SermonsTeachings

On the Cross

ሉቃስ 23:33-43

በዚህ ክፍል ውስጥ ያነበብነው ታሪክ፣ በቀን ብርሃን በብዙዎች ሰዎች ዓይን ፊት፣ ሀገሩና ሀገረ-ገዢዎችም እያዩ እና እያወቁ የተደረገ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡

የዛሬው ዘመን ቢሆን ኖሮ፣ ላይቭ (ቀጥታ) በሶሻል ሚዲያዎችና በታወቁ የዜና አውታሮች የሚተላለፍ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ኢየሱስ በሌሊት ተይዞ፣ እየተሰደበ፣ እየተገፈተረና እየተመታ ወደ ሃይማኖት መሪዎችና ወደ ሀገረ ገዢዎች ተወሰደ፡፡ በሀገረ ገዢው ጴንጤናዊው ጵላጦስ የተደረገ ምርመራም በኢየሱስ ላይ ጥፋት አለመገኜቱን አረጋገጠ፡፡ ስለዚህ ጵላጦስ ለራሱ የማያምንበትን ፍርድ ህዝቡ እንዲፈርድ ለሕዝብ አቀረበው፡፡

“ሕዝብ” ተብለው የቀረበው በሓይማኖት መሪዎች ግፍት ሥር ወድቆ ስለነበረ፣ የራሱን ምርጫ ለማድረግ ይችል ዘንድ በቂ መረጃ እና ሙሉ ነጻነት አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡ ፈሪሳዊያንና ሳዱቃውያንና ፃፍት ባደረጉበት ተጽኅኖ ውስጥ ሆኖ “ሕዝቡ” እነርሱ የሚፈልጉትን ያወራል(ማቴ 27:20)፡፡ ህዝብን ማባበሉ፣ ጫናቸውም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከዚህም በፊት ኢየሱስ ሲያደርግ ያየውናና የታዘበውን እውነት እንኳ መናገር ወይም ማሰብ ያልቻሌ ህዝብ ነበረ፡፡ ስለዚህ ጥፋት ያልተገኘበት ኢየሱስ ወንጄለኛውን በርባንን ተክቶ እንዲሞት ይጮኹ ነበር፡፡ ያውም የመስቀልን ሞት፡፡ “ይሰቀል!” “ይሰቀል!” “ይሰቀል!” እያሉ፡፡

ፍትህ በጎደለበት ፍርድ የመስቀል ሞት ከተፈረደበት በኋላ፣ ኢየሱስ ከባዱን መስቀል ተሸክሞ የጎልጎታን አቀበት መውጣት ጀመሬ፡፡ የደረሰበት ኢ-ሰብዓዊ ድርግት አቅሙን አድክሞና ጎድቶት ቢሆንም፣ በብዙ መገፋትና መናቅ ውስጥ ሆኖ ተራራውን መውጣት ግድ ሆነበት፡፡

በርግጥ ያንን ሲያደርግ ኢየሱስ እኛንም እያሰበን ነው፡፡ ሲታገስም ድካሙ በከንቱ እንደሆነ ያውቅ ነበረ፡፡ እንደሰው ሲታሰብ ግን ሁኔታው በራሱ ከባድ እንደነበረ ለመገመት አያስቸግርም፡፡

ቁ. 33 “ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ።”

በሚያሳዝንና ጭካኔ በሞላበት መንገድ ኢየሱስን በመስቀል ላይ ሰቀሉት፡፡ ሲሰቀል ግን ብቻውን አልነበረም፡፡ ክፉ አድራጊዎች በቀኙና በግራው ተሰቅለው ነበረ፡፡ ይህም ደግሞ ሰዎች ገና በግራ ያለውን ወይም በቀኝ ያለውን ወይም ሁለቱን ሲመለከቱ ኢየሱስንም በእነርሱ ልክ እንዲያዩት ያደርገዋል፤ በመስቀል ላይ የሚታዩት 2/3ኛው (66.67%) በእውነትም ወንጀለኛ ወይም “ክፉ አድራጊዎች” ነበሩና፡፡

ያለቦታው (በክፉ አድራጊዎች መካከል) ስላስቀመጡት፣ ኢየሱስን አሳንሰውታል፡፡ ወንጀለኛም አድርገውታል፡፡ ባርባን ጻድቅ ሆኖ ኢየሱስ በወንጀለኛነት ተፈርጆ ነበርና፡፡ እውነቱንም ማንም እንድያውቅ አልተፈለገም፡፡

በነገራችን ላይ፣ ባርባን ከቀኝ ገዢዎች እጅ ለመውጣት በሚደረግ አብዮት ውስጥ በቀጥታ ሲሳተፍ የተያዘ ነበረና፣ በቀኝ ገዢው መንግስት ወንጀለኛ፣ በሌሎች ዘንድ ደግሞ ጀግና ተደርጎ የሚታይ ነበረ፡፡ የሃይማኖት መሪዎቹና የሽማግሌዎቹ ኢየሱስን የማስወገድ ፍላጎት እንጂ የባርባን ፍቅር ይዞአቸው አይመስለኝም። ጵላጦስም ቢሆን ጭንቀቱ ሥልጣኑ ነበረ።

ስለዚህ ጥቂት ህዝቡ የሚፈልጉትን ነገሮች በማድረግ አብዮቱን ለማክሸፍ አሰበ። ለዚህም ጵላጦስ ሁለት የማይፈልጋቸው ነገሮችን አደረገ፡፡ 1ኛ በጣም ሊገድለው የሚፈልገውን ባርባንን ለቀቀው፡፡ 2ኛ በጣም በንጽህኛው ያመነበትን (መርምሮ የደረሰበትን) ኢየሱስን ለስቅለት አሳልፎ ሰጠው፡፡ኢየሱስም በሁለቱ ክፉ አድራጊዎች መካከል ተሰቅን እያለ፣ ሰቃዮቹ ምን እያደረጉ እንደሆን አያውቁም፡፡ ይሳለቁበታል፣ ያፈዙበታል፣ ይሰድቡታል፡፡

ቁ 34 “ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት።”

ይህን አስቡ፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ፣ ስለሰቃዮቹ ይጨነቅ ነበረ፡፡ እግዚአብሄር ይቅር ካላላቸው፣ እያደረጉት ያሉት ነገር ወደ ዘላለም ቅጣት ይወስዳቸዋል፡፡ “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!” ይላልና እግዚአብሄር (ኢሳ 5፡20-24)፡፡ ትክክለኛው ፍርድ ይመጣል።

ስለዚህ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ ስለራሱ ደንነት ሳይሆን፣ በግፍ ስለሰቀሉት ሰዎች ይማልድ ነበረ፡፡እነርሱ ግን ኢየሱስ የሚናገረው ነገር የገባቸው አይመስሉም፡፡ ክፉ የሚያደርጉ ክፋታቸውን አሁንም እየቀጠሉ ነውና፡፡ ቀጥለው፣ “ልብሱን እየተከፋፈሉ፣ “ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ”፣ መኳንንቱም ያፈዙ፣ ጭፍሮችም በጭካኔ ሆምጣጤ ያጠጡት እና ይዘብቱበት (ቁ34-37) ነበሩ፡፡ ጵላጦስም ቅን ያልነበረውን ፊርዱን ትክክል እንዳልሆነ እያወቀም፣ የክስ ወንጀሉን (የፖለትካ እና የሀገር ክህዴት አስመስሎ) ጽፎ በመስቀሉ ላይ እንዲያስቀምጡ አስደርጎአል (ቁ38)፡፡

በኢየሱስ ላይ የተጻፈውን ክስ ከሳሾቹም፣ ፈራጆቹም ትክክል እንዳልሆነ እያወቁ፣ ግን አጋጣሚ ደግኝተው ኢየሱስን በመስቀሉ ላይ ሊያዩት ወይም ስለእርሱ ሊሰሙ የሚችሉ ሰዎች ወንጀለኛ መሆኑን እዲያውቁ ለማድረግ ክሱን በአከባቢው ቋንቋ፣ በእምፓዬሩ የሥራ ቋንቋ እንዲሁም በአንጻራዊነት የአለም አቀፍ ቋንቋ ተርጉሜው በመስቀሉ ላይ አስቀመጡ፡፡ ክሱን ሰቃዮቹም አሰቃዮቹም አያምኑበትም ግን ኢየሱስን ለማስወገድና ራሳቸውን ሊነሳባቸው ከሚችለው ተጠያቂነት ለማስመለጥ ክስ ፈጥረው፣ አስተርጉሜው ለጠፉበት፡፡

ይህ በልብ ክፋት እየተደረጌ ያለው ነገር የእግዚአብሄር የጽድቅ ፍርድ ሲገለጥ ያስቀጣቸዋል፡፡ ሰው ከሰው ዓይን ሊሰወር ይችላል እንጂ ልብን ከሚመረምር፣ የልብንም ሓሳብ ከሚያውቅ ከእግዚአብሄር ሊሰወር አይችልም፡፡ ስለዚህ ነው ኢየሱስ ይቅርታን የለመነላቸው፡፡ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ፡፡ሰዎቹ ወዲያው “አሜን” ብለው ጸሎቱን አልተቀበሉትም፡፡ ኢየሱስ ግን ባይቀበሉም ይቅር አላቸው፣ አባቱም ይቅር እንዲላቸው ለመነላቸው፡፡እነርሱ የእግዚአብሄርን ልጅ እየሰቀሉና እየተሳደቡ እየዘበቱበትም አሉ፡፡ ቃሉ ደግሞ “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።” ይላል (1ሣሙ 2፡10)፡፡

ኢየሱስ ያ መድቀቅ ሳይመጣባቸው ምህረትን እየለመነላቸው ነው፡፡የምህረትን ቀን አለማወቅና ምህረትን አለመቀበል ምንኛ ያሳዝናል? አንቴ ከእግዚአብሄር ጋር ታረቅህ ወይ? አንቺስ?

ቁ “39 ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፦ አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው።”

ይህ ሰው ሞት የተፈረደበትና በመስቀል ላይ ያለ ሰው ነው፡፡ በቀረውችው ጥቂት ደቂቃዎች ወይም ሰዓታት ዘላለሙን የመቀየር እድል ግን ነበረው፡፡ ሆኖም ግን ራሱ ተሰቅሎ ከሰቃዮች ጋር ሆኖ በኢየሱስ ላይ ስድብን ይናገር ነበረ፡፡ በልቡም ይንቀው ነበረ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ መሆኑን አላመነም፣ አዳኝነቱንም መዘባበቻ አድርጎታል፡፡ ምናልባት ከሕዝቡና ከጭፍሮቹ፣ ይልቅ ኢየሱስ ስለምህረት የጸለየውን ጸሎት በደንብ የሰማ ሰው ነበረ፡፡ ግን “እኔም በደለኛ ነኝና ይቅር በለኝ” ከማለት ይልቅ፣ ለተፀለየውም ጸሎት አሜንታ ከማስተጋባት ይልቅ ኢየሱስን መሳደብ ቀላል ሆኖ ታየው፡፡ ከወዳጁም (ከሌለኛው ክፉ አድራጊ) በጥቂት ግዜ ጸሎቱ ለዘላለም ተለየው።

ዛሬም ቢሆን ክርስቲያኖች በችግርም፣ በመካራም፣ በስደትም ሆነው የሚሰብኩትንና የሚማልዱትን መልጃ ሰምተው ወደ እግዚአብሄር ከመመለስ ይልቅ የሚሳደቡ ወገኖች አሉ፡፡

ኢየሱስ ለዚህ ስድብ መልስ ሲሰጥ አንመለከትም፡፡ ይልቁንስ በምህረት የሚታመን፣ ኢየሱስ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን የተቀበለ፣ ሰው በሌለኛው ጎኑ ነበረና እርሱ ለለመነው ሊመና መልስ ሲሰጥ እንመለከታለን፡፡ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (ቁ 42) አለው።

ወገኖቼ፣ በበሽታ፣ በችግር፣ በረሃብ፣ በጦሪነት፣ በእርጅና፣ በተለያዩ አደጋዎች ይህችን ዓለም ከመልቀቃችን በፊት ምን ያክል ጊዜ እንደቀረን አናውቅም፡፡ ግን ይህችን የቀረችንን እድሜ እንዴት እናሳልፍ? እግዚአብሄርን በመሳደብ ወይስ ለምህረት ወደ ተዘረጋችው የእግዚአብሄር እጅ በመሸሽ?ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት፣ መንገድ፣ ሕይወትም” ነው፡፡ መጽሓፉም እንደሚለው “በልጁ የሚያምን የዘላለም ህይወት አለው”።

ጌታ ይባርካችሁ

ተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *