Sermons

በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን

በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን Glasgow city, Mekane Yesus congrigation, Scottish Ethiopians church, EECMY, ECMYIS, Mekane Yesus in Scotland, Mekane Yasus, Ethiopian Church in Glasgow, Scotland, Ethiopian Christina Community, Evangelical Church, Lutheran chuch in Glasgow, Scotland. we meet in St George's Tron Church, Church of Scotland, city center. Christian family, infant baptism is also practiced here. Eritrean Christian church from Lutheran chuch of Eritrea. 1 Samuel 30: 1-6

በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን

መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 30

1 “እንዲህም ሆነ፤ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በደቡብ አገርና በጺቅላግ ላይ ዘምተው ነበር፥ ጺቅላግንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፤

2 ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፤ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር።

3 ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ።

4 ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ።

5 የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር።

6 ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቈጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ።”1ሳሙኤል 30፡1-6

 

ቁ.6 “ነገር ግን ዳዊት በእግዚብሄር ልቡን አበረታ፡፡”

የክፍሉን አውድ

የክፍሉን አውድ ስንመለከት፣ ጊዜው ዳዊት (ንጉስ ለመሆን ታጭቶ ለነበረው ወታደር ማለት ነው) እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና የጥያቄ ጊዜ ነበረ፡፡ በሁሉም የተተወበት ጊዜ፡፡ ያገኘው ሁሉ ሊገድለው በሚፈልግበት ጊዜ ውሰጥ ሆኖ በአምላኩ በእግዚብሄር ልቡን አበረታ፡፡ ሁሉም ጭልምልም ባለበት ሰዓት ውስጥ አሁን አይኑን መትከል የሚችለው በእግዚአብሄር ላይ ብቻ ነበረ፡፡

ሁሉም ሲሄድ እግዚአብሄር ግን ቀሪ ረዳተችን፣ ቀሪ አለኝታችን፣ ቀሪ ዘመዳችን፣ ቀሪ አፍቃሪያችን ነው፡፡

አጠቃላይ ታሪኩን ስንመለከት፣ ጊዜው ከማናቸውም ጊዜ ይልቅ ለዳዊት የዝቅታ ጊዜ ነበረ፡፡ ይህ የዝቅታ ጊዜ ከመምጣቱ በፊት፣ ዳቂት ብዙ መልካም ነገሮችና የከፍታ ጊዜያት በሕይወቱ ላይ ተራቸውን እየጠበቁ ያልፉ ነበረ፡፡

ለምሳሌ ፡- ከልጅነቱ ጀምሮ ተደጋጋሚ ድሎችን በዱር አውረዎች ላይ በመቀዳጀቱ ከብዙ መበላቶች ድኖ፣ በጎችንም ከማስበላት አድኖ ነበረ፡፡ ይህ ብቻ ደግሞ አይደለም፤ እግዚብሄርን ማምለክ፣ ማመስገንና በእርሱ ላይ መደገፍ በሕይወቱ ውስጥ እለት በእለት ያድግ ነበረ፡፡ ይህም ትልቅ ድል ነው፡፡ በአምላኩ በእግዚብሄር ልቡን አበረታ፡፡

የእግዚብሄር ዓይኖች ስላዩትና ልቡም ስላረፈበት፣ በሕዝቡ ላይ ንጉስ ይሆን ዘንድ እንዲቀባው እግዚአብሄር ሳሙኤልን ላከበት፡፡ ዳዊት በሀገሩ ከነበሩት ሌሎች ሰዎችና ከወንድሞቹ በልጦ የተገኘውን በሌላ በምንም ሳይሆን በልቡ ነበረ፡፡ ልቡ ለእግዚአብሄር ተመችቶት ነበረ፡፡ በአምላኩ በእግዚብሄር ልቡን ጥሎአልና፡፡

በኢየሱስ ስም የእኔና የእናንቴ ልብ ለእግዚአብሄር ይመች፡፡

እንዴት ነው ልቡ እንዲህ የተመቸው?

አይኑን ጨፍኖ በእግዚአብሄር የሚታመን ይመስላል፡፡ በዚህ እምነት አንበሶችን፣ ድቦችንም መናቅ ተለማመደ፡፡ ከዚህም እምነት የተሳ ነው ማንም ማመን እስከሚያቅተው ድረስ እብደት በሚመስል ድፍረት ዱላና ወንጨፍ ይዞ ጦረኛውን ጎሊያድን ገጠመ፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ባለው እምነት ጎለያድንና እርሱ የሚታወቅበትን ማንኛውንም ነገር የናቀው፡፡ ጠላትን መናቅ ብቻ ግን በራሱ እምነት አይደለም፤ በእግዚአብሄር መታመንና የእርሱን ትልቅነት መደገፍ ደግሞ እንጂ፡፡ በአምላኩ በእግዚብሄር ልቡን ልቡን አበርትቶአልና፡፡

ሰው ከፍ ያለውን እግዚአብሄርን ሲያይና ሲታመን ብቻ ነው ግዙፉን ጠላቱን በባዶ እጅ ለማሸነፍ የሚገጥመው፡፡

ሌላው የዳዊት የከፊታ ልምምድ፣ ጎለያድን ከገደለ በኋላ ዳዊት ብዙ ዝና አገኘ፣ ከተራው ሰው እስከ ቤተ መንግስት ድረስ እውቅና አገኘ፡፡ ሰቶች ዘፈኑለት፣ ንጉሱ ሳኦልም ልጁን ዳረለት፡፡ በሃላም ንጉስ ሳኦል በወታደሮቹ ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾሜው፡፡

ለሚያይና ለሚሰማው ሰው አሁን ዳዊት ለመንገሥ በቂ እንዲሆነ ማሰብ ቀላል ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ንጉሱ ሳኦል ራሱ ዳዊትን ሲመለከት ስጋት ስጋት፣ ፍርሃት ፍርሃት ይለው፣ ዝቅተኝነትና መሸነፍ ይሰማው ነበረ፡፡ ለዚህ ነው አጋጣሚ ፈልጎ ሊገለው ሙከራ ያደርግ የነበረው፡፡ ሙከራዎቹ ሁሉ አልተሳኩለትም፡፡

የክፉ መንፈስ የሞት ወረ

ሆኖም ግን አነዚህ የንጉሱ ሳኦል የመግደል ሙከራዎች በዳዊት ላይ ተጽኖ ማድረግ ጀመረ፡፡ ምናልባትም ሳኦልን ያስጨንቀው የነበረው ክፉ መንፈስ ዳዊት ጆሮ ላይ የሞትን ወረ ማቃጨሉ አልቀረም፡፡ “አንድ ቀን ትሞታለህ”፣ “በሳኦል እጅ መሞተህ አይቀረ ነው”፣ “ዛሬ አመለጥከው እንጂ ነገ ያገኝሃል”… ብቻ ያቃጭላል፡፡ “ዳዊትም በልቡ፦ አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ፤ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፤ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲሁም ከእጁ እድናለሁ አለ።” (1ሳሙ 27፡1)

እንደ ሰውም ሲታሰብ እንደዚህ አይነቱ ነገር ለማንኛውም ሰው ማሳሳቡ አይቀረ ነው ብየ አስባለው፡፡ በአምላኩ በእግዚብሄር ልቡን ከማበርታት የሚከለክለው ነገር ተፈጠረ ማለት ነው፡፡

ይህ ወሬ ዳዊት የዱር አራዊቱንም ሆነ ጎሊያድን የገጠመባቸውን እምነት፣ የተቀባበትንም ጸጋና በእርሱ ላይ በተነገረውን ቃል ላይ የነበረውን እምነት እየሸረሸረው የመጣ ይመስለኛል፡፡

ስለዚህ ዳዊት እንደዱሮ ጭፍን እምነቱን ሳይሆን እንደ ወታደር በተለይ ደግሞ በአከባቢው በተለመደ የማምለጫ ዘዴዎችን በእምነቱ ላይ ጨምሮአል፡፡ ሸሽቶ ራስን ማዳንና ዋሽቶ መኖር የሚባሉ ከችግር መውጫ ዘዴዎችን ከእምነቱ በተጨማሪ ወስዶታል (አዶፕት አድርጎአል) ፡፡ በአምላኩ በእግዚብሄር ልቡን ከማበርታት ይልቅ በራሱ ብልሃትና ስልት መጠቀም ጀመረ፡፡

ስለዚህ ወደ ጠላት ሃገር (ወደ ፍልጥኤም ሀገር) ሸሼ፡፡ በዚያም በየቀኑ እያታለለና እያጭበረበረ ይኖር ጀመር (27፡8-12)፡፡ በአቀራራቡም የዚያን ሀገር ንጉስ እንኳን አሳምኖት ነበረ (29፡6-9)፡፡

የንጉሱ ወታደሮችና አለቆች ግን የውትድሪና ሕይወትና ፍልስፊና ሲለሚያውቁ፣ ዳዊትን ንጉሳቸው እንዳመነው አድርጎ ማመን አልቻሉም (29፡4)፡፡ በጣምም ጠሉት፡፡ አንድ ቀን የእስራኤልን ሕዝብ ለመውጋር ፊልስጥየሞች ስሰለፉ ዳዊትም አብሮአቸው ተሰለፈ፡፡ የፊልስጥኤም የጦር አለቆች ግን አልወደዱትምና ዳዊት ከሰልፊፉ ወጥቶ እንዲሄድ ንጉሳቸውን ጠየቁት (29፡6)፡፡ ንጉሱ አንኩስም ደግሞ ወታደሮቼና አለቆቹ ስላልፈለጉህ ወደ ሰፈርህ ህድ ብሎ መለሰው፡፡ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ወታደሮች አዝነው ተመለሱ፡፡

ትልቅ ውድቀትና ሽንፈት ቢመሰስልም መጨረሻው ግን ጠቃሚ

ይህ ደግሞ ለጊዜው ለዳዊት ትልቅ ውድቀትና ሽንፈት ቢመሰስልም መጨረሻው ግን ጠቃሚ ነበረ፡፡ እግዚአብሄር በራሱ ህዝብ ላይ ሰይፉን ከማንሳት ከልክሎታልና፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዚያኑ ወቅት አማሌቃውያን ዘምተውባቸው ነበርና፣ የእርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ቤቶች ተቃጠሉ፡፡ ልጆቻቸው፣ ምስቶቻቸውም ፣ ከብቶቻቸውም ሁሉ በአማሌቃውያን ተወሰዱ፡፡ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ “ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ” (1ሳሙ 30፡4)፡፡ በኋላም በድንጋይ ሊወግሩት ሁሉም ተነሱበት፡፡ “ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቈጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ” (ቁ 6)፡፡ ነገሮች ሁሉ እየከፉበት ሄዱ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የዘማሪ ተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙር ያስታውሰኛል፡፡

“ወሬው ሁሉ የሚያስራ፣

የሚሆነው በዓለም ዙሪያ፣

እየከፋ ሲሄድ ግዜው

መሸሸጊያዬ ኢየሱስ ነው”

ከከበቡት መካከል ነፍሱ ሾልካ ወደ እግዚአብሄር ጠጋ

እንግድህ ሰብሰብ አድርገን ስንመለከት፣ ዳዊት ሳኦልን ስፈራ ወደ ጫካ ስገባ፣ ሊያግዙት የተጠቀላቀሉት ሰዎች ነበሩ፡፡ ስዴቱ ስበዛ ወደ ፍልጢኤም ሀገር ስደተኛ ሆነው ገቡ፡፡ አሁን ግን የቅርብ ወዳጆቹ ሳይቀሩ ድንጋይ አንስተዋል፣ በተሰቡ ተወስዶአል፡፡ ለዳዊት ከእግዚአብሄር ውጭ ምንም አልቀረለትም፡፡ ስለዚአህ ድንጋይ ይዘው ከከበቡት መካከል ነፍሱ ሾልካ ወደ እግዚአብሄር ጠጋ አለች፡፡ በእግዚአብሄርም ላይ ልቡን አበረታ፡፡

እግዚአብሄርም አስቀድሞውኑ ይህንን ያውቅ ነበርና ለዳዊትና ከእርሱ ጋር ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰብ ጥንቃቄ አደረገላቸው፡፡ “ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር (ቁ2)”

ወገኔ፣ ሁኔታዎችን አይተይ አሁንስ ጊዜው አልፎአልና ለምን እጸልያለሁ፣ ለምንስ እታመናለሁ አትበል፡፡ እግዚብሄር አዋቂና ሁሉን የሚችል አምላክ ነው፡፡

ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ። በእግኢአብሄር መታመኑን መልሶ አገኘው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ለመስማማት ጊዜው አሁን ነው፡፡ እኛ “አሁን” የምንለው የፍርሃትን ጊዜ፣ የዝቅታን ጊዜ፣ የብቸኝነትን ግዜ፣ የድካም ግዜ፣ በብዙ ጠላቶች የመከበብ ጊዜ፣ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን እግዚአብሄር ሊሰማን፣ ሊረዳን፣ ሊያግዜን፣ ከገባንበት ክፉ ነገር ሊያወጣን የተዘጋጀበት ጊዜ ነው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

“እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።

አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።” (ኢሳ 55፡6-9)

ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አንዳበረታ፣ እኛም ወደ እግዚአብሄር እንመለስ፣ በእርሱ አንታመን፣ እርሱም ይረዳናል።

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

(በወንድም ተክሉ ፣ ሴፕተምበር 24፣ 2017 -ለግላስጎ መካነ የሱስ ምዕመን ከቀረበው)

 

የዕለቱን መጽሓፍ ቅዱስ ንባብ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *