Sermons

በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት

Seek the Lord while he may be found; call on him while he is near. Let the wicked forsake his way and the evil man his thoughts. Let him turn to the Lord, and he will have mercy (Isa 55:6-7 NIV)

“እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።” (ኢሳ 55፡6-7)

የሰው ልጅ በጊዜ፣ በቦታ እንዲሁም በሁኔታዎች የተወሰነ ነው፡፡ ለሰው ትልቅ እድል ገጠመው የሚባለው፣ እነዚህ በደንምብ አንድ ላይ ተቀነባብሮና ተሰካቶ ሲመቹለት ነው፡፡ የሰው ሕይወት በእነዚህ ወሳኝ የሆኑ ነገሮች ላይ ተመስሪቶ መዳንም መሞትም ይችላል፡፡ መውደቅም መነሳትም ይችላል፡፡

ነቢዩ ኢሳያስ፣ በዘመኑ ለነበሩት ሕዝብ (ዛሬም ለእኛ) የሚያስተላልፈው መልእክት ይህንን ነው፡፡

  1. እግዚአብሄርን ፈልጉት፡፡

ይህ ምን ማለት ነው? እግዚአብሄር በሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ እንዳለ መጽሓፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ የሚፈለግ ነገር፣ የት እንዳሌ በቀላሉ የማይታወቅ፣ በቀላሉ በአጠገባችን የማናገኝና ለማግኘት ትንሽ እንኳ ቢሆን የእኛን ጥረት የሚፈልግ ይሆናል፡፡ ታዲያ “እግዚአብሄርን ፈልጉት” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ይህ መልእክት የሚመክረን፣ ትኩረታችሁን ወደ እግዚአብሄር እንድንመልስ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ሊኖረን የሚችለውን ግንኙነት እንዳንጥለው፡፡ ሰው እርስ በእርሱን እንደሚፈልግ፣ ገንዘብን፣ ሃብትን፣ ዝናን ክብርን፣ ወዘተ. እንደሚፈልግ እግዚአብሄርን “ወዴት አለህ” ብሎ መጠየቅ ቢችል በሕይወቱ ትልቅ ነገር አድርጎአል ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሄርን መፈለግ” የራስን ደንነት፣ የራስን ደስታ፣ የራስን ዘላለም፣ የራስን ነጻነት መፈለግ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሄርን አለመፈለግ፣ በጠላት ፊት ትጥቅን እንደመፍታት ነው፡፡ ለሞትና ለስዖል ፈቅዶ ራስን እንደማስማረክ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ፣ “እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።” ተብሎአል (አሞ5፡6)፡፡

2. እግዚአብሄር የሚገኝበት ጊዜ አለ፡፡

ይህ የሚያሳየው እግዚአብሄር የሚጠፋበት ጊዜ ስለአለ ሳይሆን፣ እኛ እርሱን ለማግኘት ያለን ችሎታና ጊዜ የሚያልቅበት እንዳለ ለማሳየት ነው፡፡ ውድ አንባቢ ሆይ፣ አንተም/አንቺም አሁን ጊዜ አለህ/ሽ፡፡ አሁን፡፡ አሁን ማለት የሚትፈልገውን ለመጠየቅ፣ ለመጸለይ፣ ለማንበብ፣ ለመስማት፣ ለማሰብ፣ ለማስታወስ፣ ስትችል ማለት ነው፡፡ አሁን የሚባለው የጊዜ መቁጠሪያ በእጅህ እያለ፣ እግዚአብሄርን ፈልገው፡፡ አንቺም እህቴ እንዲሁ፡፡ ይህንን ሐሳብ ለመረዳት አንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ ማንብብ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ነገሮችን መቀየር ወይም ወደ ኃላ መመለስ የማይቻልበት ጊዜ አለ፡፡ የዛሬው ውሳኔአችን ደግሞ ዘላለማችን ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ።“በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ፦ አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። አብርሃም ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ።እርሱም፦ እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ። አብርሃም ግን፦ ሙሴና ነቢያት አሉአቸው እነርሱን ይስሙ አለው። እርሱም፦ አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ። ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።” (ሉቃ 16፡23-31)

ከዚህ መረዳት እንደምንችለው፣ ለጸሎት፣ ለንስሃ፣ ለምህረት፣ ለመመለስም ምቹ ጊዜ አለ፡፡ “ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፤ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም (መዝ 32፡6)፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ለእያንዳንዱ ሰው ተሰጥቶአል፣ ከሙሉ ነጻ ፈቃድ ጋር፡፡ ወደ እግዚአብሄር መመለስ የሚቻለው ደግሞ ሰው በሕይወት በምድር ላይ እያለና በቃሉ፣ በንስሓ ና በጸሎት እግዚአብሄርን መፈለግ ሲችል ነው፡፡ አሁን እግዚአብሄር ጸሎትን ለመስማት ቅርብ ነው፡፡ ፈቃደኛም ነው፡፡ እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፡፡ ዳዊት ልጁን ሰለሞንን ሲመክር እንዲህ ብሎት ነበር፣ “የአባትህን አምላክ እወቅ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው ብትፈልገው ታገኘዋለህ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል” (1ዜና 28፡9)፡፡

እግዚአብሄርን መፈለግ የሚገለጠው በቃል አይደልም፣ ግን በሙሉ ልብና በተግባር እንጂ፡፡ “የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም።” የሚል ተጽፎ አለና (መዝ 14፡2-3)፡፡ ስለዚህ “ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው” ይላል፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ ስንጀምር፣ ፈቃዱን መፈለግና ማድረግ እንጀምራለን፡፡ ስለዚህ እግዚዘብሄርን በመፈለግ ውስጥ፣ “ወደ አንቴ መልሰኝ”፣ “ከእኔ ምን ትፈልጋለህ?” ፣ “እንዴት ልሂድ?” ፣ “እንዴት ልኑር?” ፣ ወዘተ. በእውነት መጠየቅና መስማት አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ቃሉ ደግሞ በዚይ በኩል በጣም ያግዘናል፡፡ ያኔ እርሱ እግዚአብሄር በእውነት እንደሚገኝ ለሕዝቡ ቃል ገብቶአል እንደ ቃሉ ይገኝልናል፡፡ “እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ …” (ኤርም.29፡ 13-14) ።

በአድስ ክዳን ውስጥም እንዲህ ተብሎል፣ “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው” (2ቆሮ. 6፡2) ።

3. እግዚአብሄርን ቀርቦ ሳሌ ጥሩት፡፡

ሁሉም ነገር ሞት ነው፡፡ ሁሉም ነገር መጥፊያ ነው፡፡ ለሕዝቅኤል ሲናገር እግዚአብሄር ሕዝብ አላመለከም ብሎ አይደለም፣ ወይም ሃይማኖተኝነት ጠፋ ቢሎም አይደለም፡፡ ግን ደግሞ በእውነትና በመንፈስ እግዚአብሄርን ማምለክ አልነበረም፡፡ በሚታየውና በአደባባይ ለእግዚአብሄር የሚቀርብ የምልኮ ሥርዓት ነበረ፣ በጓዳና በልባቸው ግን ሌሎች ጣዖታት ይመለኩ ነበረ፡፡ የእግዚአብሄር ስም እየተጠራ አምልኮውና አገልግሎቱ ግን ለጣኦት ይደረግ ነበረ፡፡ እግዚአብሄርም፣ ልብን የሚመረምር አምላክ ሲለሆነ፣ ይህንን አይቶ ተጸየፈው፡፡ ይህ ህዝብ፣ እነዚህ አገልጋዮች፣ እነዚህ ካህናት፣ እነዚህ ነቢያት ከመቅደሴ ሊያርቁኝ ነው ይላል እርሱ፡፡ መቅደሱ የሌላ አይደለም፣ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቱና ወጉ የሌላ አልነበረም፣ ግን እግዚአብሄር ተገፍቶአል፡፡ ዛሬ ሕይወታችን፣ አገልግሎታችን፣ አምልኮና የአምልኮ ስፍራችን ምን ይመስላል? እግዚአብሄር የእርሱ ከሆነው ልባችነ፣ የእርሱ ከሆነው ጊዜአችን፣ የእርሱ ከሆነው ዝማሬዎቻችን፣ የእርሱ ከሆነው ስብሰባዎቻቸን፣ የእርሱ ከሆነው ሥርዓቶታችን፣ በረከቶታችን ተገፍቶ ይሆን፡፡ ከእግዚአብሄር ይልቅ እኛ፣ ወይም ሰዎች፣ ወይም ሌሎች “ጣዖቶቻችን” እየተመለኩበት ይሆንን?አሁን እግዚአብሄር አዝኖአል ግን ቅርብ ነው፣ ኃጢአት በስቶአል፣ ግን አሁንም ቅርብ ነው፣ እኛ ተሳስተናል ግን እግዚአብሄር ቅርብ ነው፡፡ እግዚአብሄር ቅርብ ነው፡፡ ጸጸት ብቻ፣ ወሬ ብቻ፣ መዝሙር ብቻ፣ ሥርዓት ብቻ በቂ አይደለም፡፡

ስለዚህ የሚያዋጣን በንስሃ መመለስ፣ በእውነት መጥራት ብቸኛ ነው፡፡ ያውም አሁን፡፡ አሁን፡፡ ቃሉ “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።” ይላልና (መዝ 145፡18)፡፡

ቃሉ እንዲህ ይላል፣ “እግዚአብሄርን ቀርቦ ሳሌ ጥሩት፡፡” እግዚአብሄር ከሄደ በኃላ በጥሪ አይገኝም፣ እግዚአብሄር ከተወ በኃላ ልቅሶ አይመልስም፣ እግዚአብሄር ከሄደ በኃላ ምንም ግብር አይመልሰውምና አሁን፣ እርሱ ቀርቦ ሳሌ፣ ጥሩት፡፡

ንስሓ አለመግባትና በሃጢአት መቀጠል እግዚአብሄርን ከእኛ እኛንም ከእግዚአብሄር ያርቃል፡፡ እግዚአብሄር ከመቅደሱ፣ ከሕዝቡ፣ ከአምልኮ ሲፍራ ከራቄ፣ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፡፡

“እርሱም (እግዚአብሄር)፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሚያደርጉትን፥ ከመቅደሴ ያርቁኝ ዘንድ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚያደርጉትን ታላቁን ርኵሰት ታያለህን? ደግሞም ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኵሰት ታያለህ አለኝ” (ሕዝ 8፡6) ።

ሰውንና እግዚአብሄርን የሚለይ ነገር ቢኖር ሓጢአት ነው፡፡ ኃጢአት ደግሞ ንስሃ ካልተገባበትና በእግዚአብሄር ምህረት ካልተደመሰሰ በስተቀር እያደገና እየበዛ፣ ስር እየሰደደና ከእግዚአብሄር እያራቀ ይሄዳል፡፡ ለሕዝቅኤል ይህ ተነግሮታል፡፡

4. ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ   

ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ። የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 3፡10-23)“እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።” (ኢሳ 55፡6-7)

ሐዋሪያ ጳውሎስም እንዲህ ብሎ አስተምሮአል፡-ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሲመሰክር፣ “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” ይላል (ሓሥ.3፡19-20) ።በዚህ የንስሃና የመመለስ ጥሪ ውስጥ የታመነና እርግጠኛ ልንሆንበት የምንችል ነገር ተነግሮናል፡፡ የእግዚብሄር ይቅርታ ብዙ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የተሰጠውን ጊዜ ተጠቅሞ ምላሽ የሚሰጥ ሁሉ ከእግዚአብሄር እጅ ብዙ ይቅርታ፣ ብዙ ምህረት እንደሚያገኝ ነው፡፡ ጥሪውን ለሚሰማ ሰው ሁሉ ወደ እግዚአብሄር ለመመለስ ፈቃደኛ ከሆነ፣ እግዚአብሄር በልግስና እንደሚምረው ይናገራል፡፡ “ይቅርታውም ብዙ ነውና”፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

 

by Teklu (18 01 2019)

 

One thought on “በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት

  1. ጌታ፣ይባረክ፣መልካም፣የቃል፣ትንታኔ፣ነው፣መረዳት፣በሚቻልበት፣ሁኔታ፣ነው፣ከምጠብቀው፣በላይ፣ነው፣በዚህ፣ቃል፣የተባረኩት፣ጌታ፣ይባርኮት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *