Sermons

ልጆች ይጠይቃሉ

ልጆች ከሚያዩት ነገር ተነስተው ይጠይቃሉ፣ ይፈጥራሉ፣ እይታቻውና በምናባቸው ስእሎችን ይስላሉ፡፡ እነዚህም ሁሉ ተያያዥነት አላቸው፡፡

ልጆች ይጠይቃሉ

“እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጥና፦ በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው ብለህ እዘዛቸው አለው። ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች ያዘጋጃቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ።” (ኢያሱ 4:1-4)

“ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን እነዚያን አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አቆማቸው። ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን፦ እነዚህ ድንጋዮች ምንድር ናቸው? ብለው ሲጠይቁ፥ ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ፦ እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻገረ፤ እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ። ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድትፈሩ ነው፡፡” (4:20-23)

ልጆች ከሚያዩት ነገር ተነስተው ይጠይቃሉ፣ ይፈጥራሉ፣ እይታቻው ይቃኛል በምናባቸውም ስእሎችን ይሥላሉ፡፡ እነዚህም ሁሉ ተያያዥነት አላቸው፡፡

ልጆች ቃላትን መማር የሚጀምሩት በወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ዘንድ ተደጋግሞ በሚነገር፣ በቤታቸውም ሆነ በአከባቢአቸው ካለው፤ ከሚሰሙትና ከሚመለከቱት ነገር ተነስተው ነው፡፡ ቃላትን ብቻ ሳይሆን ጽንሴ-ሓሳቦችንም እንዲሁ፡፡ ትውልድን የሚነገራቸው ታሪክ (ተረቱም ሆነ እውነተኛው) ይቀርጻቸዋል፡፡

ስለዚህ አከባቢና በዓይን የሚታዩ ነገሮች በትውልድ ላይ የሚያመጣውን ነገር የተረዱ የተለያዩ አካላት በዘመናት ውስጥ ትውልዶችን የራሳቸው ለማድረግ በብዙ መልኩ እየሰሩ ነበሩ፤ ዛሬም እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ዛሬም ተንቀሳቃሽም ሆነ ተንቀሳቃሽ ባልሆኑ ስእሎች በመጠቀም፣ በጌሞች፣ በአሻንጉልቶችና በሙዝቃዎች ትውልድ ገና ክፉና ደጉን ሳያውቅ እነርሱ የሚፈልጓቸውን ነገሮች (ሓሳቦችና ፍልስፍናዎች) ያስተምሩአቸዋል፡፡ ልጆችም ገና ከልጅነት የእነርሱን ታርክ መናገር፣ መዘመር፣ ማሰብ፣ መለማመድና ያንንም መሠረት አድርገው መጠበብ ይጀምራሉ፡፡

ለልጆች እውነተኛ ታሪክን ያቆይ ዘንድ እግዚአብሄር ኢያሱን ጠየቀ፡፡ ኢያሱም መልእክቱን ለሕዝቡ፡፡

በልጆች አከባቢ ያለውም ሰው ትልቁ ሥራው ልጆቹን አከባቢአቸው ካለው፣ ከሚሰሙትና ከሚያዩት ነገሮች ጋር የማስተዋወቅ፣ የማገናኘትና በልጆች አይእምሮ ውስጥ ተበጣጥሰው የሚፈጠሩትን ሥእልሎች መልክ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች እነዚያን ተበጣጥሰው በልጆች አእምሮ ያሉትን ስእሎች ማግኘት ቀላል አይደለምና በተገቢ መልኩ መርዳት ይሳናቸዋል፡፡ በቴሌቪዥን፣ በጌሞች፣ በአሻንጉልት፣ በፍልም፣ በጎረቤት ልጆች፣ በትምህርት ቤት ጓደኞች፣ በአስተማሪዎች፣ በወላጆች፣ ከቤት ሲወጡ ከሚያዩአቸው ነገሮች እንደተበጣጠሴ ካሪታ በአእምሮአቸው የተመጡትን ስእሎችን የሚያገናኙ ልጆቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በየጊዜውና በየቦታው በሚያገኙት መረጃ መሠረት ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ነገሮች የሚገናኙበት መንገድ፣ የልጆቹን ዓለም (እይታ) ይፈጥራሉ፡፡

ወደ መጽሓፍ ቅዱስ ስንመለስ፣ እግዚአብሄር በብዙ ቦታ ወላጆች ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የሚናገሩትን ታሪኮች ለሕዝቡ ይናገር ነበረ፡፡ በተለይ እርሱ አምላክ እንደሆነና እንዴት አድርጎ እንደረዳቸው፡፡ በሙሴ ይህ ተነግሮአል፣ (ዘጸ.12፡26-27) “እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፦ ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው? ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ፦ በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ።” በተጨማሪም ዘጸ.13፡14፤ ዘዳግ 4፡9፣ 6፡20፤ 6፡20፤ መዝ 78፡2-4 ማንበብ ይቻላል፡፡

ልጆች (ወይም ትውልድ) ይማርበት ዘንድ የእግዚአብሄር ህዝብ እንዲያደርጓቸው ከተጠየቁት ነገሮች ማካከል ማውራት፣ በዓላትን ማክበር፣ መሣል/ መጻፍ፣ መታሰቢያ ሐውልቶችን ማቆም፣ ወዘተ. ይገኙበታል፡፡ በነቢዩ ኢዩኤል ሲናገር (1፡3)፣ “ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ።”

በኢያሱ መጽሓፍም ስናነብ እንዲህ ይላል፡- “ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን እነዚያን አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አቆማቸው።” (4፡20)

ለምን እነዚያ አስራ ሁለቱ ድንጋዮች? ለምን በገልገላ? ድንጋይ ማቆም ምን መንፈሳዊነት አለው? እነዚህንና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎች በዚህ ስፍራ ሊነሱ ይችላሉ፡፡

በእርግጠኝነት መናገር የሚችለው ነገር ቢኖር ግን እግዚአብሄር የነገውን ትውልድ ለራሱ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በዛሬው ትውልድ ተሞክሮና ልምምድ ለቀጣይ ብዙ ትውልድ ዘንድ የሚታወስነበትንና የሚታወቅበትን ቅርስ እንድናስቀምጥ ይፈልጋል፡፡

አሁን ያለው ትውልድ ተለዋዋጭ እንደሆነ እግዚአብሄር ያውቃል፡፡ አብዛኛው ከግብጽ የወጣው ትውልድ በመንገድ ላይ ቀርቶአል፡፡ ሌሎች ደግሞ የእግዚአብሄርን ውለታና አደራረግ ረስተው አጉረምራሚ ሆነዋል፡፡

እግዚአብሄር ግን ራሱን ያለ ምስክርነት መተው አይፈልግም፡፡ እርሱ ራሱን ሊክድ አይችልምና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአድስ ክዳን የተናገረው ነገር አለ፡፡ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” (ሉቃ 19፡40)፡፡ ሰዎች ዝም ቢሉ፣ ተከታዮች ዝም ቢሉ፣ የተጠሩት ዝም ብሎ፣ መልእክት የተሰጣቸው ዝም ቢሉ እግዚአብሄር ድንጋዮች የእርሱ ሥራ እንዲናገሩ ከዘመናት በፊት ሰርቶባቸዋል፡፡ ድንጋዮቹ የ ሰው ስም፣ ዝና፣ እውቀት ወይም ዘመን ሳይበግራቸው እውነቱን ለሁሉም ይናገራሉ፡፡

ውድ ወገኖቼ፣ እኛ ስለእግዚአብሄር ዝም ብንል፣ እግዚአብሄር የሚናገርበት መንገድ አለው፡፡ ግን እኛ ደግሞ ብንሰማውና በእርሱ መንገድ ብንሄድ ለራሳችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ ትውልድም የድንጋይን ድምጽ ከሚያዳምጥ የመሰሉን የሰውን ድምጽ ብሰማ ይሻለዋል፡፡

ቃሉ “ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። ቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” ይላልና (ዘዳግም 6:7-9)

ብዙ ጊዜ እኛ ዛሬ ስለሆነልን፣ ዛሬ ስለተባረክንበት ነገር፣ ዛሬ በስሜት ተቀስቅሴን ስለምንናገረው ነገር ብቻ እንደነቃለን፡፡ ለትውልድ አሳቢ የሆነው እግዚአብሄር ግን ከትውልዱ ይልቅ በድንጋዮች የታመነ ይመስላል፡፡

ምክንያቱም ድንጋዮች በተቀመጡበት ይቆያሉ፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ ግን ብዙ ጊዜ ስፍራውን ለቆ ይሄዳል፡፡ አምላኩን በሌሎች ጣኦታት እስከ መለወጥ ድረስ፡፡ ሕዝብን የሚያስታውሱ ድንጋዮች ከዮርዳኖስ እንዲወሰዱ እግዚአብሄር አዘዘ ትውልድ፣ ይጠይቃል፡፡ ልጆች ይጠይቃሉ፡፡

ስለዚህ ኢያሱ ሲመራቸው ከነበረው እስራኤል መካከል 12ሰው ድንጋይ ይዞ ይሄዳል፡፡ አንዱን ድንጋይ ለአንድ ነገድ አድርጎ አስቆሙአቸው፡፡

እግዚአብሄር ድንጋዮቹ እንዲቆሙ ሲያስደርግ የተናገረው፣ “በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን፦ እነዚህ ድንጋዮች ምንድር ናቸው? ብለው ሲጠይቁ፥ ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ፦ እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻገረ” እንዲሉ ነበረ (ኢያሱ 4፡21-22)፡፡

ሕዝብ ሁሉ የሚያውቀው ታሪክ ቢሆንም ቶሎ መረሳቱ እንደማይቀር ጌታ ያውት ነበረና፣ መታሰቢያ ድንጋይ እንዲቆምለትና በዚያም በትውልድ ዘንድ እንዲታወስ አደረገው፡፡

በዘመናችንም እንደምናየው ትልልቅ ዜናዎች የአንድ ወቅት ወሬ ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ግን የዘላለም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በአንድ ወቅት እውቅና አግኝቶ በሌላው ደግሞ የሚቀየር ጣኦት አይደልም፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ እግዚአብሄር የሚመጣውን ትውልድ ሳይኮሎች ወይም ስነ-ልቦና ያውቃል፡፡ የሚመጣው ትውልድ ብዙ ጥያቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ በቃል የሚተላለፍን ታሪክ በድንጋይ ማመሳከር የሚፈልግ ትውልድ ነው፡፡ ይህ በእኛ ዘመንም እውነት ነው፡፡

ብዙ የአርኪዎሎጂ ስራዎች እየተሰሩ ያሉት “በድንጋዮች” ላይ ናቸው፡፡ ከቦታቸው ባልተንቀሳቀሱት፣ ባሉበት ቦታ በተቀበሩት፣ የጥንት መልክና ድዛይን ባለባቸው፡፡ እግዚአብሄር አዋቂ ነው፡፡

እንግድህ ትውልድ ይጠይቃል፡፡ ልጆቻችን፣ የልጅ ልጆቻችን ይጠይቃሉ፡፡ በአንድ ጎን አይተው፣ ሰምተው ጥያቄ መጠየቅ የሚችሉበትን ነገር ምን እያስቀረን ነው? በሌላ ጎኑ ደግሞ ሲጠይቁ ምን መልስ እንሰጣቸዋለን? ብሎ መጠየቁ አይከፋም፡፡

ነገስታት የራሳውን ታሪክ ያቆያሉ፣ የነገስታት ቤተሰቦችም እንዲሁ፡፡ ገንዘብ፣ ጊዜና የፖሌቲካ ሥልጣን ያላቸው የራሳቸውን ምልክትና ከራሳቸው ፍልስፊና ጋር የሚሄድ ነገር ብቻ እንዲሰማ፣ እንዲነገር፣ እንዲመዘገብ ይፈልጋሉ፡፡ የጥንቱንም ነገር ሳይቀር በዛሬው አስተሳሰብ ለመቀየር የሚደረጉ ሙከራዎች ብዙ ናቸው፡፡

ስለዚህ ትውልድን ከእግዚአብሄር ጋር የሚያገናኝ፣ ስለእግዚአብሄር እንዲሰማ፣ ስለእግዚአብሄር እንዲጠይቅ፣ ሃይሉን እንዲያውቅና እንዲፈራው ከኢያሱ ትውልድ 12 ሰዎች ከዮርዳኖስ የወጡ ድንጋዮችን እስከ ገልገላ መሸከም ነበረባቸው፡፡

እግዚአብሄር ጠያቂ የሆነ ትውልድ ሲነሳ ተገቢ መልስና ማስረጃ ማግኘት እንዳለበት ተናግሮአልና፡፡

“እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ። ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድትፈሩ ነው፡፡” (ኢያሱ4፡23-24)

ይህም ማለት ያያችሁትን ተዓምር ያደረገው አምላችሁ ነው፡፡ ሕያው አምላክ አላችሁ፡፡ ይህ የማሻገር ተዓምር ለአምላካችሁ ለእግዚአብሄር የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህን ቀደምም አድርጎ ምስክሮች የሆንን እኛን አለው ማለቱ ነው፡፡

ኢያሱም ይህንን እውነት ትውልዱ እንዲያውቅ ያሳስባል፡፡ አድሱ ትውልድ የእግዚአብሄርን ክንድ እንደ ተረት ተረት ብቻ ይመለከተው ነበርና ኢያሱ፣ ይህ የተደገመ ታሪክ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

የዚህ ሁሉ ድካምና ድንጋይ መሸከም ወይም መትከል ዓላማው

  1. የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች እንዲታወቅ እና
  2. እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድፈራ ነው፡፡

እግዚአብሄርን አለማወቅ ብዙ ወደ መዳፈር ይወስዳል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ አደጋ አለበት፡፡

ስለዚህ ኢያሱ በመልእክቱ ውስጥ እግዚአብሄርን እወቁ፣ አሳውቁ፣ አትርሱት፣ ታመኑት፣ ፍሩት፣ ለትውልድም አስተላልፉት እያለ ነው ማለት ነው፡፡

እኛም እንዲሁ እንዲናደርግ እግዚአብሄር አምላክ በጸጋው ይርዳን፡፡

 

ተክሉ ጃንዋሪ 8 2018

 

በተክሉ ጃንዋሪ 8 2018

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *