SermonsUncategorized

ከጸጋው ቃል የተነሣ

ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ፦ ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር። ሉቃ 4፡22 “And all bare him witness, and wondered at the gracious words which proceeded out of his mouth. And they said, Is not this Joseph's son?” Luk 4:22 Glasgow city, Mekane Yesus congrigation, Scottish Ethiopians church, EECMY, ECMYIS, Mekane Yesus in Scotland, Mekane Yasus, Ethiopian Church in Glasgow, Scotland, Ethiopian Christina Community, Evangelical Church, Lutheran chuch in Glasgow, Scotland. we meet in St George's Tron Church, Church of Scotland, city center. Christian family, infant baptism is also practiced here. Eritrean Christian church from Lutheran chuch of Eritrea.

የወንጌል ክፍል ሉቃ 4፡22-30 (ከጸጋው ቃል የተነሣ)

ቁ. 22 “ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ፦ ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር።”

ከዚህ ቁጥር ወደ ኃላ ተመልሰን ቢናነብ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ሆኖ ከኢሳይያስ የትንቢት መጽሓፍ ስለ እርሱ የተፃፈውን እንዳነበበና በትንቢት የተነገረው ቃል በጆሮአቸው እንደ ተፈፀሜ መናገሩን እናነባለን፡፡ ባነበበው ቃል የተደነቁ ምዕመናን ትኩር ብለው እንደተመለከቱትም ጸሓፊው ሉቃስ በግልጽ ተሪኮአል፡፡ “ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ” ተደነቁ፡፡

ሰዎቹ ትኩር ብለው ከመመልከትም (ከመታዘብም) አልፈው መመስከር ጀምሮ ነበር፡፡ ምን ብለው እንደ መሰከሩ በትክክል ባላውቅም፣ ከተጻፈው አንፃር ሲታይ፣ ያነበበው ትንቢትና እርሱ እንደሚመሳሰሉ፣ የሚናገርበት ጥበብ፣ ከፈሪሳዊያንና ከጻሃፍት በተለዬ መልኩ እንደሚያስተምርና ንግግሩ መልካም እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ (ማቴ 13፡54፣ሉቃ 21፡15፣ ዮሃ 7፡46)“ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር”፡፡ “ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ” ተደንቀዋልና፡፡

ኢየሱስ ያነበበው ክፍል እና የሚናገረው ነገር ወደ ማንነቱ ዕውቀት የሚመራ ቢሆንም፣ ሲሰሙት የነበሩት ሰዎች ግን በእርሱ ማመን አልፈለጉም፡፡ የንግግሩን ተጽዕኖ በማንነቱ ላይ ባነሱት ጥያቄ ለማድበዝበዝ ሞከሩ፡፡ ከአእምሮአቸው ወሰንም ለመውጣት አልፈለጉም፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ ማንነት ሊበራላቸው ሲል ቶሎ ብለው ያንን እውነት በውስጣቸው የሚያደበዝዝና በማንነቱ እንዳይቀበሉት የሚያደርጉ ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን ማንሳት ቀጠሉ፡፡

ሉቃስ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ፣ ሰዎች “ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ” ጥያቄዎችን ይጠይቁ እንደነበር ይናገራል፡፡ በዚህ ላይ የኢየሱስ ተገንዝበን ማለፍ ያለብን አንድ ነገር፣ የኢየሱስ በጸጋ የሆነ ንግግር ትልቅ ተጽዕኖ አምጥቶአል፡፡

በዓለማችን የሚፈጠሩት ሕብረተሰባዊ ቀውሶችም ሆነ መነቃቃቶች በአብዛኛቸው ቢጠኑ፣ ከተጽኖ አምጪ ንግግሮች ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው እገምታለሁ፡፡ ተጽኖው በመልካምም በክፉም ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሄር መልካም ተጽእኖ አምጪዎች እንድንሆን ይፈልጋል፡፡

የመሪዎች ንግግር፣ የፓሌቲካ ተቀናቃኞች ንግግር፣ የተመራማሪዎች ንግግር፣ ወዘተ. በሕብረተሰብ መካከል ድጋፍን፣ ተቃውሞን፣ መከፋፈልን፣ መስማማትንም፣ ፍርሃትን፣ ተስፋን፣ ጦሪነትን፣ ሠላምንም ይቀሰቅሳሉ፡፡

መክበብ 12፡11 ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን “የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው፣ የተሰበሰቡትም ከአንድ እረኛ የተሰጡት ቃላት እንደ ተቸነከሩ ችንካሮች ናቸው። ” ብሎ ይናገራል፡፡ የበሬ መውጊያ የሚባለው፣ ደንባራውንና ደካማውን በሬ፣ ወደ ፊት ዘሎ እንዲሄድ የሚያደርግ የግብርና ዕቃው ነው፣ ተኝቶም ከሆነ፣ ከተኛበት ቀስቅሶ የሚያስሮጥ ነው፡፡

እንዲሁም በጥበብ መልእክትን የሚያስተላልፉ ጠቢባን፣ ሰዎችን ከያሉበት (እንቅልፍ ወይም ተመችቶአቸው ከተቀመጡበት) ሁኔታ ቀስቅሶ ለሚፈልጉት ዓላማቸው ያስሮጣሉ፡፡

ለምሳሌ

ከነህምያ ንግግር በፊት በኢየሩሳሌም የነበሩ ነዋሪዎች በፈራረሰው ቅጥርና ከተማ መኖርን ለምደውበት፣ ባይፈልጉትም ተቀብለውት፣ ምናልባትም እንደ ሌሎቹ ከዚያ ተማርከው ባለመወሰዳቸው እንደ ጸጋም ተቀብለውት እየኖሩ ነበረ፡፡ ነህሚያ ግን መጥቶ ሠላማቸውን ረበሸ፣ በክብር ሳይሆን ለካስ በውርደት ነበሩ፡፡ ተመቻችተው ከመቀመጥ ይልቅ ተነስተው መሥራት እንደሚገባቸው መከራቸው፡፡ ከነህምያ ቅስቀሳ በኃላ (ነህ 2፡17)፣ ሰዎቹም ተነስተው በየአጠገባቸው ያለውን የፈራረሱ ቅጥሮች መስራት ጀመሩ (ነህ 3 ተመልከቱ)፡፡

ዳዊት ከአቤሴሎም ጋር በነበረው ጦርነት ውስጥ፣ አኪጦፈልን ፈርቶ ወደ እግዚብሄር የጸለየው የአኪጦፈል ጉልበት ወይም ጦረኛ መሆኑ ስለሚያስፈራው አልነበረም፡፡ ግን በሚናገረው የጥበብ ምክር የዳዊትን መንግስት ሊያፈርስ እንደሚችል ስለፈራ ነው እንጂ (2ሣሙ 15፡31፣ 16፡23፣)፡፡ የጸሎቱም መልስ እንዲህ ሆነ፣ “እግዚአብሔርም በአቤሴሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የአኪጦፌልን ምክር እንዲበትን አዘዘ” (2ሣሙ 17፡14) በዳዊት አረዳድ የአኪጦፌል የጥበብ ምክር ሀገርን ይገነባል፣ ግን ያለአግባብ ጥቅም ላይ ከዋለ አሀገርንም ይበትናልና በክፉ ላይ እንዳይውል ዳዊት ጸሎት አደረገ፡፡

አስተር በጦሪነት ሳይሆን፣ በጸሎትና ጥበብ በተሞላበት ንግግሯ ነው ሕዝቧን በሓማን ከተደገሰላቸው ጥፋት የታደገችው (አስተር 7፡2-4)፡፡

ስለዚህ የጥበብ ንግግር፣ ጸጋ ያለበት ንግግር፣ የሰዎችን ቀልብ የሚወስድና የእግዚአብሄርን ሃሳብ ወደ ሰዎች ልብ የሚወስድ ንግግር በማናቸውም የማህበረሰብ ሕይወት ውስጥ የዋዛ ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡

በመጽሓፈ ምሳሌ ውስጥም ስናነብ (10፡31) እንዲህ ይላል፣ “የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፤ የኀጥኣን አፍ ግን ጠማማ ነው።” ይህ ማለት በእግዚአብሄር ዘንድ ነገሩ ሁሉ ተቀባይነት ያገኘ ሰው (ጻድቅ) ንግግሩ ለሚሰሙት ደስ ያሰኛል ማለት ነው፡፡ ይህ አይነት የንግግር ጸጋ የደከሙትን ያበረታል፣ የዛሉትን ያጠነክራል፣ የጠፉትን ይመልሳል፣ ሰውንና እግዚአብሄርንም ያቀራሪባል፡፡

ኢሳይያስ ሲመሰክር (50፡4)፣ “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል” ይላል፡፡ እግዚአብሄር ፈቃዱን ለማድረግ የተዘጋጁ ልቦች፣ ሌሎችንም መደገፍ የሚችል ቃል ለመናገር የሚበቁ አድርጎ መላሳችንን ያስተምርልን፡፡

ወደ ጌታ ኢየሱስ ንግግር ስንመለስ፣ “ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ” አድማጮች እንደ ተገረሙ አንብበናል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ንግግሩ መልካም ከመሆኑ የተነሳ፣ ሰዎች እርሱን ሲሰሙ፣ ራሳቸውንና እግዚአብሄርን እንዲሁም ሌሎችን ሰዎች በትክክለኛ መንገድ እንዲያዩ የሚያደርግ ነበረ ማለት ነው፡፡

ግን ደግሞ “የጸጋው ቃል” የሰሙ ሰዎች ወዲያው ሥልጣኑ ላይ ጥያቄ ማስነሳት ጀመሩ፡፡ ሰዎቹ እስከ መጨረሻው ለኢየሱስ መማረክ /መሸነፍ አልፈለጉም፡፡ “ከአፉ የሚወጣው የጸጋው ቃል” ለጆሮአቸውና ለልባቸው ቢጥምም፣ አእምሮአቸው ግን ጥያቄ በማመንጨት መቃወሙን ቀጠለ(1ቆሮ 10፡5፣ ኤፌ 4፡17፤ ቆላ 2፡18)፡፡ ‹እንዴት አድርጎ ነው የዮሴፍ ልጅ፣ የሰፈራችን ልጅ፣ የልጆቻችን እኩያ፣ ወዘተ. ይህንን አይነት ንግግር ማድረግ የሚችለው?› ፡፡ አሁን እየተደረገና እየተነገረ ያለውን በሚያውቁት የኢየሱስ ቤተሰዎች ታርክ ዋጋ ማሳጣት ጀመሩ፡፡

ይህ የኢየሱስ ንግግር የሚደነቅ፣ ጸጋ የሚገለጥበት ንግግር ቢሆንም፣ ሰዎቹ ወዲያው ላለማመንና ለመጠራጠር፣ ወዲያው ገፍቶ ወደ ውጪ ለማውጣት፣ ወዲው ለመግደል ተነሱ፡፡ ኢየሱስ ግን ጊዜው ገና አልደረሰምና፣ አምልጦአቸው ሄዴ፡፡

የሚገርመው ሁሉም መስክረውለት ነበረ፡፡ ሁሉም አድንቀውት ነበረ፡፡ ሁሉም እንደርሱ ያለ ሌላ እንደማይገኝ ተናግረውለት ነበረ፡፡ ግን ደግሞ ኢየሱስ የተናገረውን እውነት ለመቀበል ስላልፈለጉ እርሱን ማጥፋት ዓላማቸው አደረጉ፡፡ በተለይ የሃይማኖት መሪዎች፣ የራሳቸው ክብር ፈላጊዎች፣ የእግዚአብሄርን ሕዝብ የሚመሩ ግን እግዚአብሄርንና ፈቃዱን የማያውቁ መሪዎች፣ ኢየሱስን የማስወገድ ዕቅድ ማውጣት ጀመሩ፡፡

ይህ አይነቱ የሰው ልጅ ልምምድ በዱሮ ጊዜ ብቻ የቀረ አይደለም፡፡ ዛሬም ሰዎች ብዙ የሚያደንቁትንና የሚያከብሩትን ኢየሱስ፣ ወደ ሕይወታቸው ላለመጋበዝ ምክንያቶችን ይፈልጋሉ፡፡ የሰው ምክንያት፣ የተፈጥሮ ምክንያት፣ የአገልጋዮች ምክንያት ወዘተ. አንዳንዶቹ ደግሞ እግዚአብሄርን የወደዱትና ያከበሩት በመሰላቸው እጥፍ ኢየሱስን ማሳደድ ይጀምራሉ፡፡ በኢየሱስ ላይ የተደረገ ደግሞ እንዴት በተከታዮቹ ላይ አይደረግም?

ሌላው ከዚህ ክፍል የምንማር፣ ለንግግሮቻችን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ነው፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደሚመስል፣ እኔን ምሰሉ” ያለው ሐዋሪያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበረ፡፡ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን።” (ቆላ 4፡6)

ብዙ ሰዎች ቤተክርስቲያን የሚታስተላልፈውን የክርስቶስ ቃል እየሰሙና እያደነቁ ግን እይታቸው፣ እምነታቸውና አስተሳሰባቸው እንዲለወጥ ስለማይፈልጉ ብቻ፣ የወንጌሉም የቤተ ክርስቲያንም ጠላት ሆነው ይመላለሳሉ፡፡ ቃሉ “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” ይላልና (ያዕ 4፡4)፡፡

እግዚአብሄር ይባርካችሁ፡፡
በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *