SermonsTeachingsUncategorized

ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል

ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና(ማቴ 3:3-17)

13 ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።14 ዮሐንስ ግን፦ እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር።15 ኢየሱስም መልሶ፦ አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት።16 ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤17 እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።

አንድ ዮሃንስ የሚባል ሰው የንስሃ ስብከት እየሰበከ ሰዎችን የንስሃ ጥምቀት ያጠምቅ እንደነበረ፣ ከጥቅት ሳምንታት በፊት አብረን አይተን ነበር፡፡

ዮሃንስ ሲያጠምቅ የነበረው ሰዎች ከሓጢአታቸው እንዲመለሱ ነበረ፡፡ ሰዎቹም ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ መጸጸታቸውንም በመጠመቅ ይገልጡ ነበረ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ግን አንድ ፈጽሞ ኃጥያትን ያላደረጌ. ሰው በጢአተኞቹ መካከል ተገኜ። ሊጠመቅ።

ኢየሱስም ዮሃንስ ሲያጠምቅ ወደ ነበረበት የዮርዳኖስ ወንዝ በዮሃንስ እጅ ሊጠመቅ መጣ፡፡ ይህ እየሱስ እያደረገ ያለው ነገር አግባብነት ያለው ነገር ሆኖ ለዮሃንስ አልታየውም፡፡

ስለዚህ አጥማቂው ዮሃንስ ኢየሱስን ሊያስቆመው ሞከረ፡፡ ከለከለው። ኢየሱስ ግን እርሱም የሚጠመቅበትን ምክንያት እና ዮሃንስ ደግሞ የሚያጠምቅበትን ምክንያት በመናገር እንዳይከለክለው ጠየቀው፡፡ “ፍቀድልኝ” አለው።

ይህ ዮሃንስ ያደረገው ነገር፣ እኔና እናንቴም በእርሱ ቦታ ብንሆን የምናደርገው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዮሃንስ “ከእርሱ የሚልቅ”፣ “የጫማውን ጠፈር እንኳ መፍታት የማይገባው “ እንደሆነ ሲናገር ነበርና የክብሩን ከፍታና የማንነቱን ሊቀት በከፊልም ቢሆን ተረድቶአል፡፡

በዚህም መረዳት፣ ስራሱ ማንነት ስጠይቁት ለነበሩት ሰዎች እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፡፡ “እርሱ ሊልቅ እኔ ላንስ ይገባኛል” በሚል መፈክር ያገለግል ነበረ፡፡ ስለዚህ ያ መላቅ ያለበት ሲመጣ ነገሮችን ለእርሱ፣ ክብርን ለእርሱ ስልጣን የማስረከብ ፍላጎቱ የተወሳሰበ ነገር አይመስለኝም፡፡

ሌላው፣ ሰው በሰው ፊት ሲቆም ጻድቅ ሆኖ መታየት ይችላል፡፡ ጻድቃን የተባሉት ግን ራሳቸውን በጌታ ፊት ሲያዩ ድካማቸውና ስንፍናቸው ይከሳቸዋል (ኢዮብ 4:18; 15:15; 25:5)። ስለዚህም ሌሎችን እያናዘዜ የሚያጠምቀው ዮሃንስ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ፣ ተናዝዞ በእርሱ እጅ መጠመቅን ተመኘ፡፡

ይህ የዮሃንስ ምኞት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ነበር የመጣው፡፡ ሌሎች ኃጢአታቸውን ስናዜዙ ኢየሱስ ግን ቆርጦ የተነሳበትን ዓላማ ዮሃንስም መገንዘብ ያለበትን ነገር ተናገረ፡፡ “እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው።”

መጀመሪያ ከራሱ አንጻር አይቶ ማጥመቁን እምቢ ያለው ዮሃንስ በኃላ ግን የኢየሱስ የጽድቅ ማንገሥ ዓላማን በማየት ታዘዘውና አጠመቀው፡፡

ብዙ ጊዜ፣ የጌታን ዓላማ ባለመረዳት ነገሮችን ከራሳችን አንጻር ብቻ በማየት ከጌታ ጋር የምንከራከርበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ የቆዬ ልምምድ ነው።

ለምሳሌ ዮሃንስ 13፡7 ስናነብ ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር በእግር ማጠብ ጉዳይ ላይ ሲከራከር እንመለከታለን፡፡ “ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው።”

ዛሬ እኛ በምን ጉዳይ ይሆን ከጌታ ጋር የምንከራከረው?

ሲታይ ክርክራችን ጌታን የማስከበር ፊላጎት ይመስላል፡፡ ምናልባት የምናደርገውም በቅንነት ነው፡፡ ጌታ ግን ለሚበልጥ ዓላማ እና ለሚሻል ውጤት ራሱን ዝቅ አድርጎ እንድንተባበረው እየጠየቀን ይሆናል፡፡ ፈቃዱ እንዲሆን እንፍቀድለት?

ዮሃንስ ፈቀደለት፡፡ ጴጥሮስም በብዙ ክርክርም ቢሆን ፈቀደለት፡፡ ዮሃንስ መፍቀዱን ተከትሎ ትልልቅ ነገሮች ሆነዋል።

ኢየሱስ ተጠመቀ፡፡ ያንን ተከተትሎ ሰማይ ተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ መልክ በእርሱ ላይ ወረደና በእርሱም ላይ ተቀመጠ፡፡ በተጨማሪም መለኮታዊ ድምጽ በዚያ ስፍራ ተሰማ፡፡

ስለእየሱስ አስፈላጊ የሆነ መለኮታዊ ምስክርነት በስፍራው ተሰማ፡፡ ይህ ምስክርንትም ሆነ ክስተት ለዮሃንስ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጠቀመን። ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ትህትና፣ ስለ መቀባበል፣ ወዘተ እየተማርንበት ነው።

ስለዚህ እኛም ዛሬ ለጌታ በመፍቀዳችን በእኛ የሚገለጥ መለኮታዊ ክብር አለ፡፡ ውጤቱ ደግሞ ከእኛ የሚያልፍ ተጽዕኖ ልኖረው ይችላል። ትውልድ ይጠቀምበታል።

ስለዚህ ጽድቅን የማንገስ ዓላማ ከኢየሱስ. እንውሰድ፣ መታዘዝንም ከዮሃንስ እንማር።

ጌታ ይርዳን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ።

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *