Sermons

ስለነፍስ የሚሠጥ ቤዛ

ስለ ነፍስ የሚሠጥ ቤዛ የለም፡፡ Mekane Yesus in Scotland,glasgow city, United kingodm. makaane Yesuus የወንጌል ሉቃ 6፡ 17-26

ስለ ነፍስ የሚሠጥ ቤዛ የለም፡፡

እርሱም (ኢየሱስ) ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና።  ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።  

ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና።  እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።”

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ህዝብ ባሉበት የተቸገሩ የሚጽናኑበትን ዘላቂነት የሌለው ደስታ ውስጥ ያሉ ደግሞ ማስጠንቀቂያ የሚያገኙበትን ንግግር በዚህ ክፍል ተናገረ፡፡ ስለ ነፍስ የሚሠጥ ቤዛ የለም፡፡

በዚህ ክፍል የምናያቸው ተሰብሳቢዎች “ከደቀ መዛሙርት ወገን” እንደነበሩ ጸሃፊው ሉቃስ ያስረዳል(ቁ17)፡፡ ይህ “የደቀ መዝሙር ወገን” ማለት ኢየሱስን የሚከተሉ ወይም ኢየሱስን መከተልን የማይቃወሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ የተቸገሩትን እየረዳ፣ የታመሙትን እየፈወሰ፣ ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩን ነጻ እያወጣና አጋንንት ካመጣባቸውም ስቃይም እየፈወሰ ነበረ፡፡ እየተደረገ ያለ የፈውስና የነጻ መውጣት ትርምስ መካከል ኢየሱስ ልባቸውንና ሕይወታቸውን ሰጥተውት እየተከተሉት ወዳሉት የራሱ ደቀ መዝሙርት ለመመልከት አይኑን አነሳ፡፡

ምንም አይነት ሁኔታና ግሪግር ቢኖርም ጌታ የእርሱ የሆኑትን አይረሳም፡፡ የውስጥ ችግራቸውንና ጮኽታቸውን ያዳምጣል፡፡ ለሃዘናቸውም ጌታ መልስና መጽናናት አለው፡፡

አንተም/አንቺም ኢየሱስን ለመከተል ወስነሽ ስትሳ/ነሺ በጌታ ልብ ውስጥ ገብተሻል፡፡ አስቀድሞውኑ የጸጋው መልእክት ከእርሱ መጥቶልሃል/ሻልና፡፡ ግሪግሮችም እንቺ እንዳትታይ አንተም እንዳትጎበኝ ምክንያት መስለው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ምናልባትየህዝብ ብዛት፣ የስራ ብዛት፣ የአጨብጫቢዎች ብዛት፣ የተከራካሪዎች ብዛትና ንቀት ወይም በሌሎች ዝሆን ዝሆን የሚያካክል አጀንዳ(ጥያቄ) ይዘው መነሳት፣ ያንተን ችግር/ሁኔታ ከመገንዘብ ሰውም እግዚአብሄርም የተከለከሉ ይመስላሉ፡፡

ግን እግዚአብሄር በጽድቅ ጠርቶሃል/ሻልና (ኢሳ 42፡6-7) አትረሳም፣ አንቺም አትረሺም፡፡

ብዙ የታመሙ ሰዎች ሲፈወሱ፣ ርኩሳን መናፍስት አስጮሄው ሲወጡ፣ ሌሎች ብዙዎች ደግሞ ኢየሱስን ነክተው ለመፈወስ ሲጋፉ፣ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ረሃብና ፊላጎት ትኩረት የሚሠጠው አልነበረም፡፡ በዚህ ክፍል ኢየሱስ ለስንት ሰዓታት ያክል ይህንን ብዙ ህዝብ እንዳገለገ አልጠቀሰም፣ ወይም ደግሞ ከስንት ሠዓት ጀምሮ እስከ ስንት ሰዓት እንደሆነ አልተገለጠም፡፡ ብዙ እልልታ፣ ብዙ ጫጫታ፣ ብዙ ደስታ፣ ብዙ ለቅሶ፣ ብዙ መጋፋት ብዙ ጥያቄም፣ ወዘተ. እንደነበረ መገመጥ አይከብድም፡፡

በዚህ መካከል ነው ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙረቱ እንዲህ አላቸው “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ።” (20-22)፡፡

ኢየሱስ ሊያረጋግጥላቸው የሚፈልገው ትልቁ ነገር፣ “የእግዚአብሄር መንግስት” የእነረሱ እንደሆነች ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መንግስት በማግኘት ውስት ትልቅ መጥገብ፣ ትልቅ በረከት፣ ትልቅ መጽናናት፣ ትልቅ ብጽዕናም አለ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስን በመከተላቸው ለሚደርስባቸው መገፋት፣ ሃዘን፣ ብቸኝነት፣ መራብ፣መጠማት ዋጋቸው ከንቱ እንዳልሆነ አውቀው በሚያልፉበት ሁኔታ ውስጥ በደስታ ችለው ማለፍ እንዳለባቸው ይመክራቸዋል፡፡

ከጊዜያዊ ሃብት፣ ጊዜያዊ ደስታ፣ ጊዜያዊ ሳቅ ና ጊዜያዊ አድናቆት ማግኘት ይልቅ ጊዜያዊ ችግራቸው፣ ጊዜያዊ ራባቸውና መገፋታቸው ዘላለማዊ ብጽዕናን ያስገኛልና፡፡

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን (ተከታዮቹን) ካጽናና በኃላ፣ ሌሎች በዚያ ቆመው የሚሳለቁ፣ የሚሳደቡ፣ የሚታዘቡ፣ ራሳቸውን ከተከታዮቹ እጅግ የተሻሉ ባለጠጎች አድርገው ለሚመለከቱ “ወዮላችሁ” አላቸው፡፡

ምክንያቱን ደግሞ ሲገልጥ፣ እነረሱ ለነገ ተስፋ የላቸውም፣ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ራሳቸውን አያገኙትምና ከዘላለማዊ በረከት፣ ደስታና ሠላም ጋር ተላልፈዋል፡፡ በኢየሱስ አስተያየት ይህ ዓይነቱ በጊዜያዊ ደስታ ዘላለምን መቀየር ወዮታ የሚገባው ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ትልቅ ድህነት ነው፡፡ ሰው ለነፍሱ የዘላለም ሕይወትን ከማግኘት የሚበልጥ ነገር ሊያገኝላት አይችልምና፡፡ በአንደበቱ ሲናገር ኢየሱስ እንዲህም ብሎ ነበር “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማቴ 16፡26) ፡፡

ኢየሱስን መከተል የራስን ነፍስ ማትረፍ ነው፡፡ ግን ከኢየሱስ ይልቅ ሌላውን ለማግኘት ከኢየሱስ መራቅ ነፍስን ማጉደል ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ እያለን ነው “ስለ ነፍስ የሚሠጥ ቤዛ የለም፡፡ የራስን ነፍስ ጥሎ ሌላ ሁሉ ትርፍ ማግኘት አስከፊ ክሳራ ነው፡፡”

የኢየሱስን ቃል ሰምተህ/ሽ ታዲያ ምን ማድረግ ይገባኛል በለህ ከሆነ፣ ከእግዚአብሄር መንግስት ሩቅ አይደለህም፡፡ አሁኑኑ ኢየሱስን ወደ ሕይወታችን መጋበዝ አለብን፡፡ ስለሓጢአታችንም ይቅርታ መጠየቅ፡፡ ከዚህም ጊዜ በኃላ ኢየሱስን ከሌላው አስበልጠን ለመከተል የሚያስችል ጸጋን ከእግዚአብሄር መለመን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

 

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *