SermonsTeachingsUncategorized

Kalu Yadinal

ማቴ 1፡18-25 ሥጋ የሆነው ቃል ያድናል፡፡

የዛሬው የወንጌል ክፍል ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዴት የሚነግረን ይሆናል፡፡ በየአመቱ የምናከብረው የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስ ልዴት በዓል፣ በተረት ተረት ላይ የተመሠረተ የውሸት ታሪክ ሳይሆን፣ በእርግጥ በገሃዱ ዓለማችን የሆነ፣ የተመዘገቤ እና ከእያንዳንዳችን ጋር የተገናኜ እውነት ነው፡፡

ሰይጣን በክፋት ሰዎች ደግሞ ሳያስተውሉት ይህንን ታሪክ እውነተኛነቱን መካድም ስለማይችሉ፣ በእውነተኛ ታሪክ ላይ እንዳንድ ተቀጽላ ነገሮችን እያመጡ የሰዎችን ትኩረት ከኢየሱስና ኢየሱስ ከመጣበት ዓላማ ወደ ተለያዩ የፈጠራ ትርክቶች በመመለስ ከራስ ሕይወት ጋር እንዳይዛመድ የማድረግ ሥራን እየሠሩ ነው፡፡

ይህንን የምልበት ምክንያት ደግሞ፣ ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው እኔን እና እናንቴን ብሎም የሰውን ዘር በሙሉ ከእግዚአብሄር ጋር ለማስታረቅ ነው፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚው እርሱ “ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ያ ማለት፣ ጌታችን ተወልዶ ኢየሱስ ተብሎ ከመጠራቱ በፊትም በእግዚአብሄር ዘንድ ነበረ፣ እግዚአብሄርም ነበረ (ዮሃንስ 1፡1-3)፡፡

በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።

ይህ ዮሃንስ “ቃል” ብሎ የሚጠራው አምላክ፣ በስጋ ሆነው የጠፉትን የሰዎችን ልጆች ለመፈለግ እነርሱን (እኛን ማለት ነው) ሆኖ መጣ፡፡ ለዚህ ነው በዮሃንስ ወንጌል ውስጥ“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” የሚለውን የምናነበው፡፡

እንግዲህ በዛሬው የወንጌል ክፍል ውስጥ ቃል ሥጋ የሆነበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ዮሴፍ የሚባል ከዳዊት የዘር ግንድ የሆነ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ማሪያም የምትባል ልጃገረድን ለማግባት ፈልጎ አጫት፡፡ በእጮኝነት እያሉ ዮሴፍና ማሪያም የግብረ-ሥጋ ግንኙነት አላደረጉም፡፡ ዮሴፍ፣ በመጽሃፉ እንደተጻፋ፣ ጻድቅና እግዚአብሄርን የሚፈራ ሰው፣ እጮኛውንም ማሪያምን የሚወድ ሰው ነበረ፡፡ ሆኖም ግን ከእለታት አንድ ቀን ያልጠበቀው ነገር በመሆኑ በጣም ከሚወዳት እጮኛው ለመለየት ስወስን እንመለከታለን፡፡ ምክንያቱም ማሪያም አርግዛ ተገኘች፡፡ ዮሴፍም፣ ተገናኝተው ስለማያውቁ፣ ያረገዘችሁ ከእርሱ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት ያውቅ ነበረ፡፡ ስለዚህ ማሪያም ለሌላ ሰው አርግዛ ይሆናል በሚል ጥርጣሬ፣ በጣም የሚወዳትን እጮኛውን ማሪያምን ሊተዋት አሰበ፡፡

በወቅቱ የነበረው ሁኔታ፣ ማሪያምን በድንጋይ የሚያስወግር ነበረ፡፡ በተለይ ዮሴፍ፣ በሆነው ነገር ከስሶ ማሪያምን ማስገደል ይችል ነበረ፡፡ ሆኖም ግን “ጻድቅ” ስለነበረ፣ ያለ እርሱ እርግጥ የተገኘችውን የእጮኛውን ሞት ፈጽሞ ማየት አልፈለገም፡፡ ይህ የሚያመለክተው፣ ዮሴፍ የእግዚአብሄርን ሃሳብ ወይም ፈቃድ በልቡ አኑሮት ይለማመድ ነበረ ማለት ነው፡፡ “በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” (ሕዝቅኤል 18፡23)፡፡ ምን ማለት ነው? እግዚአብሄር “እኔ የሃጢአተኛን ሞት አልሻም” እያለ ነው፡፡

ይህ ጻድቁ ወጣት፣ እያዘኔና እየተጎዳ፣ ነገር ግን ስለራሱ ብሎ ይህችን እጮኛውን ማስገደል ስላልፈለገ፣ በምስጥር ሊተዋት አሰበ፡፡

ይህ ማለት፣ ዮሴፍ ከሓጢአት ጋር ይተባበራል ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን “ፈራጅ” አድርጎ ራሱን በመቁጠር፣ በሌላ ሰው ነፍስ ላይ መበየን ስላልፈለገ ነው፡፡ በሓጢአተኛ ላይ የሚፈርድ እግዚአብሄር ነው፡፡ እርሱ ግን ነገሩን ለእግዚአብሄር ብቻ አስረክቦ ለመተው ወሰነ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በቃሉ “በቀል የእኔ ነው፣ ብድራትንም የሚመልስ እኔ ነኝ” ብሎአልና። ዮሴፍም ቃሉን እየኖረው እና በተግባር እያሳየ ያለ ሰው ይመስለኛል፡፡ በቅድስናው፣ በፍቅሩ፣ በእምነቱ ፣እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲሁም በርህራሄው ሊመሰከርለት ይችላል።

ዮሴፍ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር እግዚአብሄር ራሱ ጣልቃ ገብቶ፣ ለታዘዘችው ማሪያምና ለታመነው ዮሴፍ የቅን ፍርድ የሠጠው፡፡እግዚአብሄር አያይም አትበሉ፡፡ እግዚአብሄር ያያል፣ ይፈርዳልም፡፡ እግዚአብሄር የታመኑትን ሰዎች በግልጽ ለመታደግ፣ እውነታቸውንም ለማውጣት ይመጣል፡፡ እንዲሁም ደግሞ እግዚአብሄር፣ ነገሮቻቸውን ለእርሱ ላስረከቡት ሰዎች ደርሶ፣ በቀና መንገድ ይመራቸዋል፡፡

በቁ. 20 ላይ የምንገነዘበው ይህንኑን ነውና እግዚአብሄር ዮሴፍን ሲናገረው፣ ሲመራውና ማድረግ ያለበትን ሲያሳየው እንመለከታለንና፡፡መዝሙር 34፡14-18 ስናነብ እንዲህ ይላል“ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም። የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።

ይህ የእግዚአብሄር ጣልቃ ገብነት፣ ሁለቱንም ወገን ከከፋ ጉዳት አዳናቸው፡፡ ማርያምም ያልጠበቀችሁ ነገር በእግዚብሄር ፈቃድና ጸጋ ሆኖባታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲታልፍ፣ የሚደግፋት፣ ከጎንዋ ቆሞ የሚረዳት ሰው ያስፈልጋታል፡፡ በዚያ ላይ የወደ ፊት የትዳር ጓደኛዋን ማጣት በጣም ልብን ሰባሪ ክስተት እንደሆነ መገመት እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ግን “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።

በሌላ አንጻር ዮሴፍም ፍቅሩ፣ የወደፊት እቅዱና ስነ-ልቦናው የተጎዳ ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሄር የእርሱንም ጩሄት ሰማ፡፡ “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።”

ስለዚህ እግዚአብሄር በሕልሙ ታይቶት፣ “ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” አለው፡፡

እግዚአብሄርን ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ማሪያምን መጠቀም ፈለገ እንጂ የማሪያምንና የዮሴፍን የወደፊት ትዳር የመጉዳት ዓላማ አልነበረውም፡፡ ማሪያም በልዩ ሁኔታ ለልዩ ተልዕኮ ተመረጠች።

“ጻድቁ” ዮሴፍም በዚህ እግዚአብሄር ማሪያምን ለመረጠበት አገልግሎት ደጋፊ ሆኖ እንዲያገለግል በእግዚአብሄር ተመርጦአል፡፡

ዮሴፍ ለእጮኛው ለማሪያም ነፍስ ሃላፊነት ስለተሰማው፣ አሁን ደግሞ ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ከሰማይ መጥቶ ሥጋ በሆው ቃል ሕይወት ላይ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ “በጥቅት የታመነ በብዙ ይሾማል” ይላልና ቃሉ፡፡

እግዚአብሄር ለዮሴፍ ታላላቅ ሃላፊነቶችን ሰጠው፡፡ 1ኛ ማሪያምን እንዲወስድ፡፡ 2ኛ ከማሪያም ለሚወለደው ልጅም በሃላፊነት ለተልዕኮው የሚገባውን ስም እንዲሠጠው አዘዘው፡፡ ይህ ማለት፣ ማሪያም ሊትወልድ ያለውን ልጅ በሌላ በፈለገው ስም መጥራት አይችልም ማለት ነው፡፡ ምናልባት እግዚአብሄር ጣልቃ ገብቶ ለዮሴፍ ይህንን ሃላፊነት ባይሰጥ፣ ኢየሱስ ምን ተብሎ ይጠራ ኖሮአል? በሀገራችን በስም አሠጣጥ ባህል ምናልባት “የሴት ልጅ”፣ አፍራሽ፣ ድንጋታ፣ አሳምኖት፣ አስጨናቂ፣ ወይም ሌሎችም በዚህ ላይ ከመናገር የተቆጠብኳቸው ሥሞች ሊሰጡት ይችሉ ነበረ፡፡ እነዚህ ስሞች ደግሞ ለዓላማው ጋር የማይሄዱ ናቸው፡፡

ስለዚህ እግዚአብሄር፣ “ለጻድቁ” ዮሴፍ የራዕይ አግባብነት ያለውን ስም ለልጁ እንዲያወጣለት ተናገረው፡፡ “ኢየሱስ” ወይም “አዳኝ” “ፈይሳ” ተብሎ እንዲጠራ፡፡ በመገለጡ መሠረት፣ ይህ ስም “ሥጋ ለሆነው ቃል” የተሰጠው፣ እርሱ “ሕዝቡን ሁሉ ከኃጢአታቸው ስለሚያድናቸው” ነው፡፡

ኢየሱስ ያድናል፡፡ በበደልና በሓጢአት ምክንያት ከእግዚአብሄር የተለየውን ሕዝብ፣ ኋጢአት በሽተኛ፣ ክፉ መንፈስ ሰለባ፣ የሞት ደንበኛ ያደረገውን ሕዝብ ለመታደግ ነበር የመጣው፡፡ ዮሴፍ ይህንን የሚገልጽ ስም ለልጁ መስጠት ነበረበት፡፡

ሌላው እግዚአብሄር ለዮሴፍ ያደረገው ነገር ቢኖር፣ የተናገረው ነገር እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥለት ዘንድ ከተጻፈው የትንቢት ቃል ጋር አገኛኘለት፡፡ ዮሴፍ ከሕልሙ ሲነቃ፣ ያየውን ሕልም ቅዤት አለመሆኑን የሚያውቅበት መንገድ ቢኖር ከተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል ጋር መስማማቱን በማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ ስለሚወለደው ልጅ የጻፈውን ትንቢት አስታወሰው፡፡ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል” (ቁ.23)፡፡

አንዱ የጻድቅ ሰው መገለጫው ለእግዚአብሄር ቃል መታዘዙ ነው፡፡ “ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።”፡፡

ተመልከቱ፣ ዮሴፍ፣ እግዚአብሄርን ለመታዘዝ፣ በአይምሮ ለማሰብና ለማገናዘብ የሚያስቸግረውን ነገር ተቀበለ፡፡ ይህ አንዴት ሊሆን እንደሚችል ባይገባውም፣ የተቀበለው መልእክት ምንጭ እግዚአብሄር መሆንን ስላወቀ፣ አፋጣኝ የሆነ እርምጃ ሲወስድ እናያለን፡፡ ማሪያምን ወሰዳት፡፡ ይህ ደግሞ ማሪያም ለብቻዋ እያለች ማርገዟን ሰዎች አይተው በድንጋይ እንዳይወግሩአት ይረዳታል፡፡ በእርግጥ፣ ባለራይም ሰውን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በውስጡ መልካም ነገር፣ ብዙ ጻጋ ያደረገውም ሰው፣ ሌሎች ሰዎች ከጎኑ ሆነው እንዲደግፉት፣ እንዲመሰክሩለት፣ እንዲያበረታቱት ያስፈልጉታል፡፡ ለዚህ ይመስለኛል እግዚአብሄር ዮሴፍን ለማሪያም የሰጣት፡፡ ብቸኛም እንዳትሆን ያደረጋት፡፡

በእርግጥ፣ እግዚአብሄር ቅዱስ ጋብቻን ወይም ትዳርን ያከብራልም፡፡ ትዳር እንዲፈርስ አይፈልግም፡፡ ፍቅር እንዲቀጥል እንጂ እንዲጠፋ የእርሱ ፈቃድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ስለእነዮሴፍ የወደፊት ትዳርም ተጠነቀቀላቸው ማለት እንችላለን፡፡ እርሱን የሚፈልጉ ከመልካም ነገር ሁሉ አይጎድሉም ተብሎ እንደ ተጻፈው፡፡

ሆኖም ግን ቅዱስ ቃሉ ስለዮሴፍ ግልጽ አድርጎ የሚነግረን “የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም”፡፡ ይህ ማለት የግብረ-ሥጋ ግንኙነት አላደረጉም ማለቱ ነው፡፡ ይህ በራሱ በተዋደዱትና አሁን ደግሞ በመልአኩ ትዕዛዝ መሠረት በትዳር ለተሳሰሩት የትዳር አጋሮች መካከል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ግን የእግዚአብሄር ጸጋ ደግሞ ያስችላል እንጂ፡፡ ዮሴፍና ማሪያምም ምን ያህል ለተቀበሉት ሃላፊነት ጥንቁቃን እንደነበሩና አክብሮትንም እንደሰጡ ያሳየናል፡፡ ጌታን በሁለንተናቸው አከበሩት፡፡እንግዲህ ጊዜው ደርሶ ማሪያም የጸነሰችው ቃል፣ ስጋ ሆኖ ሲወለድ፣ ዮሴፍ ደግሞ በታዘዘው መሠረት “ኢየሱስ” ብሎ ስም አወጣለት፡፡

ዛሬ ይህ ሰዎችን ሁሉ ለማዳን የተገለጠውን ኢየሱስን የልዴት በዓል ስናከብር ከግል ሕይወታችን ጋር እያያዝን፣ ለእርሱ የሚገባውን አክብሮት እንድንሰጥ እግዚአብሄር ይርዳን፡፡

በመብል፣ በመጠጥ፣ በተለያዩ ተረት ተረቶችና ማስገጦች ውስጥ ተዘፍቀን፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ እኛን ለመፈለግ መምጣቱንና የደንነታችን ዋስትና መሆኑን እንዳንረሳ መጠንቀቅ አለብን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *