SermonsTeachings

ስማችሁ በሰማያት

ሉቃስ 10፡17-20
17 ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፦ ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። 18 እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። 19 እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። 20 ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማ ችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።

አሁን ባለንበት ዘመን ስለመረጃ ጥርቅም ማውራት ውስብስብ ሆኖ የሚታይ ነገር አይደለም፡፡ በሄድንበት ሁሉ መረጃዎቻችን በኮምፕውተር ውስጥ ተጠራቅመው ስላሉ፣ የምንፈልገውን አገልግሎት ከማግኘታችን በፊት፣ ወይ መመዝገብ ወይ ደግሞ ስማችን በተጠራቀመው ውስጥ መገኘቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ የያዝናቸው የአባልነት መታወቂያዎች፣ ፓስፖርቶቻችን፣ የባንክ ደብተራችን/ካርዳችን እንድሁም ለሕክምና አገልግሎት አካውቶቻችን፣ ወዘተ. ከተጠራቀመ መረጃ ጋር ተያያዥነት አላቸው፡፡

ዛሬ ባነበብነው ክፍል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ገና ኮምፕውተር ከመፈጠሩ በፊት)፣ “ስማችሁ በሰማይ መዝገብ ስለተጻፈላችሁ ደስ ይበላችሁ” ይላል፡፡ ያ ማለት ደግሞ ወደ ሰማያዊ ዴታቤዝ/መረጃ ጥርቅም ተካታችኋል ማለቱ ብቻ አይደለም፡፡ ግን ከሰማይ ሓሳብ ጋር ተስማምታችሁ፣ የሰማዩን አምላክ ፈቃድ ስላደረጋችሁ፣ በእምነት መታዘዛችሁና የተጠየቃችሁትን መፈጸማችሁ በሰማይ እውቅና አግኝቶላችሁኃል ማለትም እንጂ፡፡ እስቲ ታሪኩን ለመረዳት እሞክር፡፡

ኢየሱስ ተከታዮቹን (ሰባ የሚደርሱ ሰዎችን) ሁለት ሁለት አድርጎ የምስራችን እንዲሰብኩና ሰዎችን እንዲረዱ ላካቸው፡፡ ሲሄዱም ለመፈወስ፣ አጋንንትን ለማስወጣት፣ የእግዚአብሄር መንግስት ወደ እነርሱ እንደቀረበች ለሰዎች ለማስታወቅም ሃላፊነት ተሰጥቶአቸው ነበረ፡፡ ዴቀ መዛሙቱም ታዝዘው ከሄዱ በኃላ እያንዳንዱን ተግባር አድርገው ተመለሱ፡፡ ከእነዚህ ስራዎች ውስጥ የአንዳንዶቹን ወዲያው ፍሬያቸውን ማየት ቀላል አልነበረም፡፡ አንድ ነገር ግን በጣም ግልጽ ሆኖ አዩት። እርሱም እነርሱ እያዩ በእጃቸውም ውስጥ ሰዎች ከአጋንንት ነጻ ሲወጡ ማየት ነው፡፡ ይህም በጣም አስደነቃቸው ደግሞም አስደሰታቸው፡፡ ምናልባት ከዚያን በፊት አጋንንትን “እናስወጣለን” የሚሉ ሰዎች የሚያደርጉአቸው ነገሮች ወስብስብ ስለነበረ፣ ወይም ደግሞ ሰው በመናፍስት ላይ ስልጣን እንደለሌው አስቦም ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን ህልም ሳይሆን ያለምንም ማወሳሰብ፣ ያለምንም ዝግጅታዊ ስነ-ሥርዓት፣ የጌታ የኢየሱስን ስም ሲጠሩ አጋንንት መውጣታቸው አስደሳች ተዓምር ሆኖባቸዋል፡፡ ስለዚህ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት፡፡

በዚህ ምድር ላይ ስንኖር፣ ብዙዎቹ ስኬቶታችን እኛ ወይም ሌሎች ሰዎች በሚያዩት፣ በሚሰሙት፣ ወይም ከሚያደርጉትም ነገሮች ጋር ተያያዥነት ባይኖራቸዋል። ስለሆነም ሲሆኑልን ደስ ይለናል፣ ሳይሆኑልን ሲቀሩ ደግሞ ያሳዝኑናል፡፡

የመንፈሳዊው አለም ግን ይለያል። ዴቀ መዛሙርቱ በተሠጣቸው ተልዕኮ መሠረት ታዝዘው ተግባራቸውን ሲፈጽሙ፣ የሚታየው ለውጥ ለእነርሱ ብቻ ምስጋና የሚያሰጥ አልነበረም፡፡ ሌሎች ምክንያቶችም አሉና፡፡ በመጀመሪያ የሥራው ባለበት እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡ በመቀጠል ለሰሙት ቃል ታዝዘው መልዕክቱን የሚቀበሉ ሰዎች ስለራሳቸው መዳን ሙሉ ሃላፍነት አላቸው፡፡ አጋንንትም ቢሆን የሚወጣው የጌታ ስም ካለው የሥልጣን ጉልበት ነው፡፡

ስለዚህ ኢየሱስ ደቄ መዛሙርቱ ስለተረጉ ነገሮች መደሰታቸውን አይቶ፣ በኋላ ደግሞ ወደ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የዘላቂ ደስታቸው አቅጣጫና ምንጭ ምን መሆን እንዳለበት አሳያቸው፡፡ ደስታቸው መናፊስት ስለተገዙላቸው ወይም ስለታዘዙአቸው ብቻ ከሆነ፣ አንድ ቀን መናፊስት ከመታዘዝ እምቢ የሚልበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል (ጾምና ጸሎትም ካልተጨመረ የሚያስቸግርበት ጊዜ አለና)፡፡

የሀገሩ ሰዎችም ስብከታቸውን ከመቀበል ይልቅ ሊያሳድዱአቸው የሚነሱበት ጊዜም ሩቅ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ስማቸው በሰማይ ተጽፎላቸዋልና ዘላለማቸው ዋስትና አለው፡፡

ይህም ከማንኛውም ስኬታቸው ይልቅ ሊያስደስታቸው ይገባል፡፡
ይህንን እውነት መረዳት ዛሬም ለእኛ ለአማኞች እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በርግጥ አሁን በዙሪያችን ያሉ ነገሮችና ሁኔታዎች ስሜቶታችን ላይ የተለያዩ ተጽኖዎችን ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ ስሜቶቻችን በየጊዜው የሚከሰቱ የሁኔታ መለዋወጦችን ተከትለው ይለዋወጣሉ፡፡ የጠራን፣ የሰማነውና የታዘዝነው እግዚአብሄር ግን ከቶም አይለዋወጥም፡፡
ስለዚህ እግዚአብሄርና ከኢየሱስ የተነሳ በእርሱ ዘንድ ያገኘነው ተቀባይነት የደስታችንና የሰላማችን ምክንያት ልናደርገው ይገባናል፡፡ እንዲህ ስናደርግ ዘላለማችን ሊቃወስ የማይችል፣ አስተማማኝ በሆነው በእግዚአብሄር እጅ እንዳሌ ስለምናውቅ በነፋስ ተገፍተን አንወድቅም፡፡ ነገሮች ስሆኑም ሳይሆኑ ሲቀሩም አምላካችን ግን በሰማይ እንዳሌ ከተረዳን ከዓላማችን ፍንክች ማለት አይኖርም፡፡ ሰድራቅ፣ ምሳቅና አብድናጎ በተዘጋጀላቸው ሰባት እጥፍ እሳት ፊትለፊት ቆመው፣ “አምላካችን ያድነናል፣ ባያድነንም እንኳ አንቴ ላቆምከው ምስል አንሰግድም” ያሉት ይህ ስለገባቸው ነው፡፡

ሌላው ኢየሱስ በዛሬው ክፍላችን ውስጥ የተናገረው ሰይጣን ከሰማይ ስለ መውደቁ ነው፡፡ ሰይጣንን የጣለው እግዚአብሄር ራሱ እና በስልጣን የሚሰበከው የቃሉ ጉልበት እንጂ አገልጋዮቹ አይደሉም፡፡ ሰይጣን ወደቀ፤ ሥራውም ፈረሴ። ከዚህ የተነሳ ሠይጣን በአማኞች ላይ አንዳች ስልጣን ሊኖረው አይችልምና ተከታዮቹ በርትተው ሥራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው መከራቸው፡፡
ሠይጣን ስለወደቀ፣ ሥራውም ፈርሶበታል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ከክፋት ሥራ ተላቀው ከሚሰሙት የእግዚአብሄር ቃል የተነሳ ወደ እግዚብሄር መንግስት ይመጣሉ፡፡
እናንቴ ደግሞ “ስማችሁ በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
ጌታ ይባርካችሁ
በተክሉ የቀረበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *