SermonsTeachingsUncategorized

መሸከም አትችሉም

ቢነገራቸው መሸከም እንደማይችሉ ኢየሱስ ያውቅ ነበረ፡፡ye cannot bear them now. “12 የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14 እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15 ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።”ዮሓ 16፡12-15

መሸከም አሁን መሸከም አትችሉም (ዮሓ 16፡12-15)

“12 የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14 እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15 ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።”

ጌታችን ኢየሱስ ይህንን ቃል በሚናገርበት ጊዜ በዚህ ምድር ላይ ያለውን (በአካል የሆነ) አገልግሎቱን ወደ መፈጸምና ወደ መሞት ደርሶ ነበር። ኢየሱስ ወደ አባቱ ለመሄድ መቃረቡንም ግልጽ አድርጎ ለተከታዮቹ ነገራቸው፡፡ የመሄዱን ዜና ሰምተው ልባቸው ለታወከና የፈሩትን ተከታዮቹን ለማጽናናት፣ ለማበረታታት እና እርሱ የሰጣቸውን ተስፋ እንዲጠብቁ ለማድረግ በዚህ ክፍል የምናነበውን መልዕክት ነገራቸው፡፡

ኢየሱስ በቃሉ ዓለምን ለወጠ

ጌታ ኢየሱስ በዚህ ምድር መጥቶ የዓለምን መልክና ሁኔታ ለዘላለም የቀየረ አገልግሎት በጥቂት አመታት ውስጥ አገለገለ፡፡ በዚህ ምድር ያልታወቀውን ግን በእግዚአብሄር ዘንድ ብቻ የሚታወቁ ብዙ ነገሮችን ከሰዎች ጋር አስተዋውቆ ብዙዎችን አስደንቆም ነበር፡፡ ኢየሱስ ያደረገውም ሆነ የተናገራቸው ነገሮች እስከዛሬ በምድርቱ ላይ ብዙ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አምጥቶአል፡፡ አሁንም እያመጣ ነው፡፡ ድነት፣ ፈውስ፣ ከአጋንንት ነጻ መውጣት፣ የኃጢአት ይቅርታ እና ከእግዚአብሄርና ከሰዎች ጋር ለየት ያለ ግንኙነቶች ተፈጥሮአል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ስደት፣ ልዩነት፣ መልካቸውን የቀያየሩ ጸረ-ኢየሱስ እንቅስቃሴዎች በምድርቱ ላይ ተፈጥሮአል፡፡ እነዚህ ሁሉ ደግሞ እንደሚፈጠሩ ኢየሱስ ራሱ ተናግሮ ነበረ፡፡
ቢሆንም ግን ኢየሱስ በራሱ የአገልግሎት ጊዜ ሁሉንም ነገር ተናግሮና አድርጎ አልሄደም፡፡ ምንም እንኳ ሲናገር የሰዎችን መስማማትና አለመስማማት እያዬ ሰዎችን ብቻ ለማስደሰት ባይናገረም፣ ከሰዎች የመረዳት አቅም ጋር ግን እያመዛዘነ ይናገር ነበረ፡፡ መሸከም በሚችሉት ልክም ይናገራቸው ነበር፡፡

ኢየሱስ ሰዎችን ከእውነት ጋር ለማስተዋወቅ መሸከም በምችሉት መጠን ያስተምር ነበር

ልጆቼ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ እኔ እንደአባት መመለስ ሲሞክር በተቻለ መጠን እየተጠነቀቅሁና መረዳት በምችሉት መጠን ነው የማደርገው፡፡ ልክ አባት ለልጆቹ እንደምጠነቀቅ፣ ጌታ ኢየሱስም ሲያገለግል በነበረበት ጊዜ ለሰሚዎቹ እየተጠነቀቀ ያስተምር ነበረ፡፡ በዘመናችን እንደምንሰማውና (ምናልባትም እንደምናደርገው) ሰሚዎችን ግራ የሚያጋቡ ብዙ የስነ-መለኮት ትምህር ቃላት ወይም በሌላው ዓለም ቋንቋ አልተጠቀመም፡፡
የሚናገራቸውን አስፈላጊ ጽንሴ-ሓሳቦችንም እንኳ ሲናገር ኢየሱስ ወደ ሰሚዎች የመረዳት አቅምና የእለት ተዕለት ተግባር አምጥቶ ይገልጠው ነበረ፡፡ መሸከም በሚችሉት መጠን፡፡ ስለዚህ ነው በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች ከዓሳ ማጥመድ/ማስገር፣ ከእርሻ ልማት፣ ከንግድ ሥራ፣ ከጌታና ከባሪያ ግንኙት፣ ከወቅቶችና የአየር ሁኔታ መለዋወጥ፣ ከቤት/ሕንጻ ግንባታ፣ ከመጠጥ ውሃ፣ ከሕክምና አገልግሎት፣ ከጦሪነቶና ከቤተሰብ አስተዳደር፣ ወዘተ. ጋር ተያይዞ የተነገረው፡፡ ሰማያዊውን ምስጥር ወደ ሰዎች የመሸከምና የመረዳት አቅም ለማምጣት፡፡

ኢየሱስ በትምህርቱ ውስጥ ከሚጠቀማቸው የቃላት መሰካካት ይልቅ፣ መተላለፍ ያለበት መልእክቱን በትክክል ወደ ሰዎች ልብና ጆሮ ማድረስ ዓላማው አድርጎ ሠራ፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ ኢየሱስ “በአድስ ቋንቋ” እንኳ ተናግሮአል የሚል ቃል ተጽፎ አናገኝም፡፡ ትምህርቱ፣ ስብከቱ፣ ምክሩ፣ ትዕዛዛቱ፣ ወይም አደራረጉ በነበሩት ሰዎች የቋንቋ ልክ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ መሸከም ከምችሉት በላይ አልተናገራቸውም፡፡

ይህንን ሲል ግን ኢየሱስ የተናገረውንና ያስተማረውን በሙሉ ተከታዮቹም ሆነ ሌሎች ሰዎች በትክክል ተረድተውታል ማለት አይደለም፡፡ መሸከም መቻልና መረዳት የተለያየ ነው፡፡ ብዙዎቹ የኢየሱስን ትምህርት ሲሰሙ፥ አንዳንዱን እንደ መልካም ሓሳብ ብቻ፣ አንዳንዱን እንደ ፍልስፊና፣ ሌላውን ደግሞ ቀድሞ በሚያውቁት ሓይማኖታዊ እና ማህበረሰዉዊ እውቀታቸው ጋር አያይዘው እና አገናዝበውት አለፉ፡፡

ኢየሱስ ሲናገር ለወደፊትም ነበረ

ራሱ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ አንዳንዱን ሓሳብ ወዲያው ለሰሚዎች መረዳት ጋር እንደማይስማማ እያወቀ ግን ወደፊት፣ ከጊዜ በኋላ፣ ከልምምድ በኃላ፣ ነገሮች ከተከሰቱ በኃላ እንሚመረዱት እያሰበ ይናገር ነበረ፡፡ ለምሳሌ፣ ከመሞቱ በፊት እራት አዘጋጅቱ ስለሥጋውና ስለደሙ ሲናገር፣ እግራቸውን ሲያጥብ በቀላሉ ለሰሚዎች የሚገባ አልነበረም፡፡ ስለትንሳኤውም ሲናገር እንዲሁ፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስም ሲናገር እንዲሁ፡፡ በኋላ ግን ለሰሙትና ላዩት እጅግ ጠቃሚ ነበር። “ሌካ እንዲህ ብሎ የነበረው ለዚህ ነው” እንዲሉም አድርጎአቸዋል፡፡

ኢየሱስ ሁሉን ነገር ለራሱ ተናግሮ አልሄደም።

ደቄ መዛሙርቱን ሲልክና የመንፈስ ቅዱስ መምጣትን ተስፋ ሲሰጥ፣ ኢየሱስ ለእነርሱ ያስቀረ አገልግሎት ስለነበረ ነው፡፡ ኢየሱስ የመጣበትን የራሱን አገልግሎት ሲጨርስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሊሠሩ ያሉትን ትልልቅ ሥራዎች እንዳሉ ያውቅ ነበረ፡፡

ሊመጣ ስላለው ነገር ቢነገራቸው ደቄ መዛሙርቱ መሸከም እንደማይችሉ ኢየሱስ ያውቅ ነበረ፡፡ ኢየሱስ ይህንን በሚናገርበት ጊዜ፣ ደቄ መዛሙርቱ የሚያስቡትና ነገሮችን የሚያዪበት መነጸር በለመዱትና በተማሩት የአይውድ ህግና ስርዓት ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ሊሆን ያለው የቤተክርስቲያ አሠራርና የወንጌል ሥራ መልክ ደግሞ ከለመዱት ውጪ ስለሚሆንባቸው ሊገባቸውም ሊቀበሉትም ስለማይችሉ፣ ሊሆን ስላሉት አንዳንዶች ነገሮች ጠለቅ ብሎ አልነገራቸውም፡፡ መሸከም በምችሉት መጠን ነግሮአቸው ሌላውን ስራ ለመንፈስ ቅዱስ ተወ፡፡

እኛም ዛሬ በክርስቲና ሕይወታችንና በአገልግሎችን ጉዞ ላይ እያለን (ወይም ስንጀምር) ሁሉን ነገር አውቀን አይደለም፡፡ ለመነሻ ያህል የሚበቃንን ያክል ብቻ ያለን ይመስለኛል፡፡ በየደረስንበት ቦና ሁኔታ ግን መንፈስ ቅዱስ በምሪቱ እያቀናን፣ እየገሰፀን፣ እያጽናናንና እና መንገድ እያሳየን የምናደርጋቸውና የምናልፍባቸው ሁኔታዎች አሁንም አሉ፡፡ አንዳንዶቹን ሁኔታዎች፣ ከመጀመራችን በፊት አውቀናቸው ቢሆን በራሳችን እንደማናልፋቸው ስለምናውቅ ጉዞውን ሁሉ የምንጀመር አይመስለኝ፡፡

መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ለማክበር፣ ለእየሱስ ካለው ወስዶ ሊነግረን ለቤተክርስቲያን ብሎም ለእያንዳንዱ አማኝ የተሰጠ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተነሳ ወንጌል አሁን እየተሰበከ ባለበት ደረጃ እየተሰበከ ይገኛል፡፡ ችግሩ ግን ልክ ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ጊዜ እርሱ በመካከላቸው ሲመላለስ የነበሩቱ አይውድና አለም በሞላ ኢየሱስን በትክክል አውቀው እንዳልተቀበሉት ሁሉ፣ እኛም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለን እንደሚገባ እየሰማነው ነው ? “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡” ብሎአል ጌታ ኢየሱስ፡፡

ይህንን በማለቱ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት መቀበልና እርሱን መስማት የኢየሱስን ፈቃድ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም “እርሱ ኢየሱስ ካለው ወስዶ” ይነግረናልና፡፡ በሌላ ጎኑ ደግ ለአብ ያለው የኢየሱስ ነው፣ የኢየሱስ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ መስማት የእግዚአብሄር አብ ድምጽን መስማትም፣ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ድምጽ መስማትም ነው፡፡ እኛ በአብ በወልድ በመንፍስ ቅዱስ አንድ አምላክ እናምናለንና፡፡ ወልድ አብን አክብሮአል፣ አብም ወለድን አክብሮአል፣ መንፈስ ቅዱስም ወልድን ያከብራል፡፡

ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት

ስለ መንፈስ ቅዱስ ስንናገር መንፈስ ቅዱስን በየትኛው ልክ እንደምናስብ ነው፡፡ እንደ ሃይል፣ እንደነፋስ፣ እንደ ልሳን ፣ እንደ ትንቢት ቃል፣ ወይስ እንደመለኮቱ ነው? እግዚአብሄር ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ ያስፈልጉናል፡፡ ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስን እንደ እግዚአብሄነቱ፣ እንደ ኤልሻዳይነቱ እናውቅ ይሆን? ኢየሱስ በመካከላቸው እያለ ሰዎች በትክክል አላወቁትም (ዮሓ.1:10)፣ ደቄ መዛሙርቱም በብዙ ግራ መጋባት ውስጥ የገቡበት ጊዜ ነበረ፡፡ እኛም ዛሬ መንፈስ ቅዱስን በትክክል አውቀነው ይሁን፡፡ ከፈውሱ፣ ከትንቢቱ፣ ከአድስ ቋንቋው ባሻገር እርሱን በእርሱነቱ አውቀን እንደሚገባው እናምልከው፣ እንስማው፣ እንከተለው ሄሆን?፡፡

አንዳንድ ጊዜ እነጴጥሮስን ስንወቅስ፣ “ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በመርከብ እያለ…” እንዳይሞቱ ስለመፍራታቸው እንናገራለን፡፡ ዛሬ እኛስ መንፈስ ቅዱስ እንደተሠጠን የተስፋ ቃል ከእኛ ጋር እያለ፣ ለምን እንፈራለን? ለምንስ በሁኔታዎች ውስጥ ተስፋ እንቆርጣለን? ስለመገኘቱስ ረስተን ብቸኞች እንደሆንን ለምን ራሳችን እንቆጥራለን? ጌታ ከእኛ ጋር ነው፣ እኛም እርሱን ዘወትር መታመንና መታዘዝ አለብን፡፡ ጌታ ይርዳን፡፡

በዘወትር ሕይታችንና አገልግሎችን ለመንፈስ ቅዱስ በመታዘዝ የኢየሱስን ፈቃድ እያደርግን እንድንኖር እግዚአብሄር ይርዳን፡፡ ጌታ አቅማችንንና ምን ያክል መሸከም እንደምንችል ያውቃል፣ ከአቅማችን በላይም ምንም አያሸክመንም (1ቆሮ 10፡13)፡፡ ስለእኛ ይጠነቀቃል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ግን በደረስነበት ደረጃና ሁኔታ፣ ያላወቅነውን እየገለጠልን፣ ከፈቃዱ ጋርም እያስተሳሰረን ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ለዛሬና ለሚመጣው ማንኛውም ሁኔታ መንፈስ ቅዱስን መጠበቅ፣ እግዚአብሄርን መታመንና ቃሉን መስማት እጅግ ይበጀናል፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *