Sermons

ታንኳህን ለጌታ

መካነ የሱስ በስኮትላንድ፣ ስብከት፣ በሊሊ፣ አይዳ፣ ግላስጎ መካነ ኢየሱስ፣ ሉቃ 5 1-11፣ የእሁድ አገልግሎት፣ ታንኳሽን ጌታ ይፈልገዋል፡፡ ታንኳህን ለጌታ

ሉቃስ 5፡1-2 ታንኳህን ለጌታ (ታንኳሽን ለጌታ)

ቁ 1-3 “ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፥ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤ በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር።”

ብዙ ደክመው ግን ምንም አሣ ያልያዙ አሣ አጥማጆች መረባቸውን በጌንሳሬጥ ባህር ዳር እያጠቡ ያጥቡ ነበረ፡፡ ጌታ እየሱስ ደግሞ እዚያው አከባቢ የእግዚአብሄርን ቃል ለብዙ ህዝብ ሲያስተምር ከህዝቡ ብዛት የተነሳ ስፍራው ተጨናንቆ ነበር፡፡ በጣምም ስላጣበቡት በጀልባ ላይ ሆኖ ማስተማር ለጌታ የተሻለ አማራጭ ነበረ፡፡ እናም የጴጥሮስን ታንኳ (ጀልባ) ተውሶ፣ በእርሷ ላይ ተቀምጦ ህዝቡን አስተማረ፡፡ ሁሉንም ማዘዝ የሚችል ጌታ፣ (ቢፈቅድ ውሃ ላይ መራመድ የሚችለው ጌታ፣) ወደ ጴጥሮስ ታንኳ ገብቶ ጥቅት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፡፡ ኢየሱስ ትሁት ነበረ፡፡ ጴጥሮስም ለጌታ ታዘዘ፡፡ ታንኳውንም ለአገልግሎቱ ሠጠ፡፡

ከእኛስ ጌታ ዛሬ ምን ይጠይቅ ይሆን? ምን እንድናደርግለትስ ፈልጎ በትህትና ይጠብቀናል? ታንኳህን ለጌታ ሥጥ፡፡

ቁ 4-5 (ኢየሱስ) “ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን፦ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው ስምዖንም መልሶ፦ አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው።”

ጌታም ማስተማሩን (የራሱን ሥራ) በጨረሠ ጊዜ ጴጥሮስ መረቡን እንደገና እንዲጥል ነገረው (አዘዘው)፡፡ ጴጥሮስና ጓደኞቹ ለሊቱን ሙሉ አሣ ለመያዝ ሲደክሙ ነበረና በዚያን ሰዓት የሚያስፈልጋቸው ማረፍ ነበረ፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ ባይመስለውም የጌታን ቃል በማክበር መረቡን ጣለ፡፡ ጌታን ጨክኖ በመታዘዙ ብዙ አሣ ለመያዝ ቻለ፡፡ በራሳቸው ጊዜና ልምድ ሞክረው ምንም ፍሬ ያላገኙበት ሥራ ኢየሱስን ሰምተው (ታዝዘው) እንደገና ስሞክሩት ከጠበቁት በላይ አሣ ማግኘት ቻሉ፡፡ ለጌታ የሚታዘዝ መረቡን ጥሎ ባዶ እጁን አይመለስም፡፡ታንኳህን ለጌታ ሥጥ፡፡

ቁ 6-7 “ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው።”

ጌታ ብድራትን አይረሳም፡፡

በዚህ ቦታ እየሱስ የሚፈልገውን አገልግሎት ካገኘ በኃላ ምስጋናውን ለመግለጥ ባዶነታቸው የሚለወጥበትን ቃል ለጴጥሮስና ለጓደኞቹ ሰጠ፡፡ ቃሉ ደግሞ ባዶ መረባችውንና ባዶ ጃልባቸውን በአሣ የሚሞላ ነበረ፡፡ ጴጥሮስ ለጌታ አገልግሎት ጀልባውን በመፍቀዱ ጌታ ደግሞ የጴጥሮስን ጉድለት ሞላለት ብዙ የደከመበትን ነገር ግን ማግኘት ያልቻለውን ነገር ጌታ በቀላሉ እንዲያገኝ አደረገው፡፡ ታንኳህን ለጌታ ሥጥ፡፡

ሁልጊዜ ጌታ ስለ ስሙ የምናደርገውን ነገር አይረሳም፡፡ የእግዚአብሄር ቃልም እንዲህ ይላል “ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” (ማቴ 10፡42) “እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።” (ዕብ 6፡10)

ቁ 8-9 “ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው። ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥”

ጴጥሮስ፣ ጌታ ያደረገው ነገር፣ ባየ ጊዜ በመደነቅ እና በፍርሃት ተሞላ፡፡ የአይገባኝም መልእክቱን ለማስተላለፍም፣ በጌታም እግር ላይ ወድቆ ከርሱ እንዲርቅ ለመነው፡፡ ጴጥሮስ በሆነው ነገር፣ ምን ያህል የማይጠቅም እና ሃጢአተኛ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ጴጥሮስ ለሊቱን ሙሉ ደክሞ ያላገኘውን ብቻ ሳይሆን በአሳ ማጥመድ ሕይወቱ አግኝቶ የማያውቀውን የአሣ ብዛት አገኘ፡፡ ሆኖም ግን በይበልጥ ጉልበቱንና ልቡን ያንበረከከው፣ የአሳ ማግኘት ደስታ ሳይሆን የጌታ ጽድቅና የራሱ ሃጥአተኝነት ነበረ፡፡ ኢየሱስም የጴጥሮስን “ከነ ተለይ” ማለት ከጥላቻ ሳይሆን ከፍርሃት የመነጨ ጥያቄ መሆኑን አወቀና አትፍራ አለው፡፡

“አትፍራ፡፡”

10-11 “እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን፦ አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው። ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።”

በዚህ ስፍራ ጌታ ጴጥሮስን እና ጓደኛውን ወደ እግዚአብሄር ታላቅ ሥራ ሲጠራው እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ሠዎች የዕለት ተለት ኑኖአቸውን ለመሙላት የሚሮጡ አሳ አጥማጆች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ወደ ታንኳው ከገባ በሃላ ግን ነገሮች ተለወጡ፡፡ ታንኳህን ለጌታ ሥጥ፡፡

ሞት ያስፈራል፡፡ ኃጢአት ደግሞ ለሞት አሳሊፎ ይሰጣል፡፡ ጴጥሮስ በታንኳው ጭኖት የነበረውን መምህር (የጌታን) ሥልጣንና ማንነት ሲመለከት የሚሞት ሳይመስለው አልቀረም፡፡ እርሱ ከመሞቱ በፊት እየሱስ ተለይቶት እንዲሄድለት ለመነው፡፡

ጌታ ግን ሊገለው ወይም ሊፈርድበት ሳይሆን እርሱን ሊያገኝ ሂዶ ኖሮአል፡፡ በመጀመሪያ ታንኳን ብቻ የፈለገ ቢመስልም ለካስ ጌታ ጴጥሮስን ራሱን ፈልጎት ነበረ፡፡ እርሱ ይህንን ደካማና ሃጥአተኛ ሰው ተቀብሎታልና፡፡ ጌታ እነዚህን ተራ ሠዎች ከነድካማቸው እና ከነሃጥአታቸው እያሉ ነው የጠራቸው፡፡ ውድ እና ክቡር ወደሆነው ሰዎችን ወደ ማጥመድ (ወደ እግዚአብሄር መንግስት የማፍለስ) ሥራ በእርሱ እንደሚሠራም ነገረው፡፡

እነርሱም ይህ ታላቅ ጥሪ በልባቸው ሚዛን ሲደፋ አሳ በማጥመድ ህይወት ውስጥ አይተውት የማያውቁ እጅግ ብዙ አሣ ይዘው ሳሉ ተሯሩጠው ገበያ ከማፈላለግ ይልቅ ጀልባቸውን ወደ ዳር አውጥተው ያ ሁሉ የተደነቁበትን ብዙ አሣ እዛው ጥለው ጌታን በህይወት ዘመን ሙሉ ለመከተል ወሰኑ፡፡ ከጌታ ካገኙት ብዙ አሣ ይልቅ ጌታን ራሱን መከተል የተሻለ ሆኖ አገኙት፡፡ ታንኳህን ለጌታ ሥጥ፡፡

እኛም ዛሬ ጌታን ለመከተል እንደ ጴጥሮስ ከእኛ የሆነ የህይወት ፍሬ ሳይኖር እንዲሁ ከነ ሃጥአታችን እያለን ወደ እኛ ከመጣው ከጌታ ነው፡፡ እግዚአብሄር ወዶን እርሱን እንድንከተል ከጨለማ አውጥቶ የርስቱ ወራሾች አድርጎናል፡፡ ለመዳናችን ያደረግነው ምንም ዓይነት አስተዋፅዖ ሣይኖር እንዲሁ በጸጋው ድነናል፡፡ ስለዚህ እኛም ይህንን የመዳን/የሕይወት ጥሪ በጨለማ ላሉ ሠዎች በማካፈል ሰዎችን አጥማጆች ሆነን እንድንቀር ጌታ ይርዳን፡፡ በሌላ አገላለጥ፣ ጌታ እንድንሆንለት የሚፈልገውን ሆነን እንድንገኝ ጌታ ይርዳን፡፡

 

ጌታ ይባርካችሁ

በእህት ሊሊ የቀረበ

2 thoughts on “ታንኳህን ለጌታ

  1. የኔ እህት ሊዬ ወደ ምትወጂው ጌታ ሄደሻል . . . ብናዝንም ጌታን ለምን አይባልምና የወደደውን የሚያረግ አምላክ ነው፡፡ ትናፍቂኛለሽ

    1. ትንሾ ሌሌየ ትንሽ እያለሽ ስለተለየሁሽ ያ በራስ ተአማኔነት ያለው ወርቃማ ቃላትሽ ሁሌ ይናፍቀኝ ነበር በድምፁ ተገናኝተን በአካል ላገኝሽ እየናፈኩ ይሄ ሆነ …….ግን በጌታ ነገር የበረታሽ ስለነበርሽ ያ በቄ ሆኖል ተጽናናሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *