Sermons

ጌታ ሁልጊዜ ትልቅ

ጌታ ሁልጊዜ ትልቅ Ethipian and Eritrean Lutheran Christians in Scotland. Amharic Service,Evalgelical Church Mekane Yesus, Ethiopian Christian Church in Glasgow, Eritrean Christian Church in Scotland, Evangelical and Lutheran church,ECIS

ማር 9፡30-37 ( ጌታ ሁልጊዜ ትልቅ ነው፡፡)

30-31 ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤ ለእነርሱም፦ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል ይላቸው ነበር። 32 እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፥ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። 33 ወደ ቅፍርናሆምም መጣ። በቤትም ሆኖ፦ በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ተነጋገራችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 34 እነርሱ ግን በመንገድ፦ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ተባብለው ነበርና ዝም አሉ። 35 ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠርቶ፦ ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው።

36 ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው አቅፎም፦37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።

ቁ 30 ”ከዚያ ወጥተው” – ከቤት – ቁ.28

ወደ ላይ ተመልሰን ማር 9፡14 ስንመለከት ኢየሱስ ከነበረበት ቦታ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ “ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ

ምናልባት ይህ ክርክር ደቀመዛሙርቱ በሕዝብ ተከብበው እያሉ ሰለተደረገ፣ ጻፍቶቹ የኢየሱስ ወንጌል እንዳይሰበክ፣ ደቀ መዛሙርት አልፈው ተልዕኮአቸውን እንዳይፈጽሙ፣ በሕዝቡም ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ይሆናል፡፡ የሚያሳዝነው በዚያችው በክርክሩ ጊዜና ቦታ፣ በአጋንት የሚሰቃይና ከእርሱም ጋር የሚጨነቅ ወላጅ አባት መኖራቸው ነው፡፡ አባትየው ልጁን ያመጣው መፍትሔ ያገኝልኝ እንደሆን ልሞክር ብሎ ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ አጋንንቱን ሊያወጡለት አልቻሉም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ጻፍቶቹ በከረረ ክርክር ውስጥ አስገብቶቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ኢየሱስ መጣ፡፡

ኢየሱስ ሲመጣ ጻፍቶቹን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው፡- “ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ?” ብሎ (ቁ 16)፡፡ ምናልባት ለእኔ ሲገባኝ፣ ይህ ጥያቄ፣ ለምን ሥራ ታስፈቱአላችሁ ማለቱ ይመስለኛል፡፡ ወንጌልን ለመስባክ፣ አጋንንትን ለማስወጣት፣ በሽተኞችን ለመፈወስ ተልዕኮ ይዘው የወጡ ሰዎችን ጊዜ በክርክር መያዝ ልክ አልነበረምና፡፡ ብዙዎች ከሓጢአትና ከሠይጣን እስራት የወንጌሉን ቃል ሰምተው ነጻ መውጣት የነበረባቸው ጊዜ ሪዕሱና ዓላማው ግልጽ ባልሆነ ክርክር ተወስዶአል፡፡ ጌታ ሁልጊዜ ትልቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ተልዕኮአችንንና ጥሪአችንን ረስተን አላስፈላጊ ነገሮች ላይ ውድቷ ጊዜያችንንም ሆነ ሌሎች ሰዎች ለመዳን ያገኙትን ዕድል በከንቱ ስናጠፋ ጌታ ያዝናል፡፡

በቁ. 30 ላይ እንደምንመለከተው ኢየሱስ በምድር ላይ የነበረው ጊዜ በጣም እያጠረ ስለመጣ ቶሎ ብሎ የመጣበትን ዓላማ ለመፈጸም ስቻኮል፣ ደቀ መዛሙርት ግን ይህ የገባቸው አይመስልም፡፡

ቁ 19 ላይ ኢየሱስ “የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ?” ያለው የተሠጣቸውን ጊዜ ተጠቅመው እያመኑበት እንዳልሆነ ለማሳየት ነው፡፡ በምድር ላይ ሰው ሆኖ የሚመላለስበት ጊዜው በጣም አጭር በሆነበት በዚያ ሰዓት እነርሱ ግን ገና በእምነት አልተለወጡም ነበር፡፡ ጌታ ሁልጊዜ ትልቅ ነው፡፡

አላስፈላጊ ክርክር በሰዎች ሕይወት ውስጥ እምነትን፣ ደህንነትን፣ ሰላምንና ነጻ መውጣትን አያመጣም፡፡ እነዚህ ሁሉ መምጣት የሚችሉት ሰዎች እውነተኛው የእግዚአብሄር ቃል ሲነገራቸውና እነርሱም ሲቀበሉት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢየሱስ ከመጣ በሃላ እምነትን የሚያበረታታ ቃል የተናገራቸው፡፡

“ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው?” ብሎ ኢየሱስ የጠየቀውንም ጥያቄም ስንመለከት፣ ስለእምነት አስፈላጊ መልእክት ለማስተላፍ ፈልጎ ነው፡፡ ቁ 23 ኢየሱስ “ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።” ብሎአልና፡፡ በተለምዶ ብዙ ጊዜ ያስቆጠሩብን ችግሮቻችን መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚችሉ ስለማናምን ለመቀበል እንገደዳለን፡፡ ግን ጌታ ሁልጊዜ ትልቅ ነው፡፡ እርሱ ነገሮችን መቀየር ይችላል፡፡

ኢየሱስ በሁሉም አቅጣጫና በሚያደርገው በማናቸውም ነገር ሰዎችን በእምነት ወደሚገኘው ወደ እግዚብሄር መንግስት የማምጣት ዓላማ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል።”

ቁ. 28 ላይ “ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት፡፡” ኢየሱስም “ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም” አላቸው፡፡ ይህንን በማለቱ ኢየሱስ የአገልግሎት ሕይወትና መንፈሳዊ ጦርነት ሁልጊዜ ከተመሳሳይ ጉልበትና ብልሓት ጋር መታገል እንዳልሆነ ገለጠ፡፡

ስለዚህ ሁልጊዜ የሚያስፈልገን ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ሕያው አድርጎ መጠበቅ ነው፡፡ ስልትና ዘዴ ይቀየራል፡፡ ሥራና አሰራር ሊለወጥ ይችላል፡፡ የጠላትም ውጊያ እንዲሁ፡፡ ግን ጌታ ሁልጊዜ ታላቅ ነው፡፡ እርሱ ይመራል፣ ይመክራል፣ ሃይልንም ይሰጣል፡፡

ሌላው በዚህ ክፍል የምንመለከተው ኢየሱስ ጻፍትንና ሕዝቡን ብቻ ተችቶ እንዳላበቃ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም መጸለይና መጾም እንደሚገባቸው አመለከታቸው፡፡ አገልግሎታቸው በልምምድና በክርክር ብቻ ውጤታማ የሚሆን ሳይሆን በጸሎትና በጾም በሚያገኙት የእግዚአብሄር ሃይል ሁልጊዜ አስፈላጊ እንደሆነ አስተማራቸው፡፡ ዛሬም ይህ መልእት ለራሳችን ያስፈልገናል፡፡ ፆምና ፀሎት ለሕይወታችንም ሆነ ለአገልግሎታችን በተለይ ደግሞ መልኩንና ወገኑን እየቀያየረ የሚያጋጥመንን የጠላት ውጊያ ለማሸነፍ አስፈላጊ ነው፡፡

በሌላ አባባል ከእግዚአብሄር ጋር በመነጋገርና በእርሱ ፊት ራስን በማዋረድ በክፉ መናፍስት ላይ ድል ማግኘት አለ፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ በእግዚአብሄር በመደገፍ ካላገለገልን የሆነ ቦታ ደርሰን መቆማችን አይቀርም፡፡ ጌታ ሁልጊዜ ታላቅ ነው፡፡

ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በነበረው ጥቂት ቆይታ ይህንን የመታመን፣ የመደገፍና በእግዚአብሄር ፊት ራስን የማዋረድ ሕይወት እንዲለማመዱ መከራቸው፡፡

ከዚያም በኃላ ኢየሱስ ለብቻቸው አውጥቶአቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ አሳልፎ እንደሚሠጥ፣ መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞትና በሶስተኛውም ቀን እንደሚነሳ ግልጽ አድርጎ ነገራቸው (ቁ 30-31)፡፡ ጌታ ሁልጊዜ ታላቅ ነው፡፡

ይህን እውነት ማወቅ ለሕይወታቸውና ለአገልግሎታቸው አስፈላጊ ስለሆነ ሊነገራቸው ተገቢ ነበረ፡፡ የወንጌለም እምብር እዚህ ላይ ነው፡፡ ግን አልገባቸውም፡፡ ግልጽ ተደርጎ ቢነገራቸውም ሊገባቸው አልቻለም፡፡ እንዳይጠይቁትም ፈሩ፡፡ ይህ ፍሪሃት ምናልባት ከኩራታቸው ምናልባትም ልብ ካለማለት የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡

በእነርሱ ብቻ ላይ ጣት መጠቆም ግን አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ዛሬ ያለን ክርስቲያኖችና አገልጋዮች እንዲህ እንመስላለንና፡፡ ስለጌታ ዳግም ምጽአት ሰምተናል፣ ምናልባትም ሰብከናል፡፡ ግን ገብቶናል ወይ? ጌታ ኢየሱስ ማንም ባላወቀበት ጊዜ በድንገት እንደሚመጣ ተናግሮአል፡፡ ግን እኛ የምንኖራቸውን ሕይወቶቻችንና የሚናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ የጌታን ዳግም ምጽአት እያስታወስን፣ በግንዛቤ ውስጥ እያስገባንና ተልዕኮችንን ለመፈጸም ችኮላው ይሰማናል ወይ? ጌታ ይርዳን፡፡ ጌታ ኢየሱስ “ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ማድረግ ይገባኛል” ይል ነበረ፡፡

ለደቀ መዛሙርት እንደ ትንቢት የተነጋራቸው እና እንዲጠባበቁት የተጠየቁት ኢየሱስ ተላልፎ እንደሚሠጥ፣ እንዲሞት፣ እንዲነሳና ወደ አባቱ እንዲሄድ ከዚያም ተመልሶ እንደሚወስዳቸው ነበረ (ዮሓ 14፡ 1-6)፡፡ ከእነዚህ አብዛኛው ተፈጽሞ ስላሌ ለእኛ የምንጠብቃቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ ግን ለእኛ የቀረ አንድ ነገር ብኖር ኢየሱስ ዳግም እንደሚመጣና እንደሚወስደን ነው፡፡ ለዚህስ እኛ እየተዘጋጀንና ሌሎችን እያዘጋጀን ነው ወይ?

ለኢየሱስ ጊዜ አጭር ነበረ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ግን ነገሮች ቀላልና እንደዛሬው ብቻ መስሎ ይታዩ ነበረ፡፡ በደቀ መዛሙርቱም ሕይወት ይህ ጊዜውን የማወቅ ነገር እንዲሆን፣ በእምነት፣ በመታመን፣ በአፋጣኝ መልእክትን በማድረስ ሰዎችን ወደ እግዚብሄር መንግስት እንዲያመጡ ስለሚፈለግባቸው ኢየሱስ ለብቻቸው ወስዶ አስተማራቸው፡፡

በቁ 33 ኢየሱስ ጉዞአቸው ላይ ምን እንደ ተነጋገሩም ጠየቃቸው፡፡ በቁ. 34 ላይ “እነርሱ ግን በመንገድ፦ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ተባብለው ነበርና ዝም አሉ።” ይላል፡፡ የእነርሱ አይምሮና ልብ የተያዘው በዚህች ምድር ላይ “ታላላቆች” ወይም ፊተኞች ሆነው የመኖር ፍላጎት ነበረ፡፡ ኢየሱስ ስለሞቱና ትንሳኤው ሲነግራቸው እነርሱ ደግሞ ‹ያለ ኢየሱስ በሚኖሩበት ጊዜ› በመካከላቸው የማንን “ታላቅነት ተቀብለው” እንደሚኖሩ ይከራከሩ ነበረ፡፡ ሙሉ ትምህርቱም ስላልገባቸው፣ የሞቱን ነገር ብቻ ይዘው እርሱ ከሞተ ማን መሪ ይሁን ወደሚል ክርክር ገቡ፡፡

ኢየሱስ ግን የሰውን ልብ ጨምሮ የሚያውቅ ስለነበረ፣ ፍላጎታቸውና የፈለጉትን ለማግኘት እየተከተሉት ያለው መንገድ እንደማይጣጣም አሳያቸው፡፡

በክፍሉ እንደምናነበው ኢየሱስ “ታላቅ” ወይም ፊተኛ ለመሆን መፈለጋችሁ ኃጢአት ነው አላላቸውም፡፡ ይልቁንስ ፊተኛ መሆን ከፈለጋችሁ መከተል ያለባችውን መረሆዎች አሉ ብሎ ስለእርሱ መከራቸው፡፡ (ቁ. 35)

  1. ከሁሉ በሃላ ራስን ማሰለፍ ነው – “ከሁሉ በኋላ” ይሁን፡፡ ሌሎችን ያስቀድም ማለቱ ነው፡፡ ለእኔ ብቻ በሚል ሃሳብ መኖር አይገባወም፡፡
  2. “የሁሉም አገልጋይ ይሁን” ሁሉንም ደግሞ ከራስ አብልጦ ማየት፡፡ ወንድሜ ከእኔ ይሻላል በሚል እሳቤ ይኑር፡፡

ሰዎች ለምን ታላቅ መሆን ይፈልጋሉ ብለን ብንጠይቅ፣ ተቀባይነት ማግኘት እንዱና ትልቁ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምናልባት በመንገድ ላይ ሆነው ሲከራከሩም የደቀ መዛሙርቱ ሓሳብ ውስጥ የነበረው ይሄው ነው፡፡

ኢየሱስ ይህንን አይነቱን የታላቅነት መረዳት ማፍረስ ፈለገ፡፡ ኢየሱስ አሁን በምድር ላይ በስጋ እያሌ ብቻ በመካከላቸው ታላቅ ሆኖ እርሱ ከዚህ ምድር ሲሄድ ደግሞ በሌላ የሚተካ ታላቅነት እንዳልነበረው ማስገንዘብ ፈለገ፡፡ ጌታ ሁልጊዜ በመካከላችን ትልቅ ልሆን ይገባዋል፡፡ ስናየውም ሳናየው ስንቀርም፣ በቅባችን ሆኖ ሲያገለግለንም ምናልባት ሪቆናል ብለን ስናስብም ከርሱ ተሸሎ በሕይወታችን ታላቅ መሆን የሚገባው ሌላ ማንም የለም፡፡ ጌታ ሁልጊዜ ታላቅ ነው፡፡

ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሁልጊዜ በራሳቸው ሳይሆን በኢየሱስ ስም (የእርሱን ተልዕኮ) ይዞ መሄድ እንዳለባቸው፣ ያንን ተልዕኮ ይዞ የሚመጣባቸውን ማንኛውንም ሰው ደግሞ (ትልቅም ሆነ ትንሽ) መቀበል እንዳለባቸው አስተማራቸው፡፡ በአጠቃላይ እንግዲህ ትልቁ፣ መንግስት ያለውና ወደ መንግስቱ ሰዎችን ለማምጣት ሰዎችን ላኪው፣ ጌታ ነው፡፡

እንደ ክርስቲያኖች በምናደርጋቸው ማናቸውም ነገር ውስጥ የጌታን ታላቅነት ካሳነስንና ራሳችንን ወይም ሌሎችን ሰዎች ታላላቆች ማድረግ ከጀመርን ጥሪአችንን ረስተናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ ትልቅ ነው፡፡

(በተክሉ)

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *