማናቸውም ሃጢአትና በደል ውስጥ ገብተን ከሆነ፣ በድርግቶቻችንም ራሳችንና ሌሎችንም ጎድተን ብሆን እንኳ ይህችን የንስሃ እድል ተጠቅመን ወደ እግዚአብሄር ምህረት የመሸሽ እድል አለን። ሆኖም ግን እግዚአብሄር ለንስሃና ለመመለስ የሰጠንን ጊዜ በዋዛ እና በማስመሰል ለማሳለፍ ተዘጋጅተን ከሆነ፣ ሊመጣ ካለው በረከት መካፈል እንድሁም ሊመጣ ካለው ቅጣት ለማምለጥ አንችልም፡፡
  4. የምህረት በር ከተዘጋ በኋላ የቁጣ መዓት አለ፡፡ ለምህረት የተዘጋጄው የእግዚአብሄር ክንድ ጊዜው አብቅቶ ከታጠፈ፣ በቁጣ ደግሞ መገለጡ አይቀረ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ምህረት የተጠቀለሉ ቅዱሳን በስንዴ ሲመሰሉ፣ በአመጻ መቀል የሚፈልጉ ደግሞ በገለባ ተመስለዋል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሁለተኛ ላይገናኙ እና ለዘላለም ልለያዩ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ጎተራው የእግዚአብሄር መንግስት ነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ከእግዚአብሄር መልካምነት ተለይቶ ለዘላለም በሥቃይ መኖርን የሚገልጥ ነው፡፡

ስለዚህ ሁላችንም ዛሬ እድሉ አለን፡፡ ሁላችንም በድለናል፡፡ ሁላችን የእግዚአብሄር ምህረት ያስፈልገናል፡፡ ሁላችንም በደጉ እግዚአብሄር እየተጠራን ነው፡፡ ስለዚህ ወገኖቼ፣ ኑ፣ ሕይወትን እንምረጥ፡፡

የማቴዎስ ወንጌል 3

1-2 በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።

3 በነቢዩ በኢሳይያስ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና።

4 ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ።

5 ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤

6 ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።

7 ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?

8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤

9 በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፦ ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።

10 አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።

11 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤

12 መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *