Sermons

እውነተኛ አምልኮ

worshiping the Lord in truth and Spirit

የዕለቱ የወንጌል ክፍል፡

ማር 7 1-13  (እውነተኛ አምልኮ ይፈለጋል፡፡)

1 ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።

2 ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ።

3 ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥

4 ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ።

5 ፈሪሳውያንም ጻፎችም፦ ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት።

6 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤

7 የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ።

8 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ።

9 እንዲህም አላቸው፦ ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።

10 ሙሴ፦ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ፦ አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና።

11 እናንተ ግን ትላላችሁ፦ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፦ ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥

12 ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤

13 ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።


በዚህ ክፍል ፈርሳዊያንና የሕግ አስተማሪዎች ከኢየሩሳሌም ተጠራርተው ኢየሱስ ወደ ነበረበት (ወደ ገሊላ) እንደ መጡ እናነባለን፡፡ ኢየሱስንም ከብበውት ነገሮችን ሁሉ በቅርበት ይከታተሉ እንደነበርም እናያለን፡፡ ገሊላ ከኢየሩሳሌም ወደ 100 ማይልስ ይርቃል ተብሎ ይገመታል፡፡

እነዚህ ሰዎች ከዚያን ያክል ርቀር የመጡት እንደ ሌሎቹ በኢየሱስ ዘንድ ካለው በረከት ለመካፈል፣ ትምህርቱንም ለመስማት ወይም ደግሞ ለነበረባቸው በሽታ ፈውስ ለማግኘት አልነበረም፡፡ ምናልባትም፣ ራሳቸውን አዋቂዎች አድርገው ስለመጡና ኢየሱስንም ለገዳደር ስለመጡ፣ ከኢየሱስ አንዳች መልካም ነገር ሰምተው ለመጠቀምም የተዘጋጁ አይመስሉም፡፡

 

ሕግን ለማስከበር የመጡ ሰዎች የሕጉን ምንጭና ዓላማ አለማወቃቸው ግን ለኢየሱስ ይገርመው ነበረ፡፡ አብሳኛው የገሊላ ሰዎች እነርሱን ከኢየሩሳሌም የመጡ ሓይማኖተኞችና የእግዚአብሄር ሕግ ባለሙያዎች ሆነው እንደመምጣታቸው የሚፈሩአቸውና የሚያከብሩአቸው ቢሆንም፣ የሰውን ሁሉ ልብና ሥራ ለሚያውቀውና ለሚመዝነው ኢየሱስ ዘንድ ግን እነዚህ ሰዎች እነርሱምን የሚከተሉአቸው ሁሉ ‹‹ የከንፈር ብቻ አምላኪዎች›› ሆነው ይታዩ ነበር፡፡God requires worship that is in truth and Sprit እውነተኛ አምልኮ ይፈለጋል

ምክንያቱም ለራሳቸውም የእግዚአብሄርን ሕግ የተውና በሰዎች ወግ የተጠመዱ ናቸው፡፡ ይህንን በሌላ አገላለጽ ስንናገር፣ የተጠሩበትም ሆነ የሚኖሩለት ዓላማና ምክንያት የጠፋባቸው፣ ከመንገድ የሳቱ አስተማሪዎችና መሪዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ይህንኑን ሕይወታቸውን ኢየሱስ በሌላ ቦታ ሲገልፀው ‹‹ዕውር ዕውርን መምራት ይችላልን?›› ብሎ በመጠየቅ ነው፡፡

የሚያሳዝነው ደግሞ አለማወቃቸውን የማያውቁ፣ መሳታቸውን የማያስተውሉ፣ ሌሎችን በእነርሱ መንገድ ለመምራት ግን ብዙ ዋጋ እየከፈሉ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱ ስናገራቸው ፣ ‹‹እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።›› ብሎአቸዋል፡፡ ልክ በማርቆስ ላይ እንደምናነበው ወደ 100 ማይልስ ገደማ ተጉዘው ሕዝብን በኢየሱስና በትምህርቱ ላይ ለማሳመጽ እንደሚሠሩት ማለት ነው፡፡

በዮሓንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ሲመልስ (9፡41)፣ ‹‹ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ኃጢአታችሁ ይኖራል›› ብሎ ነበር፡፡ ኋጢአታችሁ ይኖራል ማለት ምን ማለት ነው? አለመናዘዝና ንስሓ አለመግባት ለኃጢአት ሕያውነትን ይሰጣል ማለት ነው፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን እንዲህ በእግዚብሄር ፊት ራስን የማመጻደቁ ባሕሪይ የእግዚአብሄርም ፍርድ ይቀሰቅሳል፡፡ በኤርሚያስ 2፡35 እግዚአብሄር ስለእስራኤል በነቢዩ ሲናገር ‹‹ አንቺ ግን፦ ንጹሕ ነኝ በእውነት ቍጣው ከእኔ ተመልሶአል አልሽ። እነሆ፦ ኃጢአት አልሠራሁም ብለሻልና በፍርድ እከስስሻለሁ›› ብሎ ነበር፡፡ ጠቢቡ ሴለሞን ደግሞ ‹‹ ኋጢአቱን የሚደብቅ አይለማም›› (ምሳ 28፡13) ብሏል፡፡

ዛሬም ቢሆን ‹‹ኃጢአትን መንከባከብ›› ሳይሆን መናዘዝና ከርሷ መመለስ ለሰው ልጅ ነጻነትንና ሕይወትን ያስገኛል፡፡ ቃሉም ‹‹ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።›› ይላልና(1ዮሓ 1፡8-10)፡፡

እንግዲህ ወደ ማርቆስ 7 ስንመለስ፣ ከኢየሩሳሌም ለመጡት ፈርሳዊያንና የሕግ አስተማሪዎች ኢየሱስ ‹‹ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነውተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ።›› ብሎ ይወቅሳቸዋል (ቁ 6-7)፡፡ ይህ ዓይነቱን የአፍ ብቻ የሆነውን አምልኮና አገልግሎት እግዚአብሄር ከጥንት ጀምሮ የጠላው፣ የማይቀበለውና እንደዚህ የሚያደርጉትንም እንደማያጸድቅ ከትምህርቱ መረዳት እንችላለን፡፡

ጌታ ኢየሱስ ሲናገራቸው፣ የእግዚአብሄርን ትታቸው ወደ ራሳችሁ ወደ አባቶቻችሁም ወግ ተመልሳችኋል ይላቸዋል፡፡ ልክ እንደ የእግዚአብሄር ቃል አድርገው የራሳውን ህግ ይሰብካሉ(ቁ 7)፡፡ የእግዚብሄር ፍላጎትና ፈቃድ ትቶ (ቁ.8) የሰዎችን ሃሳብና ፈቃድ፣ የሰዎችንም ሥርዓት ማግዘፍ ትልቁ ችግራቸው እንደነበር ኢየሱስ በግልጽ ፍትለፍት ተናገራቸው፡፡

በተጨማሪም ኢየሱስ ሰዎቹ ስለእግዚአብሄር ህግ ያላቸውን ንቀትም (ቁ.9) አበክሮ ይናገራል፡፡ ይህ የራስን ህግ እንደ እግዚአብሄር ቃል የማስተማሩ፣ የእግዚአብሄር ህግ የመተውና የመናቅ ሁኔታ የእግዚአብሄርን ቃል አቅም ወደ ማሳጣት ወይም ወደ መሻር መርቶአቸዋል (ቁ.13)፡፡

በአንድ ሰው ሕይወት፣ አገልግሎት ወይም የአምልኮ ቦታ ውስጥ የእግዚአብሄር ቃል አቅም ካጣ ወይም ከተሻረ እውነተኛ ፈውስና አርነት በዚያ ሰው አይኖርም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢየሱስ በግልጽ ፍትለፍት ተናገራቸው፡፡

ይህ የኢየሱስ አቀራረብ በዘመናችን ከተለመደው የመንፈሳዊ ችግር አፈታት ዘዴ ጋር አይመሳሰልም፡፡ ምክንያቱም፣ በአብዛኛው የሚደረገው ንጽጽራችን የሌላውን ሰው ሓሳብ ከራሳችን ሓሳብ ጋር፣ የሌላውን ፍላጎት ካራሳችን ወይም ከቡድናችን ፍላጎት ጋር፣ የሌላውን ሥርዓት ከራሳችን ሥርዓት ጋር እያመዛዘንን እንከራከራለን፡፡ ኢየሱስ ግን የፈርሳውያኑንና የሕግ አዋቅዎችን አሠራር እግዚአብሄር ከሚፈልገው አሠራር ጋር እያስተያየ ተናገራቸው፡፡

በተጨማሪም ደግሞ ኢየሱስ ‹እናንቴም በራሳችሁ መንገድ ቀጥሉ፣ እኔና ተከታዮቼ ደግሞ በራሳችን መንገድ እንሂድ› አላለም፡፡ ግን ሰዎቹ የፈለጉትን የማድረግ ምርጫ ለእነርሱ ትቶላቸው፣ መነገር የነበረበትን እውነት ግን ተናገራቸው፡፡

ይህ ኢየሱስ ለምሳሌ ያህል ሰዎቹ ያደርጉ ከነበረ ነገሮች አንዱን አነሳላቸው (ቁ 11-13)፡፡ በዚያን ዘመን በነበሩ የአይውድ እምነት ተከታዮች ዘንድ ድርግቱ ተቀባይነት ያገኘና ሕዝብ ሁሉ የሚቀበሉት ልምምድ ነበረ፡፡ ኢየሱስ ግን ከድርግቱ ጋር የተያያዘው መሪ ሓሳብ ከእግዚአብሄር ቃል ስለሚጋጭና ትክክል ስላልነበረ አልተቀበለውም፡፡ ሀገር ሁሉ፣ ዓለምም ሁሉ ተስማምተው በእግዚብሄር ሃሳብ ላይ በሚነሳ መልኩ ሥርዓቶችን ብገነቡም፣ የእግዚብሄር ሐሳብ አያስለውጡትም፣ በክፋታቸውም እግዚአብሄር አይሸነፍም፡፡

እውነተኞች የእግዚብሄር መልእክተኞችም፣ ከሕብረተሰቡ የወጡ እብዶችም እየመሰሉ ከእግዚአብሄር ጎን ተሰልፈው እውነቱን ለሕዝብ ያውጃሉ፡፡ እስቲ በዚህ በኢየሱስ ትምህርት ራሳችንን፣ ሥራዎቻችንን እና አሠራሮቻችንን እንፈትሽ፡፡ ወደ እግዚአብሄር ሃሳብም እንመለስ፡፡

 

እግዚአብሄር በጸጋው ይርዳን፡፡

 

ጌታ ይባርካችሁ

(በተክሉ፣ መካነ የሱስ በስኮትላንድ 2 ሴፕተ.2018)

 

እግዚአብሄር በጸጋው ይርዳን፡፡

 

ጌታ ይባርካችሁ

(በተክሉ፣ መካነ የሱስ በስኮትላንድ 2 ሴፕተ.2018)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *