EventsSermons

ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል

ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል Merry Chrismas, ECMYIS, mekane Yesus in Sctland

ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል

10 መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ 11 ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። 12 ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። 13 ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ 14 ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። (ሉቃ 2፡10-14)

ውድ የድረ ገጻችን ተከታዮች፣ እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልዴት በዓል አደረሳችሁ፡፡ በዓሉ የእግዚብሄርን ፍቅር፣ ሠላም፣ በጎነትና መልካምነት በግል ሕይወትዎ፣ በቤተሰብዎ፣ በአከባቢዎና በምድሪቱ ዙሪያ የሚያዩበትና የሚለማመዱበት እንዲሆንልዎት ምኞታችንና ጸሎታችን ነው፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ዓለም በመምጣቱ ብዙ ታሪኮች ተለውጦአል፣ ብዙ ጥያቄዎች መልስ አግኝተዋል፣ ብዙ እንቆቅልሾች ተፈተዋል፣ ብዙ በሽተኞችም ተፈውሰዋል፣ ብዙ ሙታኖችም ሕይወት አግኝተዋል፡፡ ይህ ብቻ ደግሞ አይደለም፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መምጣት ብዙ ጦሪነቶችን፣ ብዙ ሰልፎችን፣ ብዙ ስደቶችንም አስከትሎአል፡፡

ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው፣ ትልቅ የሕይወት ብርሃን በምድር ላይ በመብራቱ የብዙዎች ጨለማ ሲበራ፣ ብዙ የጨለማ ወዳጆችና በብርሃን ውስጥ መስራት የማይችሉቱ ደግሞ ላለመጋለጥ ብዙ ጦሪነቶችን በማወጃቸው ነው፡፡ አብዛኞቹ ጦሪነቶች የታወጁት በሰዎች አእምሮ ውስጥ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በገሃዱ አለም በግልጥ በታሪክ ተመዝግበው የሚገኙ ጦሪነቶች ናቸው፡፡

የእነዚህ ጦሪነቶች ትልቁ ዓላማ ወደ ዓለም ሊመጣ የነበረውን ብርሃን መከልከል፣ ጥሶ ከመጣ በሃላ ደግሞ መጥቶ የነበረውን ብርሃን ማጥፋት ነበረ፡፡ ብርሃኑ ግን እነርሱ ለማጥፋት በሞከሩት በብዙ እጥፍ እየተፈናጠረና እየተቀጣጠለ፣ ዓለሙን ሁሉ አዳሪሶአል፣ ከትውልድ ወደ ትውልድም ተሸጋግሮአል፡፡ የዓለም ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ዛሬም ይሰበካል፣ ዛሬም ያድናል፣ ዛሬም ይለውጣል፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡

እኛም ዛሬ የምናከብረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዴት ወደ የግል ጆሮዎቻችን ከመድረሱ በፊት ብዙ የእምነት አባቶችና እናቶች ብዙ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ በጌታ ጸጋና ረድኤትም መልእክቱን ለእኛ ማድረስ ችለዋል፡፡ ስለዚህ የብርሃኑ አሠራር በእኛም ውስጥ ተጽዕኖ ማምጣት ችሎአል፡፡ እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን፡፡

ማሪያም የጌታችንን መምጣት መልእክት በመቀበሏ፣ በሕይወቷ ተወራርዳለች፡፡ የሞት ጥላም በዙሪያዋ አጥላልቶ ነበረ፡፡ ውርደት፣ መተው፣ መጠላት፣ ድካም፣ ሥፍራ ማጣት ተራ በተራ ሞክሮአታል፡፡ ግን በእግዚአብሄር እርዳታ፣ በፈለገችውና በሚመቻት ቦታና ጊዜ ሳይሆን ቀድሞ በእግዚአብሄር በተወሰኔ ቦታና ጊዜ የዓለም ብርሃን የሆነውን ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደች፡፡ ኢየሱስ በቤትልሄም መወለድ ነበረበት፡፡ የማሪያም በዚያ አድካሚ ጊዜ ረጅም ጉዙ መጓዝ፣ ወደ ትክክለኛው ቦታ (በትንቢት ወደ ተነገረው) መሄጃ እንጂ የእግዚብሄር ቅጣት ደርሶባት አልነበረም፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡

ወገኖቼ፣ ምናልባት በእግዚብሄር ሓሳብ ውስጥ እያላሁ፣ የማትፈልጉትን ጉዞ እየተጓዛችሁ ይሁን? አይዞአችሁን፣ ወደ ትክክለኛው ቦታ መድረሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡

ዮሴፍም እንደአንድ ወንድ እንደአንድ አይውዳዊም፣ በሕይወቱ የሚጠየፈውና በሚያሳፍር በሚመስለው ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በእግዚአብሄር ጸጋና እርዳታ፣ ያንን ትልቅ ጉዞ ከማሪያም ጋር መጓዝና የእግዚአብሄርን ታላቅ ስራ ማየት ችሎአል፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡

ሀገረ ገዢው ሄሮድስ በሕጻናት ላይ ያሳወጀው የሞት አዋጅ፣ ወደ ዓለም መጥቶ የነበረውን ብርሃን ለማጥፋት ነበረ፡፡ ለምን? “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።” (ዮሃ 1፡9-10) ሄሮድስ አላወቀውም፡፡ የስልጣኑ ተሻሚ እንጂ የሕይወት ጌታ አድርጎ አልወሰደውም፡፡ ሠይጣን ግን ይህን አለማወቅና ራስ ወዳድንነት (ራስን የመከላከል ትግል) ተጠቅሞ ዓለሙን በሙሉ በጨለማ የማስቀረት ዓላማ ነበረው፡፡ ያልተሳካ ዓላማ፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡

ዛሬም ብሆን ብዙና ተመሳሳይ አለማወቆችና ራስ ወዳድነቶችን በመጠቀም ለእኛም ሆነ ለሌሎች የሚጠቅም ብርሃኖቻችን፣ ራእዎቻችንና፣ በረኮቶቻችን ለማጥፋት ጠላት ተግቶ ይሰራል፡፡ ግን “የተስፋን ቃል የሠጠው እግዚአብሄር የታመነ ነው” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እግዚአብሄር ራሱ ድል አድርጎ እኛን ደግሞ እንደ አሸናፊዎች ያስከደናል፡፡ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” ይለናል፡፡ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡

መልካም የጌታችን ኢየሱስ የልዴት በዓል ይሁንልዎት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *