Sermons

የእምነት ቃል

ወንጌላችን እንግዲህ ይህ ነው፡፡ በኢየሱስ አምኖ ስለመዳን፣ በትንሳኤው ጉልበት አምኖም ስለመጽደቅ፡፡ ዛሬ እኛም “ የምንሰብከው የእምነት ቃል ” ይህ ነው፡፡

ሮሜ 10፡1-11 ( የምንሰብከው የእምነት ቃል )

በዚህ ክፍል ውስጥ ሃዋሪያው ጳውሎስ፣ ስለአይውድ ወንድሞቹ መዳን ያለውን ሸክምና ፀሎት መሠረት አድርጎ መዳንና ጽድቅ የሚገኙበትን መንገዶች ያብራራል፡፡ ክፍሉንም ሳነብ አንድ ነገር ታወሰኝ፡፡ ሥራ ቀላል መንገድ እያለ፣ ለአድካሚ፣ ጊዜንና ጉልበቱን ጨራሽ መንገድን ስለሚመርጡ ሰዎች፡፡

ከአመታት በፊት በአድስ አበባ (ፊንፊኔ)፣ ማህበረሰባዊ አገልግሎትን ለማግኘት ፈልጌ ቀኑን ሙሉ ተሰልፌ ቀኑ ሲያልቅ ገና ተራዬ ስላልደረሴ፣ “በቃ ነጌ ኑ” የተባልንባቸውን አጋጣሚዎች አስታወስኩ፡፡ አንዳንዴ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ የመብራት ወይም ውሃ ቢል ለመክፈል በመብራት ሃይል ወይም ደግሞ ውሃ ገቢ መሰብሰቢያ ግቢ ተሰልፈን፣ ጊቢው አንሶን መንገድ ላይ በሁለትና በሶስት ረድፍ ተሰልፈን ጸሐይና ዝናብ መትቶን ወይ መብራት ጠፋ ወይ የሆነ ነገር ሆኖአልና ነጌ ኑ የሚባልበት አጋጣሚዎችን አስታወስኩ፡፡ ታዲያ በዚያን ጊዜ፣ አሁን በብዙ ቦታና ሃገሮች እንዳለው ባለንበት ሆነን በካርድ መክፈል ቢቻል ኖሮ ምን ያክል የዚያን ሁሉ ሰው ድካምና የግዜ መባከን ማስቀረት ይቻል እንደነበር አስብኩ፡፡

ሓዋሪያው ጳውሎስ ሕግን ጠብቆ መዳንና በወንጌል ቃል አምኖ መዳንን እያነጻጸረ፣ በዚህ ክፍል ያሳያል፡፡

ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በስኮትላነድ ውስጥ ባለንበት ከተማ፣ የውሃና የመብራትን ክፊያ ካሽ ይዤ መብራት ሃይል ሄጄ በእጅ ለመክፈል እፈልጋለሁ የሚል ሰው ከተገኘ ብዙ ደክሞ ግን ሳይሳካለት ይመለሳል፡፡ ምክኒያቱም “ሂድና ኦንላይን ክፈል” ወይም “በካርድ ክፈል” ወይም ደግሞ የመብራቱን ካርድ ወደሚቀርብ አገልግሎት ሸጪ ሱቆች ሂድ ስለሚባል፡፡ ቢሆንም ከተለያዩ ሁኔታዎች የተነሳ ዛሬም አድካሚውን መንገድ የሚመርጡ ሰዎች አሉ፡፡

ሓዋሪያው ጳውሎስ፣ ሰው የህግን ሥራ ፈጽሞ መዳን ከፈለገ ሕግን በሙሉ መፈጸም ይኖርበታል እንጂ ይችላል ይላል፡፡ “ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና“ (ቁ 5) ይላል፡፡ ሆኖም ግን ችግሩ ማን ነው ህግን በሙሉ በራሱ ፈጽሞ በእግዚአብሄር ፊት ራሱን ማጽደቅ የሚችለው?

በሰው ፊት ጻድቅ መስሎ መታየት ይቻላል፡፡ በራስም ምዛን ራስን ጻድቅ አድርጎ ማቅረብ ይቻል ይሆናል፡፡ ግን በእግዚአብሄር ፊት ለመቆም የሚያበቃ በራስ ሥራ የሆነ ጽድቅ ይዞ መሄድ የሚችል ማን ነው?

እንደ ሓዋሪያው አገላለጽ፣ በዘመኑ የነበሩት እስራኤላዊያን “የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም” (ቁ.3) ። ያ ማለት ምን ማለት ነው? ሰዎች ይጸድቁበትና ይድኑበት ዘንድ የተላከላቸውን ኢየሱስን ማመን ትተው፣ በሙሴ ህግ ላይ ሙጭጭ ብለው በመቆም፣ እጅግ እየደከሙ ግን ደግሞ ሳይጸድቁ ይኖራሉ፡፡

በዘመናችም ይህ በግልጽ ይታያል፡፡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን አምኖ በእርሱ ከመጽደቅ ይልቅ፣ “እኔ ክፉ ነገር አላደረግሁ፣ ሰው አልበድልም፣ አልሰርቅም፣ አላመነዝርም፣ እጾማለሁ፣ ለደሃ እሰጣለሁ፣ ወዘተ. እያሉ የራሳቸውን ጽድቅ ይደረድራሉ፡፡ መጽሓፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ብሎ በግልጽ ያስቀምጣል

ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።” (1 ዮሃ 1፡8-13)

ስለዚህ ሁለቱ ዓይነት የጽድቅ መንገድ የየራሳቸው አካሄድና መርሆ እንዳላቸው ሐዋሪያው ያብራራል፡፡

አንደኛው “ከሕግ የሆነ ጽድቅ” ነው፡፡ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት ይኖራል፡፡ በማድረግ ብቻ፡፡

ሁለተኛው “ከእምነት የሆነ ጽድቅ” ነው፡፡ “በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል” ይላልና (ቁ 8)፡፡

ከላይ በተናገርኩት ምሳሌ ውስጥ ልክ የካርድ ክፍያው አይነት ነው ፤ ጥቂት በተኖችን በመንካት ብዙውንና አድካሚውን ሥራ ማስቀረት ነው፡፡

በጳውሎስ ገለጻ ውስጥ ደግሞ በአፍ መመስከር እና በልብ ማመን ሥራውን ሁሉ ይጨርሳል፡፡ “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና።” (ቁ9-11)፡፡ በተጨማሪም ሮሜ 5፡1-2 ማንባብ ይቻላል፡፡ “ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው፡፡”

በእርግጥ፣ ኢየሱስ ጌታ ነው ብሎ መናገር በራሱ ቀላል አልነበረም፡፡ በአፍ ብቻ (እምነትና የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሳይሆኖር) የሚነበነብ መፈክርም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም፣ ጳውሎስ በሚያገለግልበት በዚያን ዘመን ጌታ ተደርጎ (የሁሉ ባለቤት) ተደርጎ የሚሠገድለት ሀገረ ገዢውና እርሱን የሾመው የሮማ መንግስት ነበረ፡፡ የሌላ የማንንም ጌትነት መናገር የሚፈልግ፣ በፖለትካ ግጭትና በእምጳየሩ ክህደት ወንጀል ይጠየቃል ማለት ነው፡፡

ከዚህም የተነሳ ብዙዎች የኢየሱስን ጌትነት በቃልና በኑሮ ስለመሰከሩ፣ በመጋዝ ተሠንጥቀውበታል፣ በፈላ ዘይት ውስጥ ተጠብሰውበታል፣ በእሳት ተቃጥለሁበታል፣ ከአውሬ ጋር ተላፍተውበታል፣ በብዙ ዓይነት ስዴትና መከራ ውስጥም አልፈውበታል፡፡ ስለዚህ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብሎ መናገር እንደ ዘመናችን ቀላልና ሳያስቡበትና የራስን ዋጋም ሳይተምኑ የሚታወጅ ወይም የሚመሰከር ነገር አልነበረም፡፡ በእርግጥም ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡

የኢየሱስ ጌታ መሆንን ለመመስከር ከሞት መነሳቱንም ጨምሮ ማመን ይጠይቃል፡፡ ትንሳኤውን አምኖ መመስከርም እንደዚሁ በአይውድም ዘንድ ሳይቀር እንደ ወንጀል የሚታይ ነበረ፡፡ ለዚህ ነው እነ ጴጥሮስ በሸንጎው ፊት ሲቀርቡ “በዚህ ስም ሁለተኛ እንዳትናገሩ” ተብለው ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ፡፡ ይህንን ቢይን ለማስተላለፍ “አለቆቻቸውና ሽማግሌዎች ጻፎችም ሊቀ ካህናቱ ሐናም ቀያፋም ዮሐንስም እስክንድሮስም የሊቀ ካህናቱም ዘመዶች የነበሩት ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ” ፡፡

ጴጥሮስንና ዮሐንስን “ ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።”

ይህ ነው እንግዲህ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍ መመስከር ማለት፡፡ “ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው፡፡”

እኛም ዛሬ፣ ባለንበት በማናቸውም ሁኔታ፣ በሕይወታችን በተገቢው አኳን ስለኢየሱስ ጌትነት እንዳንመሰክር የሚገዳደሩን ሁኔታዎችን አሠራሮች (ሥርዓቶች) ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለኢየሱስ ጌትነት ከመናገር ይልቅ አመቻምቼን አንዲናልፍ በኑሮ፣ በሥራ፣ በገንዘብ፣ በዝምድና፣ በጉርብትና፣ በጓደኝነት፣ በትዳር፣ ወዘተ. ሊያስፈራሩን የሚሞክሩ ብዙ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለትህን ካልተውከው በዚህ መሥራት አትችልም፣ ወይም ጓደኛችን መሆን አትችልም፣ ወይም ዝምድናህን አንፈልገውም፣ ወይም ኑሮህ ችግር ውስጥ ይወድቃል፣ ወዘተ በማለት ሊያስፈራቱ የሚዝቱ ብዙ ናቸው፡፡

በዚህ ሁኔታ ወስጥ ነው “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር” ትድናለህ የሚለው አውነት ግልጽ የሚሆነው፡፡ ይህ ወደ ኢየሱስ ትምህርት ይመልሰናል፡፡ በሰው ፊት ስለኢየሱስ ስለመመስከርና እርሱን ስለመካድ፡፡ ለዳነ ሰው ኢየሱስ በአባቱ ፊት ይመሰክርለታል ፡፡ በሰው ፊትም አልካደውምና እምነቱ እውነተኛ ስለሆነ ጌታም አያፍርበትም፡፡(ማቴ 10፡33)

ወንጌላችን እንግዲህ ይህ ነው፡፡ በኢየሱስ አምኖ ስለመዳን፣ በትንሳኤው ጉልበት አምኖም ስለመጽደቅ፡፡ ዛሬ እኛም “ የምንሰብከው የእምነት ቃል ” ይህ ነው፡፡

በኢየሱስ ትንሳኤው የማያምን ሰው ለራሱም የትንሳኤውን ሃይል ተስፋ ማድረግ ስለማይችል፣ ከዛሬ ሕይወት ያለፈ ተስፋ አይኖረውም (1ቆሮ 15፡16-19)፡፡ ለዚህም ዓለሙን መውደድና ዐላማዊ ሆኖ መኖርን ከዘላለማዊ ሕይወቱ ያስበልጣል ማለት ነው (ያዕ 4፡4)፡፡ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሄር ጋር በጠላትነት መኖር ስለሚሆን የሐጢአት ኑሮ ነው (ጽድቅ የለሌበትም ማለት ነው)፡፡

ያለእምነት የሚደረግ ሁሉ ሓጢአት እንደሆነም ተጽፎ አለና፡፡ በመጽሓፍ ቅዱስም በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ውስጥ ስንመለከት፣ በትንሳኤው ያመኑ ሰዎች ናቸው ሞትና ስዴት ሳይበግራቸው፣ እስከሕወታቸው ጫፍ ድረስ ለጌታ ክብርና ደስታ የኖሩት፡፡ ይህ ደግሞ ለአማኞች ሁሉ በተሠጠውና የሚጸልዩ ሰዎች ሊቀበሉት በሚችሉት በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የሆነ ነው (1ቆሮ 12፡3፣ ሉቃ 11፡13)፡፡ “ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው፡፡”

እኛም እስከ መጨረሻው ድረስ የኢየሱስን ጌትነት በመመስከርና በትንሳኤው ጉልበት በመተማመን እንድንኖር እግዚአብሄር በጸጋው ይርዳን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ

 

በተክሉ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *