Sermons

እርሱን ስሙት

እርሱን ስሙት::ኢየሱስን አለመስማት ለሰው ልጅ ሕይወት ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ስለዚህ ነው “እርሱን ስሙት፡፡” የሚል ድምጽ የመጣው፡ecmyis, Mekane Yesus in Scotland, Glasgow Mekane Yesus, Lutheran chuch in Glasgow, Evangelical Christian chuch in Scotland, Glasgow, Amharic Service, Afan Oromo, Tigrigna and Enlsih Bible daily verses. Sundy service

ሉቃ 9፡28-36 (እርሱን ስሙት :-ያለንበትን የከበረ ጊዜ እናውቀዋለን?)

28 ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 29 ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ። 30 እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ 31 በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር። 32 ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። 33 ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። 34 ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። 35 ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። 36 ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም።

 

በዚህ ክፍል ወስጥ መመልከት የምንችላቸው ብዙ ቁልፍ ቁልፍ ሃሳቦች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ

1.       ኢየሱስ ይፀልይ ነበረ፡፡

ጸሎት ማለት ከእግዚአብሄር ጋር መነጋገር ማለት ነው፡፡ ችግራችንን፣ ምስጋናችንን፣ ስጋታችን፣ ፍርሃታችንን፣አምልኮአችንን ይዘን ወደ እግዚአብሄር የምንቀርብበትና እርሱም የምናገረንን ከምንሰማበት አንዱ መንገድ ነው፡፡

በመጽሃፍ ቅዱሳችን ውስጥ ኢየሱስ ደጋግሞና ምሳሌዎችን ወስዶ ካስተማራቸው ትምህርቶች የጸሎት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ኢየሱስ ስለጸሎት ያስተማረው በመናገር ብቻ ሳይሆን አዘውትሮ በማድረግም ነው፡፡

ኢየሱስ ሕዝብ ባሉበት፣ ደቀ መዛሙርት ብቻ ባሉበት፣ ከደቀ መዛሙርትም መካከል ጥቅቶች ብቻ ባሉበት፣ እንዲሁም በአብዛኛው ደግሞ በግሉ ይጸልይ እንደነበረ ከቅዱሱ መጽሓፍ እናነባለን፡፡

ኢየሱስ ስለ ጸሎት ሲያስተምር ከፈተና ማምለጫ፣ ከገቡበት ችግር መውጫ፣ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የሚፈልጉትን ነገር ማግኛ፣ ለዳግም ምጽአጽም መዘጋጃ መንገድ አድርጎ ነበረ፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ጸሎት ራስን ማዋረድም ነው፡፡ ኢየሱስ በአባቱ ፊት ዝቅ ብሎ ሲቀርብ፣ ቅዱሳን ከሰማያት ወረዱ፣ አብም ሊያከብረው በደመናና በድምጽ ተገለጠ፡፡

ኢየሱስ መጸለይ ከነበረበት እኛስ ምንኛ አብዝተን መጸለይ ይኖርብን ይሆን?

ለሕይወታችን፣ ለቤተሰቦቻችን፣ ለአገልግሎታችን፣ ለሕዝቦቻችን፣ ለሀገሮቻችን ጸሎት አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ኢየሱስ የአገልግሎት ባልደረቦቹን ከመምረጡ በፊት ከአባቱ ጋር ተነጋገረ (ጸለየ)፡፡

በገተሰማኔ ሆኖ የመጨረሻውን ፀሎት ሲጸልይ፣ ደቀ መዛሙርቱ ግን ሲተኙ አይቶአቸው “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፡፡” አላቸው፡፡

2.       ሲጸልይ የኢየሱስ መልክ ተለወጠ ልብሱም ተብለጭለጨ

በዚህ ክፍል ውስጥ ኢየሱስ እየጸለዬ እያለ፣ መልኩ/ፊቱና ልብሱ እንደ ተለወጡ እናነባለን፡፡ ይህም ኢየሱስ የነበረውንና ደግሞም የሚጠብቀውን ክብር ለደቀ መዛሙርቱ ለመግለጥ ሲሆን ለራሱ ደግሞ ሊመጣበት ያለው መከራ የሕይወቱ መጨረሻ እንዳልሆነም የሚያሳይ ነው፡፡

3.       ሙሴና ኤልያስ መጥተው ኢየሱስን አነጋገሩት

ሙሴና ኤልያስም የተገለጡት በክብር ነበረ፡፡ በኢየሱስ ፊት ስላለው መከራና ክብር አነጋገሩት፣ በመከራውም አጽናኑት፡፡ ሙሴ አገልግሎቱን ከጨረሰ ቦሃላ ሲሞት እግዚአብሄር እንደቀበረው መጽሓፍ ቅዱስ ላይ ተጽፎአል (ዘዳ 34፡5-6)፡፡ ኤሊያስ ደግሞ በስዴትና በመከራ የተሞላ የነቢይነት አገልግሎቱን ከጨረሴ በሃላ እግዚብሄ እንደወሰደው በመጽሃፍ ቅዱሳችን እናነባለን (2ነገ 2፡11-18)፡፡

ሁለቱ ሰዎች (ሙሴና ኤልያስ) የህግና የትንቢት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሃጢአተኛ ሃጢአተኝነቱን እንዲያውቅ የሚያደርገው ህግ በሙሴ ሲሠጥ፣ በሓጢአት ምክኒያት ደግሞ ሰዎችን ስለሚያገኝ መከራና ቅጣት እንዲሁም በእግዚአብሄር ምህረት ስለሚመጣው ቤዛነት የተናገሩት ነቢያት ነበሩ፡፡ አሁን ሁለቱም ለእየሱስ እየመሰከሩና በእየሱስ ፍጻሜ እንደሚያገኙ እያመለከቱ ነው፡፡

 

“አብርሃም ግን፦ ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው። እርሱም፦ አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ። ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።” (ሉቃ 16፡29-31)

4.       እነጴጥሮስ በክብር መገለጫ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶባቸው ነበረ

በሰው ሕይወት ውስጥ ብዙ አጋጣሚዎችና ዕድሎች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዱ ግን በጣም አስገራሚና መልሰን ልናገኘው የማነችል ልሆን ይችላል፡፡ በዚህ ኣይነቱ ብርቅዬ አጋጣሚ በአግባቡ አለመጠቀም እንዴት ይቆጫል?

እነጴጥሮስ ሙሴና ኤልያስ መጥተው ኢየሱስን ሲያነጋግሩት በዚያ ነበሩ፣ ግን እንቅልፍ ከብዶባቸው በኃላም ፍርሃት ወሮአቸው ነበርና በውል የሚናገሩትንም የማያውቁበት ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡

እስቲ እንበልና ጴጥሮስ፣ ዮሃንስና ያዕቆብ በንቃት ሆነው ያንን ክስተት ቢከታተሉት ምን ይሆን ነበረ?

  • ምናልባት የኢየሱስ መከራና ሞት የእግአዚብሄር አጀንዳ ውስጥ ያለና መሆን ያለበት ነገር መሆኑን ስለሚረዳ ጴጥሮስ የሰውን ጆሮ ባልቆረጠ ነበር፣ ወይም ክህደት ውስጥ ባልገባ ነበር፣ ወይም ደግሞ ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳም በሃላ ስፍራውን ለቆ ባልሄደ ነበር ብለን መገመት እንችላለን፡፡ እነዚህና ሌሎች አሳዛኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጴጥሮስ ሕይወትና ታርክ ውስጥ ጠባሳ ባልተው ነበረ፡፡ እኛም ጴጥሮስን አሁን በምናውቀው መልኩ ባላወቅነው ነበረ፡፡
  • ምናልባት ስለዚያች ጊዜና ሁኔታ አሁን ከምናውቀው በበለጠ አይተውና ሰምተው ይጽፉልን ይሆን፣ ያጽናኑንም ይሆን?
  • ምናልባት ስለሙሴና ኤሊያስ፣ ከዚህ ምድር ሕይወት ከተላቀቁ በሃላ ስለሚኖሩት ኑሮ የበለጠ ታሪክ እንሰማ ይሆን?

በእርግጥ አብዛኛው መረጃ ስለማያስፈልገንና ለደንነታችን ወሳኝ ስላልሆነ እንዳልተመዘገበ አስባለሁ፡፡ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ራሱ መልሶ ለእነርሱና ለደቀ መዛሙርቱ በተናገረ፣ በገለጠ ወይም ደግሞ ክስተቱን በደገመ ነበርና፡፡

ግን ደግሞ በእግዚአብሄር መገኛ ቦታና ጊዜ ውስጥ ሆነው “ምን እንደሚናገሩ እስከማያውቁ” ድረስ በእንቅልፍ መሸነፍ ምንኛ ምስክንነት ነው፡፡ ክብሩ ከብዶቸው፣ ሃይሉ በርትቶውባቸው ቢሆን መልካም ነበረ፡፡ አሁን ግን እንቅልፍ ከብዶባቸው ተገኙ፡፡

በዚህ ላይ የእኔ ዓላማ ጴጥሮስና ዮሓንስ እንዲሁም ያዕቆብ መክሰስ ወይም መውቀስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትልቁ ቁምነገር ለእኛ የሚሆን ትምህርት ከዚህ ውስጥ ማግኘት ነው፡፡

ከማናቸውም ጊዜ የበለጠ፣ በጸጋ ጊዜ ውስጥ አለን፡፡ በብዙ የእግዚአብሄር ምህረትና መልካምነት፣ በጸጋው በሚሠጡ የተለያዩ ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ስጦታዎች ተከበን አለን፡፡ ጌታን ከፈለግነው ለማግኘት በካህናት ወይም በመላዕክት በኩል መቅረብ ወይም የበግ ጠቦት፣ ኮርማ ወዘተ.ማቅረብ አያስፈልገንም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተከፈተ በር ሠጥቶናል፣ “ለምኑ ይሠጣችሁሃል፣ ፈልጉ ታገኛላችሁ፣ መዝጊያውን አንኳኩ ይከፈትላችሁሃል” ብሎ፡፡ “በስሜ የምትለምኑትን አብ ይሠጣችሃል” ብሎም መክሮአል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፣ ለበደልነው በደል ምህረት፣ ላጠፋነው ጥፋት ይቅርታ ተትረፍርፎ አለ፡፡

ይመራን፣ ያስተምረን፣ ይገስጸን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ተሠጠን፡፡ በብዙ ጸጋና የእግዚአብሄር በጎነት የተባረክን ትውልድ ነን፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ሁሉ በረከትና ሥጦታ፣ በዚህ ትልቅ ዕድልና ጊዜ በአግባቡ እየተጠቀምን ይሆን?

ስንቶቻችን በዚህን ጊዜ እንኳ ኃጢአት ከብዶን እንኖራለን፣ ስንቶቻችን በዚህን ጊዜ ስንፍናና “እንቅልፍ” ከብዶን የምንናገረውንና የምናደርገውን እስከማናውቅ ድረስ እንቅልፍ ተጫጭኖናል?

እያዬን የማናይ፣ እየሰማን የማንሰማ፣ ጌታ ከእኛ ጋር እያለ የማናስተውል፣ ግን በእንቅልፍ ልብ የምንቀባጥር ጌታም የምታዝበን ስንቶች ነን?

ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።” (ቁ 33)

ኢየሱስ፣ ኤልያስና ሙሴ ስለኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት (ወደ ጎልጎታ ስለመሄድ)፣ ስለኢየሱስ ለሰው ልጆች ሁሉ መሞት ይነጋገሩ ነበረ፡፡ ጴጥሮስ ደግሞ ባሉበት ታራራ ላይ ረዘም ላሌ ጊዜ ዳስ ሰርቶ ስለ መኖር ይናገራል፡፡ ኢየሱስ ስለሰዎች ሁሉ ስዘጋጅ ጴጥሮስ ደግሞ በዚያ ቦታ ስለተገኙት ጥቅት ሰዎች ይናገራል፡፡

ሌላው ቀርቶ በዚህ ምድር የመከራና የድካም ጊዜያቸውን ጨርሰው የሄዱትን ሙሴና ኤሊያስ እንኳ በዚያ ለማስቀረት ሲያስብ አላፈረም፡፡ ይህ የእንቅልፍ በእርሱ ላይ መክበድና የፍርሃት ምልክትና ውጤት ነው፡፡ የምድር ተልዕኮውን ጨሪሶ ለመሄድ እየተዘጋጄ ያለውን ኢየሱስ ድንኳን ተሠርቶለት በተራራ ላይ እንዲቀመጥ መጠየቅ ምንኛ ከተልዕኮ አላማ መውጣት ነው?

እኛስ ለአጭር ጊዜ በምንኖርበት ምድር እያለን አስደናቂ የሆነ ዘላለማዊ በረከት፣ ክብርና ተልዕኮ ተሰጥቶን አለን፡፡

ታዲያ ብንነቃና ከጌታ ጋር ወደ ግባችን ብንገሰግስ አይሻለንም ወይ? ጴጥሮስን ከዚያ ግራ መጋባት ውስጥ አውጥቶ የጉዞ አላማውን በክብር እንዲጨርስ የረዳው ጌታ እኛንም ይርዳን፡፡

ገና ጴጥሮስ የራሱን ሃሳብ እየተናገረ እያለ፣ ከሰማይ የመጣው የእግዚአብሄር ድምጽ አቋረጠው፡፡

5.       ለኢየሱስ የሚመሰክር ድምጽ በደመና ውስጥ መጣ

እኔ ጴጥሮስ በሙሴና ኤሊያስ መምጣት፣ በኢየሱስ ፊትና ልብስ መለወጥ ተገርመው ዳስን ስለመስራት በእንቅልፍ ልብ ስናገሩ፣ እግዚአብሄር አብ ግን የትኩረት አቅጣጫቸውን መቀየር ፈለገ፡፡

ይህ ጊዜ የሙሴ ወይም የኤሊያስ ጊዜ እንዳልሆነና ይህ ጊዜ ስለኢየሱስ መልክና ልብስ መለወጥም ብቻም እንዳልሆነ ማሳየት ፈለገ፡፡

ይህ ጊዜ ኢየሱስን ስለመስማት ነው፡፡ ለኢየሱስ የሚገባውን ክብርና አምልኮ ስለመሥጠት ነው፡፡ ስለዚህ ነው “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ የመጣው።

ቁ 34-35 “ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም፦ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።”

ሕይወታችንና ዘላለማችን በኢየሱስ ውስጥ አለ፡፡ ኢየሱስን መስማት እግዚአብሄር አብ ከእኛ የሚፈለገው ትልቅ ነገር ነው፡፡ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” ተብሎ ተጽፎአልና (ዮሃ 3፡26)፡፡ “እርሱን ስሙት፡፡”

እግዚአብሄር አብ ስለኢየሱስ ሲናገር ይህ የመጀመሪያም የመጨረሻም ጊዜ አይደለም (ዮሃ 12፡27-33) ፡፡ ኢየሱስ ሲጠመቅም ተመሳሳይ መልእክት ተላልፎ ነበርና (ማቴ 3፡17)፡፡ እግዚአብሄር ራሱን እየደጋገሜ ኢየሱስን ስለመስማት ሲናገር፣ እርሱን አለመስማትና አለማመን የሚያመጣው ፍርድ ስላሌ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስም እርሱን ስለመስማት ሲናገር እንዲህ ብሎአል “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።” (ዮሓ 5፡24) የዕብራዊያን መልእክት ጸሓፊም እንዲህ በሎ ፅፎአል (2፡2-4)፣

በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።

ኢየሱስን አለመስማት ለሰው ልጅ ሕይወት ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ስለዚህ ነው “እርሱን ስሙት፡፡” የሚል ድምጽ የመጣው፡፡

6.       እነጴጥሮስ ያዩትና የሰሙትን ሳይናገሩ ቆዩ

ሌላው አንድ በጣም ደስ የሚለው ነገር፣ እነጴጥሮስ ስለኢየሱስ የተነገራቸውምን ወዲያው ሥራ ላይ ማዋል መጀመራቸው ነው፡፡ በተራራው ከተፈጸሜው ክስተት በሃላ፣ ኢየሱስ በእርሱ ላይ መምጣት ያለበት ነገር (ስቅለቱ፣ሞቱና ትንሳኤው) እስከሆን ድረስ ለማንም እንዳትናገሩ ብሎ እንዳዘዛቸው (ማቴ 17፡9)፣ በተራራው ላይ ያዩትን ትልቅ ክስተት ከማውራት አንደበታቸውን ለጎሙ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም እየሱስን መስማትን ወዲያው መለማመድ ጀምረዋል፡፡

እስቲ እኛ ምን ያክል ለጌታ እንታዘዛለን? ዝምበሉ ሲለን ዝም ማለት፣ ተናገሩ ስነባል መናገር እንችል ይሆን?

ጊዜው ሲደርስ ግን ይህ ያዩትና ሰሙት ነገር ለእነጴጥሮስ እምናትና አገልግሎት ጽናት ሠጠ፡፡ ጴጥሮስም በኃላ ሲመሰክር እንዲህ ቢሎአል፤

የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።” (2ጴጥ 1፡16-18)

 

ፈቃደኛ ከሆናችሁ እስቲ ይህንን ጸሎት ከእኔ ጋር ድገሙት

ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ስለእኔ ስትል ራስህን አዋርደህ ወደ ዓለም ስለመጣህ አመሰግንሃለው፡፡ በዚህም ምድር ላይ ስለእኔ ስለከፈልከው ዋጋ፣ መከራን ስለተቀበልክልኝ፣ ስለተሰቀልክልኝ፣ ስለሞትክልኝ፣ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ስለተነሳህልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡

ጌታ ሆይ፣ እኔ አንተን ባልሰማሁበት፣ ባልታዘዝኩበት ጊዜና ነገር ሁሉ አሁን ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ፡፡ ከዚህም በሃላ በሚቀረኝ ዘመኔ ሁሉ፣ አንተን እየሰማውና እየታዘዝኩ መኖር እንዲችል በጸጋህ እርዳኝ፡፡

እግዚአብሄር ሆይ፣ ስለምትወደኝና ልጅህን ስለላክልኝ፣ እርሱን እንዲሰማና እንዳምን በምስክርነት እውነቱን ስለገለትክ አመሰግንሃለሁ፡፡ በቀሪው የሕየወት ዘመኔ ሁሉ አንተ የምትወደውንና በእርሱም ደስ የምልህን ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስማትና ለመታዘዝ እባክህ ጸጋን አብዛልኝ፡፡ በኢየሱስ ስም አሜን፡፡

 

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *