Sermons

ከድካምሽ ተፈትተሻል

ከድካምሽ ተፈትተሻል

ከድካምሽ ተፈትተሻል

10 በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር።

11 እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም።

12 ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና። አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤

13 ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።

14 የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን፦ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ።

15 ጌታም መልሶ፦ እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን?

16 ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው።

17 ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው። (ሉቃ 13፡10-17)

ምንድን ነው ያጎበጠህ/ሽ?

የሰው ልጅ ጎብጦ እንዲሄድ ከሚያድርጉ ነገሮች አንዱ የድካም መንፈስ ነው፡፡ በሽታ፣ ሓጢአት፣ ሃዘን፣ ጭንቀት፣ ወዘተ. ሰዎች ቀና ብለው እንዳይሄዱ የሚያደርጉበት ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በዚህ ክፍል የተጠቀሰው አጉባጭ ነገር የድካም መንፈስ ነበረ፡፡

ይህ ችግር በሴትዮዋ ላይ ዘመናትን አስቆጥሮአል፡፡ 18 ዓመት በሙሉ ተሰቃይታበታለች፡፡ ቀና ብላ መሄድ አልቻለችም፡፡

አምልኮ አናቋርጥ

ሆኖም ግን ከዚህ የምንማረው አንድ ነገር ቢኖር፣ ችግሮችና ተግዳሮቶች ዘመናትን ቢያስቆጥሩም አንድ ቀን እግዚአብሄር መፍትሄ ማምጣቱ እንደማይቀር ነው፡፡

እግዚአብሄር የደህንነት አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከድካም መንፈስ ነጻ ያወጣል፡፡ እንዲሁም ሰዎችን ከሚያጎብጡ ነገሮ በሽታዎች ቢሆኑ፣ ሃጢአት ቢሆን፣ ሃዘንና፣ መከራም ቢሆን ኢየሱስ ነጻ ያወጣል፡፡

በአነበብነው ታሪክ ውስጥ የተጠቀሰችው ሴትዮ፣ ለ18 ዓመት ብርታቷ ተወስዶባታል፡፡ ይህ ደግሞ ቀና ብላ እንዳትሄድ አድርጓታል፡፡ ሠይጣን ከባድ ሸክም ጭኖባታል፡፡

ሆኖም ግን ከነ ድካሟ በአምልኮ ቦታ የሚትገኝ፣ ነበረች፡፡ ለማማረር፣ ከሰዎች ተለይታና በቤቷ ተደብቃ ለመኖር በቂ የሚመስል ምክንያት ነበራት፡፡ እንዴት አድርጌ ከእነ ጉብጥናዬ የአምልኮ ቦታ እሄዳለሁ አላለችም፡፡

ምናልባት የጉብጥናዋን ነገር፣ ቋሚ ችግሯ አድርጋ ተቀብላዋለች፡፡ ወይ ደግሞ እግዚአብሄርን ማምለክ ከሁኔታዋ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ ገብቷት ይሆናል፡፡ ግን ለማምለክ በቦታዋ ተገኝታለች፡፡

ያን ጊዜ ነው ኢየሱስ የመፈታትን ቃል የተናገረባት፡፡ “ ከድካምሽ ተፈትተሻል ” አላት፡፡ ከእንግዲህ ችግርሽ ጊዘው አልፎበታል፣ ከእንገዲህ ጉብጥናሽ ታሪክ ብቻ ነው፡፡ ከድካምሽ ነጻ ወጥተሻል፡፡ ኢየሱስ ዛሬም ነጻ ያወጣል፡፡ ኢየሱስ ዛሬም ከድካም መንፈስ ይፈታል፡፡ ኢየሱስ ዛሬም ይችላል፡፡ ኢየሱስ በድንገት፣ ባልጠበቅህው አንቺም ባልጠበቅሽው ጊዜ መጥቶ መፈታትን በሁኔታህ/ሽ ላይ ያውጃል፡፡ “ከድካምሽ ተፈትተሻል!”

እንግዲህ ከሴቲዮዋ የምንማረው፣ ጎብጠውም፣ ታመውም፣ ተቸግረውም፣ ደክሞንም ወደ አምልኮ ቦታ መምጣት ይቻላል፡፡ እኛ የእግዚአብሄርን መንግስትና ጽድቁን ስንፈልግ፣ ሌላው (ፈውሱ፣ ነጻነቱ፣ በረከቱ፣ ገንዘቡ፣ እውቀቱ፣ ንብረቱ፣ ወዘተ.) ይጨመሩልናል፡፡ ክርስቶስ ለችግረኞች፣ ለሓጢአተኞችም ነው፡፡

ችግሮችም ዓሜታት ስላስቆጠሩብን እድሜ ልክ ወይም ለዘላለም ከእኛ ጋር ይኖራሉ ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በቃ ሲል ያበቃሉ፡፡ ያቺ ሴት “የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም።”

ምናልባት ይህቺ ሴት ቀንታ ለመሄድ ብዙ ጥራለች፣ ብዙ ሞክራለች፣ ምናልባትም ብዙ ባለመድሃኒቶችን ፈልጋለች፣ ምናልባትም ብዙ ጊዜ ፆማ ጸልያለች፡፡ ነገር ግን “ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም” ነበረ።

አንድ የጉብኝት ቀን አለ፡፡

አንድ ቀን ግን፣ አንድ ቀን፣ ኢየሱስ በቦታው ሲገኝ፣ ኢየሱስ ሰው ሊሰራ በማይችልበት ጊዜ ለሥራ ሲነሳ፣ አንድ ቀን ጉብጥና አበቃ፡፡ አንድ ቀን ታሪክ ተለወጠ፡፡ አንድ ቀን የሚፈውስና ነጻ የሚያወጣው የኢየሱስ ቃል ደረሰላት፡፡

ያቺ ቀን ለሌሎች የሚትመች ቀን ላትሆን ትችላለች፡፡ ያቺ ቀን “የሰንበት” ቀን ሊትሆን ትችላለች፡፡ ይህቺ ቀን ኢየሱስንና ሥራውን በሚቃወሙት ሰዎች መካከል የተፈጠረች ጊዜ ሊትሆን ትችላለች፡፡ ግን ይህቺ ቀን፣ የመፈታት ቀን ናት፡፡ ቃል ከኢየሱስ ይወጣል፡፡ የኢየሱስም እጅ ለመዳሰስ ትዘረጋለች፡፡ “ ከድካምሽ ተፈትተሻል! ”

“ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።” ምናልባት በጸሎት ቤትም ሆነህ፣ በአምልኮ ቤትም እያለሽ ምስጋና ከአፍህ ርቆ ይሆን? በመከራ እና በሲቃይ አንቺም ለማመስገን አቅም አጥተሸ ይሆን? አይዞሽ፣ አንቴም አይዞህ፣ ቀጥ ብሎ ለመቆምና እግዚአብሄርን የማመስገን ጊዜ ይመጣል፡፡ አሁንም መጥቶአል፡፡ ኢየሱስ “ ከድካምሽ ተፈትተሻል! ” አላት፡፡

ኢየሱስ በተናገረው መሠረት፣ የድካም መንፈስ የሰይጣን ማሰሪያ ሆኖ “የአብርሃምን ልጅ” ያስጨንቅ ነበረ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ባይገልጠው ኖሮ ማንም ይህ ከሰይጣን እንደሆነ አያውቀውም፡፡ የተለመደው በሽታዋ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የተፈጥሮ ቁመናዋን አበላሽቶባታል፡፡

ጌታ ደግሞ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ያስባል፡፡ ሰይጣን አንዳንዶችን በድካም መንፈስ፣ አንዳንዶችን በክፋት መንፈስ ሌሎችን ደግሞ በስቃይ እና በበሽታ አስሮ ያሰቃያቸዋል፡፡ እዲህ ለታሰሩትም መፍቲሄ ማምጣት የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡

ኢየሱስ ይጠራል፡፡

ኢየሱስ፣ ሲያይና ሲጠራ ወደ እርሱ መሄድ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ “ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራት”

ኢየሱስ ሲጠራ፣ ለተመልካች ነገሮችን ያላገናዘቤ ይመስላል፡፡ ግን ኢየሱስ ሠይጣንን ፊትለፊት ለማዋረድና ሴቲዮዋ ደግሞ የምስጋና ምክኒያት እንዲትሆነ ወደ ራሱ ጠራት፡፡ ብዙ ጊዜ እንደርሷ ዓይነት ችግር ያላቸው ሰዎች ወደ ፊት ለመውጣት ይቸገራሉ፣ ያፍራሉ፣ ወይም ምቾት አይሰማቸውም፡፡ ኢየሱስ የጠራት በጭካነ ሊመስለን ይችላል፡፡ እርሱ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነጻ ሊያወጣት ነው፡፡

ዛሬም በተለያዩ አይነት እስራት ውስጥ ያሉትን ኢየሱስ እየጠራ ነው፡፡ እርሱ ሲጠራ ሰምተው ወደ እርሱ የሚሄዱትም ለዘመናት ከያዛቸው እስራት ነጻ ይወጣሉ፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡

ምናልባት ይህንን ታሪክ ሲናነብ መገንዘብ የሚያስፈልገን ነገር ይኖራል፡፡ ሴቲዮዋን ያጎበጠው ሰይጣን ነበረ፡፡ በተጨማሪም፣ እንደ ሃጢአት፣ በሽታ፣ መከራ፣ ሃዘን ሊያጎብጡ ይችላሉ፡፡ ኢየሱስ ለእነዚህ ሁሉ መፍትሄ ነው፡፡

ሌሎች ሊሉ የምችሉትን ረስተን ኢየሱስ ሲጠራን ወደ እርሱ መምጣት ዘመናት ካስቆጠረብን ችግራችን ይለያያናል። በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም አምልኮአችንን ማቆም የለብንም። እግዚአብሄር ራሱ ሁኔታዎችን ይለውጣልና።

እግዚአብሄር ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *