SermonsUncategorized

እግዚአብሄርን ማስገረም

እግዚአብሄርን ማስገረም አይቻልም፡፡ መካነ ኢየሱስ, መካነ የሱስ በስኮትላንድ, እጅህ ንጹህ አይደለም, No surprise!, ስብከት በተክሉ , የግላስጎ አመኞች, የእግዚአብሄርን ጸጋ አልጥልም, እሬ እኔ ማን ነኝ, ያንስብሃል ምስጋናዬ ያንስብሃል ጌታ, ምህረት የበዛለት , Amazing grace, saved by grace, Mekane Yesus, ECMYIS, Mekana Yasus in Scotland, Glasgow christians, Evangelical chuch in glasgow, wash your hand, hand washing

(እግዚአብሄርን  ማስገረም አይቻልም፡፡ )

“እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥ ንጉሡ ነቢዩን ናታንን፦ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው።” (2ሣሙ 7፡1-2)

 

ንጉሱ ለእግዚአብሔር አዘነ

ንጉሱ ዳዊት በዙሪያዉ የነበሩት ጠላቶችን ሁሉ ከአሸነፈና ግዛቱን ካስከበረ ቦሃላ የራሱን ቤተመንግስት አሰራ። ዳዊት በዚህን ግዜ ትላልቅ የሚባሉ ስራዎችን ያጠናቄቀ ይመስላል ። ሆኖም ግን ዳዊት የአምልኮ ሰዉ ስለነበር ለአምልኮ ወደ መገናኛ በድንኳኑ ሲሄድና ሲመለስ የቃል ክዳኑ ታቦት በድንኳን (በመጋረጆች) ተቀምጦ በማየት ሃፍረት የተሰማው ይመስላል።

እግዚአብሔር ለዳዊት ብዙ ውሌታዎችን ውሎለታል። ባለ ብዙ ድልም አድርጎታል። አሁን ዳዊት የስቃይና የስደት ዘመን አልፎ፣ ነግሶና መንግስቱም ተደላድሎ፣ ከዝግባ የተሰራ ቤት እና ቤተመንግስት አለው። የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን (በመጋረጆች ውስጥ) ተቀምጦ ይገኛል። በዚሁም ምክንያት ዳዊት ለእግዚአብሔር አዘነ እና የእግዚአብሔር የቃል ክዳን ታቦትን ከነበረበት ድንኳን ማውጣት ፍላጎት አደረበት።

 

እግዚአብሄርን  ማስገረም

በዚህም ዳዊት ደግሞ በተራው ባለውሌታውን እግዚአብሔርን በተግባሩ ማስደነቅ ፈለገ። ያውም እግዚአብሔር ሳይጠይቄው በራሱ ፈቃደኝነት ተነሳስቶ የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ ለመስራት በመነሳቱ። ይህ ያሰበዉ ነገር ተቀባይነት ይኖረው እንደሆን ለማወቅ ዳዊት ነብዩ ናታንን አማከረ። የዳዊት ሓሳብ ነቢዩን ደስ አሰኝቶታል። ግን እግዚአብሔር በዚህ ሓሳብም ሆነ በነቢዪ ምክር ደስ የተሰኜ አልነበረም፡፡”አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም” አለው፡፡ እግዚአብሄርን  ማስገረም አይቻልም፡፡

ቁ. 3-6 “ናታንም ንጉሡን፦ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው።

በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው፦ ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም።”

(ቁ 12-13) ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ።እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።”

አንዳንድ ጊዜ ጥሩ የምንላቸውም ሰዎች፣ ነቢያትን ጨምሮ፣ ከእግዚአብሄር ሀሳብ ጋር የማይሄድ ሀሳብ ሊያመነጩ ይችላሉ፡፡ ለሰዎች ሲቀርብ በጎ ሆኖ የሚታዩትን ሓሳቦታችንን እግዚአብሄር ግን ላያጸድቅልን ይችላል፡፡

ነቢዩ ናታን በጣም እርግጠኛ የነበረበትና እግዚአብሄርም በተናገረው ያጸናው እግዚአብሄር ከዳዊት ጋር ስለመሆኑ ነው፡፡ ግን በዳዊት ልብ ስለነበረው ነገር እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ በነቢዩ ኤርሚያስ መጽሓፍ እንደምናነበው የሰው ልብ ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል፣ ይላል፡፡እግዚአብሄር የሰውን ሁሉ ልብ ይመረምራል፣ ያውቀዋልም፡፡ ቢሆንም ግን በሰው ልብ ያለውን በሙሉ ለነቢያቱም ቢሆን አይገልጥም፡፡ ስለዚህ ናታን በዳዊት ልብ ስላለው ነገር ሁሉ እርግጠኛ ሆኖ “በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ” ማለት አልነበረበትም፡፡ በዳዊት ልብ ውስጥ ኩራትም፣ ፍረሃትም፣ ዝናም፣ ስንፍናም፣ ወዘተ. ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በሌሊት ተገልጦለት፣ ነቢዩ ቶሎ ለዳዊት የመከራትን ምክር እንዲያነሳ ጠየቀው፡፡

ሰው በእግዚአብሄር ሃሳብ ውስጥ ገብቶ ሲያስብና እንደ እግዚአብሄር ቃል ሲያቅድ፣ ሲመክር እና ሲሠራ ብቻ ሥራውና አላማው በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ስለማግኘቱ እርግጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ፀሎትና ከእግዚአብሄር ጋር ጊዜ መውሰድ የእግዚአብሄርንም ቃል ማወቅ የሚያስፈልገው ለዚያ ነው፡፡

ነቢዩ ናታን ከዳዊት ከሰማ በሃላ ወዲያው የነበረው መልስና ጊዜ ወስዶ ከእግዚአብሄር ከሰማ በሃላ የሠጠው መክር የተለያዩ ናቸው፡፡ እንዲያውም የሚቀራረኑ፡፡ የነቢዩ ትልቅነት ግን፣ ‹እኔ አንዴ ስለተናገርኩ እግዚአብሄር የነገረኝን ቢናገር በንጉስ ዘንድ ውሸታም እባላለሁ› ብሎ ከመታዘዝ እምቢ አላለም፡፡ ነቢዩ ናታን የቀደመችውን የራሱን ምክር አፍርሶ በኃላ የመጣውን የእግዚአብሄርን ሃሳብ አስተናገደ፡፡ እግዚአብሄርን መስማት ማለት እንዲህ ነው፡፡

እግዚአብሔር መቅደሱ በዳዊት እጅ እንዲሰራ ፈቃደኛ አልነበረም። ለዚህ የዳዊት የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ምላሽ እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር በአጭሩ ለመመልከት እንሞክራለን።

  1. የእኔ ጥያቄ አይደለም። ቁ 7 “ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን?” እግዚአብሄር አስቀድሞ ከሕዝቡ የጠየቀው ልባቸውን እንዲሠጡትና በእውነት እንዲያመልኩት እንጂ ሕንፃ እንዲገነቡለት አልነበረም፡፡ እግዚአብሄር የሕዝቡ አምላክ መሆን ይፈልጋል፡፡ መቅደስ መስራት በኃላ የሚመጣ ነው፡፡ ከልብ መሠጠት በኃላ፣ ከእግዚአብሄር ከሰሙ በሃላ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ስለዚህ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ እግዚአብሄር ሕዝቡን ወደ ራሱ የመምራት ፍላጎትና ጥያቄ ነበረው፡፡ እነርሱን ወደ እውነተኛ አምልኮ በማምጣት ላይ እንጂ በሕንጻ ግንባታላይ ጥያቄ አላቀረበላቸውም፡፡ ዘለዋ. 26፤ 3-12 “… ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።” በእርግጥ ለወደፊቱ የመቅደስ መሠራት በእግዚአብሄር ልብ ውስጥ ነበረ፣ በዳዊት ግን አልነበረም፡፡ ዳዊትም እንዲሠራው አልተጠየቀም፡፡ ስለዚህ ዳዊት በእግዚአብሄር ልብ ውስጥ ያለውን ማግኘቱ መልካም ሆኖ እያለ፣ ጊዜውን ግን አላወቀም፡፡
  2. አንቴ አታስገርመኝም። ዳዊት ለእግዚአብሄር ያስፈልገዋል ያለውን ተረድቶ ቶሎ በመሥራት እርሱን ለማስገረም የተነሳ ይመስላል፡፡ እዚህ እንደሚባለው፣ “ሳርፕራይዝ!” ሊለው፡፡ ልብን የሚያውቅ እግዚአብሄር ግን፡- አንቴ አታስገርመኝ፣ እኔ ግን አስገርሜሃለሁ ደግሞም አስገርምሃልሁ። ቀድሜህ ያቀድሁትን አሳዉቅሃለሁ። የዘላለም እቅድ በአንቴና በቤትህ ላይ ነው፡፡ አሁን የሆንከውን ሰው ያደረግሁህ እኔ ነኝ። አለው፡፡ በዚህ ግዜ እንግዲህ፣ ዳዊት የእግዚአብሄርን ቤተ መቅደስ ሊሠራበት የተነሳበት በራስ የመተማመንን ስሜት የሚያፈርስ ነገር ተፈጠረ፡፡ እግዚአብሄርን በምንም ማስገረም አይቻልም፡፡ ለእግዚአብሄር የምንሰራው እርሱ ባቀደልን መሰረት እርሱ ራሱ በሠጠን ፀጋና ሥጦታ ተጠቅሜን ስለሚሆን በራሳችን ጊዜና ሀብት ሠርተን የምናመጣለት ነገር የለንም፡፡ እግዚአብሄርን  ማስገረም አይቻልም፡፡

በአድስ ክዳን እንዲህ ተጽፎአል፣ “ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።” (1 ጴጥ 4፡11) No surprise!

    3. ቤቴ በንጹህ እጅ ይሠራል። ዳዊት ፍላጎቱ፣ ገንዘቡ፣ ስልጣኑና የሰው ጉልበት ስላለው ብቻ የእግዚአብሄርን ታቦት ከድንኳን ሊያወጣ አሰበ፡፡ እጁን ግን መታጠብ እንዳለበት አላወቀም፡፡ እግዚአብሄር ምህረት አደረገልን ማለት፣ በንስሓና በፍረሃት በእግዚአብሄር ፊት መቅረብ የለብንም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ይቅር ለማለት አንድ አፍታ ይበቃዋል፡፡ እኛ ግን ከልምምዶቻችን ለመውጣት ጊዜያት ያስፈልጉናል፡፡ እግዚአብሄር መቅደሱን እንዳይሰራ የከለከለበትን ምክንያት ለልጁ ስመሰክር፣ “ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ፦ ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም።”(1 ዜና 22፡7-8)እግዚአብሔር የሚቀርብለትን መስዋዕት ብቻ ሳይሄን መስዋዕቱን የሚያቀርቡ ሰዎችን ልብና እጅ ይመለከታልና ለዳዊት “እጅህ ንጹሕ አይደለም” አለዉ።

  1. ከዚህ የምንማረው፣ እግዚአብሄር ኃጢአተኛውን ጻድቅ ነው የማይል ነገር ግን ይቅርባይና መሃሪ አምላክ እንደሆነ ነው፡፡
  2. እግዚአብሄር የእጅንና የልብን ንጽሕና እንደሚፈለግ ዳዊት በዚህ ስፍራ ከእግዚአብሄር ተምሮአል፡፡ በመዝሙሮቹም ስለዚህ ነገር ዘምሮአል፡፡ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።” “አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።… እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።” (መዝ 51፡1-10)
  3. እግዚአብሄር ለዳዊት “ያንቴ እጅ ደም አለበት” አለው። ጦረኛ እጅ ሳይሆን ንጹህና ጥበበኛ እጅ በስሜ የሚጠራውን ቤት ይሰራልኛል አለው።

በዚህ እግዚአብሔር ምን እያለ ነው? አንቴ ሓጢአተኛ ነህ። እኔ አውቅሃለው። አንቴ ከየት እንዳመጣሁህ ሳይቀር ረስተሃል። ግን ፀጋዬ ለዚህ አድርሶሃል። በቀጣይነትም ከአንቴና ከዘርህ ጋር በምህረቴ የሚሰራቸው ስራዎች አሉኝ። ከልጅህም ጋር የሚሠራው በምህረቴ ነው፡፡ ስለዚህ ዳዊት በስከትና በዕረፍቱ ጊዜ የነበረውን የግንባታ ሃሳብ ተጠቅሞ እግዚአብሄር ራሱን ወደ ማየትና ወደ ምስጋና መራው፡፡ ዳዊትም ስለተነገረው እውነት በነቢዩም ሆነ በእግዚአብሄር ላይ ሲያጉረመሪም አናይም፡፡ ግን ቁጭ ብሎ የምህረቱንና የቸርነቱን ብዛት መቁጠርና ማመስገን ጀመረ፡፡

ወገኖቼ፣ ስኬት ወደ ምስጋና እንጂ ወደ ኩራት እና በራስ ላይ ብቻ ወደ መተማመን ሊወስደን አይገባም።

እግዚአብሄር ለዳዊት ኃጢአተኝነቱን ብቻ አሳይሆቶ አልተወውም፡፡ ግን ደግሞ ከቀድሞ በሚበልጥና ዳዊት ፈጽሞ በማይጠብቀው መልኩ እርሱንና ከእርሱ በሃላ የሚነሱትን ልጆቹን እንደሚያስገርም ነገረው፡፡

የመቀመጥ ግዜም ያስፈልጋል፡፡

ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት (በመገኘቱ ውስጥ) ተቀመጠ። በዚያም ሆኖ ትክክለኛ ማንነቱን እና የእግዚአብሔርን ቸርነት ማሰብ ጀመሬ። እግዚአብሔር ልብን እንደሚያውቅም ተረዳ።

ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድር ነው? ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ ስለ ባሪያህም ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው።ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድር ነው?” (2 ሣሙ 7 ቁ 18-20)

ከአመታት በኃላም ልጁን ሰለሞንን ሲመክር “እግዚአብሔር ልብን ይመረምራልና በፍጹም ልብህ አምልከው ” ብሎ ነበር ።

እኛም አንድ አንድ ጊዜ እግዚአብሔርን ቁጭ አድርገን የእርሱን ሥራ በራሳችን ለመስራት እንጥራለን፡፡ መስራት ክፉ ባይሆንም እግዚአብሔርን የውሌታች ባለዕዳ ለማድረግ ማሰባችን ግን ችግር ነው።

ቁጭ ብለን ማንነታችንን እና የእግዚአብሔርን ቸርነት ለማሰብ ጊዜ መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡

ሞት ተፈርዶበት እያሌ ከዚያ አስመልጦት በህይወት ያኖረውን ጌታ ንጉሥ ሆኖ ማገልገል ላይ የሚገኘው ዳዊት እግዚአብሄርን ባለእዳ ማድረግ ይችላል ወይ? እኛስ ብንሆን፣ እግዚአብሄር ሳያደርግልን፣ ለእግዚአብሄር የምናቀርበው ነገር ምን ይኖረናል?

እግዚአብሄርን በማመን ያገኘውን ጽድቅስ ጥለን/ረስተን ነገሮችን በራሳችን፣ በጉልበታችን፣ በገንዘባችን፣ በትምህርታችን፣ ወዘተ. ማሰብ ጀምረን ይሆን? ሓዋሪያው ጳውሎስ ለገላቲያ ሰዎች ሲጽፍ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

“ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።

ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና።

እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።

የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።” (ገላ.2፡ 17-20)  እግዚአብሄርን  ማስገረም አይቻልም፡፡

ስለዚህ እኛም በእግዚአብሄር መገኘት ውስጥ በመቀመጥ በእኛ ላይ የበዛውን፣ የዳንበትንም የእግዚአብሄርን ጸጋ እና ምህረት፣ በጎነትና ቸርነት እናስብ፡፡ እግዚብሄርን እናመስግን፡፡ እግዚአብሄር የእኛን መንገድና ሃሳብ እምቢ ብለን፣ እኛን ስለጠላን አይደለም፡፡ እርሱ እኛ ካሰብነው ቀድሞ ሁሉንም ነገር አቅዶና ወስኖአል፡፡ እኛ ግን ሁልጊዜ ከእርሱ እየሰማን፣ እየታዘዝን፣ በተሳሳትንበት ንስሃ እየገባን የመታዘዝና የምስጋናን ኑሮ መኖር እንድንችል እግዚአብሄር ይርዳን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ

 

በተክሉ

 

 

 

 

 

 

ineManNegn.png

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *