SermonsTeachings

እልካችኋለሁ

እልካችኋለሁ ፡፡

እልካችኋለሁ (ሉቃስ 10:1-11)

አንዲት በግ በተኵላዎች መንደር መገኘቷን ቢታውቅ ምን የምታደርግ ይመስላችኃል? አንድ ወታደርስ የበላይ አዛዡን ትዕዛዝ ለመፈጸም በጠላትነት በሚፈልጉት መካከል ብላክ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይህ እጅ ለመስጠት ያልተዘጋጄ ግን ብዙዎችን ለመማረክ የሚሄድ ወታደር ሊይዙት በሚፈልጉ ጠላቶቹ መካከል ራሱን ቢያገኝ ምን ማድረግ አለበት? ይህ ወታደር ለዓላማውና ለተልዕኮው ታማኝ በሆነ ልክ በሚጠሉት ሰዎች መንደር የሕይወቱ ተጋላጭነት እየጨመረ ይሄዳልና ራሱን ለማዳን ተስፋ የሌለው ያደርገዋል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዴቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ ሲልክ የሰጣቸው ማስጠንቀቂያና መመሪያ ነበረ፡፡ የጦር አዛዥ ወታደሮቹን ተልዕኮና መመሪያ ሠጥቶአቸው እንደሚልክ አይነት ይመስላል፡፡

“ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ” (ቁ3) ። ተኵላ የቤግ ጠላትም በግ ወዳድም ነው፡፡ አስተውሉ የቤግ ወዳጅ አላልኩም ግን በግ ወዳድ፡፡ ተኩላ በግን ለመብላት ይፈልጋል፣ ያድናል፣ ይከታተላል፣ ባገኘበት ቦታም ለመያዝ ያሯሩጣል፡፡ ጌታ ኢየሱስም ተከታዮቹን ወደ ዓለም ሲልክ፣ በዓለማዊ አስተሳሰብና አገዛዝ ተይዘው ያሉትን ለመታደግ “ሂዱ” ብሎ ላከ፡፡

ዓለም ሰዎችን ለዘመናት ሲትውጥ፣ ሲትበላም ነበረች፡፡ ዛሬም ቢሆን እንዲሁ፡፡ ዓለም የእግዚአብሄር ሰዎችን ለማሸነፍ፣ ለመዋጥ፣ የራሷ ለማድረግ በብዙ ትጥራለች፡፡ መጽሓፉም “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” ይላል (1ዮሃ 2፡15)። በዓለም ወዳድ ወይም ዓለማዊያን መካከል መኖር እጅግ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህም በሌላ ቦታ ጌታ ኢየሱስ ወደ አባቱ ስለተከታዮቹ ሲጸልይ፣ “እንድትጠብቃችው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንህም” ብሎ ነበረ፡፡ ያ ማለት በዓለም ወይም በዓለማዊያን መካከል ለሚኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች ጦሪነቱ ና መታደኑ ምን ያክል አስከፊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው (ዮሃ 15፡19)፡፡

ዓለም ብዙ ገጽታ አላት፡፡ ዓለማዊያንም እንዲሁ፡፡ በዓለም ብዙ ነገር አለ፡፡ ሓይማኖተኝነት (“የሙሴ ደቄ መዝሙር ነን” የሚሉ)፣ ፖሌትከኛነት (ለቄሳር ግብር የሚሟገቱ)፣ ለክፋት፣ ራስ ወዳድነት፣ የዝናና ክብር ፍላጎት፣ ወዘተ. ስለዚህ ዓለም ለእርሷ የማይመች ሓሳብ ይዞ የሚሄደውን ማንኛውን ሰው ለመዋጥ/ ለመብላት ያላትን ሃብትና ዕውቀት ሁሉ ትጠቀማለች፡፡ ከፈለገች ሃይማኖቱን፣ ካላዋጣት ፖሌትካውን፣ ካልሆነ ሃብትን፣ ካልሆነ ጊዜያዊ ደስታ የሚያስገኙ ሌሎችን ነገሮች፣ ካልሆነ ጦሪነትን፣ ከፈለገች ደግሞ ዕውቀትና ምርምርን ተጠቅማ ያገኘችውን ሁሉ መቆጣጠርና የራሷ ለማድረግ ትሠራለች፡፡

ጌታችን ኢየሱስም ወደዚህች ተደራጅታ ወደ ተቀመጠችና የብዙ ምዕተ-ዓመታትን ልምድ ያላትን ዓለም ጥቅቶችን ጠርቶ ላከ፡፡ እነዚህ የተጠሩ ጥቅቶች ደግሞ ሄደው ሌሎችን እንዲያወጡና ስላሉበት ሁኔታ እንዲያሳውቋቸው ላካቸው፡፡ “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበች” እንዲሉአቸው፡፡

ይህ መለወጥ የማይችል የበተክርስቲያን ድምጽ ነው፡፡ የእውነተኞች የክርስቶስ ተከታዮችም ስብከት ነው፡፡ ሰው ቢሰማም ባይሰማም መነገር ያለበት መልእክት፡፡ ሰባኪዎቹም የተላኩት “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ” የሚለውን መልእክት እንዲያስተላልፉ ነው፡፡

ዓለም ስለእግዚአብሄር መንግስት መስማት ካቆመች ቆይታለች (ያዕ 4፡4)፡፡ ወይም ደግሞ ዓለም “የእግዚአብሄር መንግስት” ነው ቢላ የምታስተምረው ጠፊውን ዓለምን ነው፡፡ በሰይጣን አጋዥነት ትርጉሙን ቀይራዋለች (ማቴ 4፡8)፡፡ ስለዚህ በእርሷ ያሉት ሰዎች ትክክለኛ የሆነ የእግዚአብሄር መንግስት ጽንሴ-ሓሳብ የላቸውም፡፡

ቢሆንም ግን ጌታ ኢየሱስ በአድስ መልክ ትክክለኛውን የእግዚአብሄር መንግስት መምጣት ግንዛቤው እንዲኖራቸውና ወደ መንግስቱ እንድመጡ የተላኩ መልእክተኞችን ላከ፡፡ እነዚህ ተለኪዎች በዓለም ዓይን ሲታዩ በጣም ተጋለጭ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ጌታ ኢየሱስ እነርሱን በበግ ዓለማዊያኑን በተኩላ አስመስሎ ተናገረ፡፡ “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ (ቁ3) ።”

ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ የተጠቀመው እነርሱን ለማስፈራራት ወይም የዓለምን ብርታት በአእምሮአቸው ለመክተት አይደለም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ትልቅነትና ለዚህ መልእክት አድራሽነት የተሾሙ ሰዎች በራሳቸው ታምነው እንዳይሄዱ ነገር ግን ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሄር ሠጥተው እንድንቀሳቀሱ ለመምከር ነው፡፡

ከማጠቃለሌ በፊት እስቲ ጌታችን ለደቄ መዛሙርቱ ከነገራቸው መካከል ጥቂቶቹን አንመልከት፡፡

  1. ብቻችሁን የማትወጡት አገልግሎት ተቀብላችኋል፡፡ ይህ ከቁጥር አንጻር ነው፡፡ ምናልባት ሰባ/ሰባ ሁለት ሰዎች በአንድ ጊዜ ሁለት ሁለት ተደርገው ወደ 35(36) መንደር ሲሄዱ እጅግ ብዙ ይመስላሉ፡፡ ለስራው ሲበተኑ ግን ምን ያህል ተጨማሪ ብዙ መልእክተኞች እንደሚያስፈልጋቸው ይረዳሉ፡፡ ጌታም ለዚህ ጉዳይ እንድጸልዩ ትዕዛዝ ሰጥቶአቸዋል፡፡ ዛሬም በየመድረኩ ላይ የሚጋፉ አገልጋዮችን ስንመለከት ሰው በስቶ ሥራ ግን የጠፋ ይመስለን ይሆናል፡፡ ጌታ ግን፣ “መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” ብሎአል፡፡
  2. በጌታ ጉልበት ታመኑ፡፡ እናንቴ በተኵላዎች መካከል የተላካችሁ በጎተች ናችሁ፡፡ እሬኛና አዳኝ ካልረዳችሁ በአቅማችሁ ራሳችሁን እንኳ ማዳን በጉልበታችሁ አትችሉም ፡፡ ስለዚህ በብርታታችሁ ሳይሆን ከእናንተ ጋር በሚሆነው እና የመንግስቱ አዋጅ ነጋሪዎች ባደረጋችሁ በእግዚአብሄር ታመኑ፡፡ ይህ መታመን ደግሞ ስለነፍሳችሁ፣ ስለምግባችሁ፣ ስለልብሳችሁ፣ ስለጤናችሁ፣ ስለ አጠቃላይ ደህንነታችሁም (ሴክውሪቲም) ነው፡፡ በገንዘባችሁ ጉልበት አትመኩ (“ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ”)፤ የምታገኙት መስተንግዶ (ተቀባይነት) ላይ አትደገፉ፡፡ ሰላም እናንቴ ይዛችሁ ከወጣችሁት መልዕክት እንጂ ከምታገኙት ከበረታ አይመጣም፡፡ ይልቁንስ እናንቴ ለገባችሁበት ቤት ሁሉ ሰላም ሥጡ፡፡ “ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ።” በምግባችሁ ጥራትና ብዛት ላይ ኣይናችሁን አትጣሉ፡፡ ያገኛችሁትን ብሉ (ቁ 7-8)፡፡ በምግብ ላይ ዓይንን መጣል እነሄዋንን ከገነት አስወጥቶአቸዋል፡፡ በዓለም ያሉ ሰዎችም ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑባቸው አሉ፡፡ ስለዚህ እናንቴ ተልዕኮአችሁን በመወጣት የላካቸውን ጌታ ለማስከበር ሥሩ፡፡
  3. መልእክቱ ይተላለፍ፡፡ ሰዎች ስላልተቀበሉአችሁ ዝም ብላችሁ አትሂዱ፡፡ “ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ”። እየተፈለገም ቢሆን እየተጠላ ወንጌል መሰበክ አለበት።

ውድ አንባቢ ሆይ፣ ይህንን መልእክት ስታነብ /ስታነቢ ምን ታስብ/ቢ ይሆን? ስለራስህ፣ አንቺም ስለራስሽ ፣ ስለእግዚአብሄርና ስለመንግስቱ ምን ገብቶአል/ሻል? እንደ ዓለማዊ ወይስ እንደ መልዕክተኛ፣ ጠፊውን ዓለም ለመውረስ እንደሚሯሯጥ ወይስ የሰማይን መንግስት እንደሚጠባበቅ እየኖርክ/ሽ ነው? የእግዚአብሄር መንግስት አሁን ወደ አንቴ/ቺ እንደ ቀረበስ ተረድተሃል/ሻል ወይ?

እናስብበት፣ አሁን ጊዜው ሳያልፍ ለመንግሥቱ ወንጌል ጥሪ ተገቢ ምላሽ እንስጥ፡፡ ቃሉ “የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ” ይለናልና፡፡ እንዲሁም “ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ” ይለናል፡፡

እግዚአብሄር ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *