SermonsTeachingsUncategorized

ሊያከብሩ የተመለሱ

ሉቃ 17፡11-19 (የምስጋና አምልኮ የበረከት ምንጭ ነው፡፡)11 ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። 12 ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ 13 እነርሱም እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። 14 አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። 15 እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ 16 እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። 17 ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? 18 ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። 19 እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።

ጌታ ምስጋናችንን ይፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ ተደርጎልን ግን ማመስገን እንረሳለን፡፡ በዛሬው የወንጌል ክፍል ውስጥ ያለው ታሪክ የሚያሳየን ከመንደር ወጣ ብለው የሚኖሩ አስር ለምጻሞች ነበሩ፡፡

በካህን ተመርምሮ ተላላፊ መሆኑ የታመነበት የቆዳ በሽታ ስላለባቸው ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ሰዎቹ ከመንደር ወይም ከከተማ ወጥተው ከሰው ተለይተው እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡በኃላ እንደምንመለከተው ችግራቸው በእምነትና በባህል የተለያዩትን ሰዎች አንድ ላይ አኑሮአቸዋል፡፡

እነዚህ ሰዎች ስለኢየሱስ አስቀድሞውኑ ሰምተዋል፡፡ ምክንያቱም ስሙንና የማዳን አቅም እንዳለው ያወቁና ያምኑ ነበረ፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ እነርሱ ባሉበት አከባቢ ሲመጣ ከርቀት ቆመው፣ “እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ።”

ሰዎቹ የራሳቸው ልዩነቶች ነበሩአቸው፡፡ የዜር ወይም የጎሳ፣ የባህል፣ ምናልባትም የሃብት፣ የትምህርት፣ ወዘተ.፡፡ ሆኖም ግን ሁለት ነገር አንድ አድርጎአቸዋል፡፡ ችግራቸው/በሽታቸው እና ጸሎታቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች የምመና ስብስብን ይመስላሉ፡፡ ለምጽ በመጽሓፍ ቅዱስ መሠረት የኃጢአት ምሳሌ ነው፡፡ ሁሉም ባሉበት ቦታ የሆኑት ለምጻቸው አስገዳጅ ስለሆነባቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ተገልለው ሲኖሩ፣ በሚአዩአቸው ዘንድ አስሩ ለምጻሞች ተብለው ይገለጻሉ፡፡ ችግራቸው አንድ አድረጎአቸዋልና፡፡

በሌላው ጸሎታቸው ነው፡፡ ምኞታቸው፣ ልመናቸው የእግዚአብሄርን ምህረት ማግኘት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም በአንድ ላይ በመስማማት ለምህረት ጮኹ፡፡ “ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ።”ጌታም ጩኼታቸውን ሰማ፡፡

ሰዉ ከሰው መካከል ተገልሎም፣ ከማህበረሰብ መካከል ተገልሎም፣ ከሃይማኖት ቤቶች ተገፍቶም፣ ቢሆን ወደ እግዚአብሄር ድምጹን ማሰማት ይችላል፡፡ ሃጢአተኛ፣ ለምጻም፣ በሽተኛ፣ የእከሌ ዘር የእከሌ ጎሳ መሆን እግዚአብሄርን ከመስማትና ከመማር አይከለክልም፡፡ ምህረት ፈላጊ ነፍስ ባለችበት ሆና “ጌታ ሆይ ማረኝ” ቢትል መሃሪው ጌታ ይምራታል፡፡ ከሪቀትም ቢሆን ይሰማታል፡፡

ለምጻሞቹ የኢየሱስን ምህረት ለመኑት፡፡ ኢየሱስም በሙሴ ህግ ውስጥ ተጽፎ እንዳለው ከበሽታቸው መንጻታቸውን ወደ ካህን ህደው እንዲያሳዩ ነገራቸው፡፡ ምናልባት ሊሄዱበት የሚችለው ካህን አስቀድሞውኑ ለምጻሞች መሆናችውን አረጋግጦ ከህዝብ መካከል ራሳቸውን እንዲያገሉ ያዘዛቸው ካህን ሊሆን ይችላል፡፡ ኢየሱስ በሽታውን ያረጋገጠው “ዶክተር” ፈውሱንም እንዲያረጋግጥላቸው ፈልጎአል፡፡ ስለዚህ ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አሳዩ አላቸው፡፡

በታሪኩ መሠረት፣ ሰዎቹ እምነት ያላቸው ይመስላሉ፡፡ ኢየሱስ ያዘዛቸውን አምነው ስለተቀበሉ በሽታው ገና በላያቸው ላይ እያሌ ወደ ካህኑ ጉዞ ጀመሩ፡፡ በመንገድ ላይ እያሉ ግን አንዳች ነገር ገብቶአቸዋል ወይም ተሰምቶአቸዋል፡- መፈወሳቸው፡፡ “እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ።“ ይላልና ቃሉ፡፡ በእምነት ወደ ጌታ የሚትለምን ነፍስ በእምነትም የሚትታዘዘው ነፍስ ከጌታ ዘንድ ምህረትን ታገኛለች፡፡ አስሩም ከነበረባቸው የቆዳ በሽታ ነጽተዋል፡፡ ኢየሱስ “አሥሩ አልነጹምን?” ብሎ ሲጠይቅ አሥሩ ስለመንጻታቸው እርግጠኛ ነበረ፡፡

ከተፈወሱትም መካከል አንዱ፣ ሳምራዊ የሆነው፣ በሰውም እይታ ከሌሎቹ ይልቅ ሓጢአተኛ ተደርጎ የሚታሰበው ለምስጋና ተመለሰ፡፡ የምስጋነው አቀራረብም ያለ ምንም መቆጠብና ይሉኝታ ነበረ፡፡ “በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ”፡፡ኢየሱስን ግን የሰውዬው መመለስ ብቻ ሳይሆን የሌሎቹ አለመመለስ ገረመው፡፡ ወደትም እንዳሉ ጠየቃቸው፡፡ አስተውሉ፣ ሰዎቹ አልተፈወሱም አይለንም ቃሉ፣ ካህኑ ፈውሳቸውን አላጸናምናምም አይለንም፡፡ ነገር ግን ተመልሰው መጥተው አላመሰገኑም ነው፡፡

መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፣ እግዚአብሔር የጸጋ ሁሉ አምላክ ነው፡፡ ለመልካሞቹና ለክፉዎቹ እኩል ዝናቡን ያዘንብላቸዋል፡፡ ጸሓይንም ያወጣላቸዋል፡፡ በዚህም ቦታ ለለመኑት ሁሉ ስለመናቸውን ሰጥቶአቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ምስጋና ያቀረበው ከአስሩ አንድ ተጠቃሚ ብቻ ነበረ፡፡

ዘጠኙ ምስጋና የሌላቸውም ሆነ ብቸኛ አመስጋኙ፣ ሁሉም አንድ እኩል ነገር ነበር የተሠጣቸው፡- ከለምጻቸው መፈወስ፡፡ አመስጋኙ አሁን ተጨማሪ ነገር አግኝቶአል፡፡ በጌታ ዘንድ የከበረው እምነቱ ተመሰከረለት፣ ደንነትና በረከትንም ጨምሮ ተቀብሎአል፡፡ “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።” ድነት ከፈውስ ይበልጣል፡፡ ጌታን በሕይወታችን ከሚደሰትባቸው ነገሮች አንደኛውና ዋነኛው የነፍሳችን ፈውስ ነው፡፡ ደንነት ማግኘታችን፡፡ለተደረገልን ማንኛውም ነገር እግዚአብሄርን ማመስገን ስንለማመድ፣ ብዙ ተጨማሪ በረከቶችን ከእግዚአብሄር እንቀበላለን፡፡ ስለመቀበሉ ብቻም አይደለም፡፡ እስቲ አስቡ፣ ሕዶ በጌታ ፊት ተገኝቶ ከእርሱ ጋር መነጋገርስ ምነኛ ትልቅ በረከት ነው፡፡ ወደ እርሱ ቀርቦ ከሥጋ ፈውሱ የሚበልጠው ምህረቱና ደንነቱ በሕይወታችን መኖሩን ከአፉ ስንሰማ አያስደስትምን?

አንድ ሰው ለጸሎትም ሆነ ለምስጋና በእግዚአብሄር ፊት በሚቀርብበት ጊዜ መገንዘብ ካለበት ነገር አንዱ በትልቁ በእግዚብሄር ፊት መገኘቱ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ በፍቅርና በትህትና የሚቀርቡትን በበረከት ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡

ምናልባት ሌሎቹም በደስታ ወይም በምስጋና ጮኼው አመስግነው ሊሆን ይችላል፡፡ ደስም እያላቸው ወደ ቤታቸው ሄደው ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ተመልሰው ጌታነ ማመስገን ያልቻሉት በጣም የናፈቁአቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለማዬት፣ ምናልባትም ከረጅም ግዜ ወደ ተለዩት የሥራ ገበታቸው ቸኩለው ለመመለስ ሊሆንም ይችላል፡፡ አናውቀውም፡፡ በትክክል መናገር የምንችለው ግን ለምስጋና ወደ ኢየሱስ አልተመለሱም፡፡ ይህ ድርግታቸው ወይም ውሳኔአቸው ደግሞ ጌታን ደስ አላሰኘውም፡፡

ወገኖቼ፣ ጌታን ለአንድ አይነት በረከትና ፈውስ ብቻ አንከተለው፡፡ ከጌታ ያገኜነውንም ብቸኛ በረከት ይዜን ሌላ ነገር እንደማያስፈልገን ሆነን ከጌታ አንሽሽ፡፡ጌታ ምህረት አድርጎልን ከሆነ፣ ጌታ ከበሽታ ፈውሶን ከሆነ፣ ጌታ ሥራ ሰጥቶን ከሆነ፣ ጌታ የትምህርት በር ከፍቶልን ከሆነ፣ ጌታ የትዳር ጓደኛ ሰጥቶን ከሆነ፣ ጌታ የተሸሌ ሕይወት የምንመራበትን ማንኛውንም ነገር አድርጎልን ከሆነ፣ ደስ እያለን ቀርበን እናመስግነው፡፡ በፊቱ እንውደቅና “ተመስን” እንበለው፡፡ ያቺ ያገኘናት አንድት ወይም ጥቅት ነገር ለዘላለም ከጌታ ፊት ይዞን አይህድ፡፡ ጌታ ይጠይቃል፡፡ “አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ?” ይላል፡፡

ሓይማኖተኝነትና ዝና ብቻ ጌታን አያስደስተውም፡፡ በእውነትና በፍቅር በሆነ አምልኮ፣ ጌታ ያደረገውን ጥቅት ነገር እንኳ ሳይንቅ የሚያከብር ልብ ግን ተጨማሪ በረከትን ከጌታ ይቀበላል፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *