Sermons

Easter about Future

ትንሳኤ ምልክትም ነው፡፡ ኢየሱስ እንደ ተናገረ ሆኖአል፡፡

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በመላው ዓለም (በተለያዩ ቀናት ቢሆንም) ይከበራል፡፡ በዓሉ ኢየሱስን አውቀውና አምነው በሚከተሉትና ስሙን በትክክል መጥራት በማይመቻቸው ሁሉ ዘንድ ይከበራል፡፡ የአካባበሩም መልክና ስም የተለያዬ ነው፡፡ በመብል፣ በመጠጥ፣ በመጾም፣ በመፈሰክ፣ በመዘመር በመዝፈን ወዘተ.

ከኢየሱስ ከሞት ከመነሳት እውነት (ሃቅ) በተስተጀርባ በተለይ ዛሬ ላይ ያለን ትውልድ በትክክል ማሰብና መገንዘብ ያለብን እውነት እንዳለ አምናለሁ፡፡ እርሱም ትንሳኤው ኢየሱስ ተመልሶ እንደሚመጣ እርግጠኞች ያደርገናል፡፡

ጌታ ኢየሱስ ገና ከመገደሉ በፊት ለተከታዮቹ ደጋግሞ ኣሳልፎ ሊሠጥና መከራ ሊቀበል እንዳለ፣ ሊሰቀልና በሶስተኛው ቀን ከሞት ስለመነሳቱ እና ወደ አባቱ እንደሚሄድ ተናግሮ ነበረ፡፡ እያንዳንዱም ነገር ከሦስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተፈጸመ፡፡ ኢየሱስ እንደ ተናገረ ሆኖአል፡፡

እጅግ መገንዘብ ያለብንና ልናስበበት የሚገባን ነገር ግን ኢየሱስ ከላይ ስለጠቀስኳቸው ነገሮች ብቻ አልተናገረም፡፡ ከእርገቱ በኃላም ስለሚፈጸሙ ነገሮች ተናግሮአል፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ መውረድ፣ ስለአማኞችና ስለቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ጉዞ፣ በመጨረሻም ዘመን ስለሚሆኑ ነገሮች ተናግሮአል፡፡ ኢየሱስ በመጨረሻ ዘመን ችግር እንዳለ ብቻ አመልከቶ አልተወም፡፡ እጅግ አስገራሚ የሆነ፣ ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውንና ያለውን የሚመጣውንም መከራ ሁሉ የሚያስረሳ ትልቅ መጽናናትና ተሓድሶ ቃሉን ሰምተው ለሚያምኑ ሁሉ እንደሚሆን ተናገረ፡፡

በአንጻሩ ደግሞ እየሰሙ የማይሰሙ፣ እያዩ የማያዩ፣ እግዚአብሄርን መከተልና ቃሉን መስማት ሞኝነትና ክሳራ እየመሰላቸው ለናቁት ደግሞ ቃሉ ራሱ እንደሚፈርድባቸው ተናግሮአል፡፡

ልጅ እያለው አንድ ጊዜ የሆነውን ነገር አስታውሳለሁ፡፡ ኩመራ ከሚባል ሰው ጋር እህል እጠብቅ ነበረ፡፡ ኩመራ የሚያድርበት ጎጆ ከአከባቢው ትንሽ ከፊ ባለ ቦታ ላይ ቢሆንም በአቅራው ያለው ትልቅ ወንዝ በመሙላቱ አከባቢውን ማጥለቅለቅ ጀመረ፡፡ እኔም ቡና ሊጠራው ሂጄ እየበዛ ያለው ጎርፍ ስላልተመቸኝ ቶሎ ና ጎርፍ አለና አልኩት (በዚያን ጊዜ የወንዙ ሙላት እንደሆነ አልገባኝም ነበረ)፡፡

ኩመራም ከጎጆው ወጥቶ፣ ጎርፉ ወደ ጉልበቱ አከባቢ ስለደረሰ፣ ሱሪውን ሰብስቦ ከሚሻገር “ቡናው ይቅርብኝ” ብሎ ብሎ ወደ ጎጆው ተመለሰ፡፡ ቢለምነውም እምቢ አለ፡፡ ብዙም ሳንቆይ ያልገመትነው ነገር ሆነ፡፡ በላይ በኩል ከመንገዱ የወጣው ወንዝ በብዙ ፊጥነትና ጎልበት እየገነፈለ መጥቶ ኩመራን ቀለበት ውስጥ አስገባው፡፡ እኔም ጮሄት አቀለጥኩ፡፡ “ኩመራ በውሃ ተበላ” እያልኩ፡፡ብዙ ሰው ተሰብስቦ መጣ፡፡ ግን ገብተው ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ኩመራ ደንግጦ ከጎጆው ወጣ፣ አሁን ግን በቅድሙ መንገድ መሻገር ፈጽሞ አይገመትም፡፡ ሰዎችም በዚያ ሞክር፣ በዚህ ሞክር እያሉ ይጮሁ ነበረ፡፡ በዚያ ላይ የወንዙ አሞላል ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፣ በዚያ ስል በዚህ ሲል ከብዙ ጭንቀት በኃላ በአንገቱ ተሻገረ፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡ እርሱ ከተሻገረ በኃላ ጎጆውም በጎርፉ ተወስዳ እንዳልበረች ሆነች፡፡ ወንዙ ሲቀንስ በአከባቢው ከሞላ ደለልና ወንዙ በተዋቸው ግንዶች ተሸፍኖ ስለነበረ፣ ጎጆ በዚያ እንደነበረ ለመገትም ያስቸግር ነበረ፡፡

በዚህ እውነተኛ ታሪክ ውስጥ፣ ኩመራ የችግሩን አደገኝነት ከተረዳና መውጫ እየፈለገ እያለ (ገና መትረፉንም ሳያውቅ)፣ “ወይ እኔ፣ ቅድም ጎርፉ ጉልበት ሳይደ፣ርስ ሱሪዬን ሰብስቤ ተሻግሬ ቢሆን” ማለቱ አልቀረም፡፡ ከወጣ በኃላ ኩመራ ሲናገረኝ፣ “ይቅርታ፣ እኔ እኮ እንዲህ አልመሰለኝም፣ ልጅ ስለሆንክ ብቻ የፈራህ መስሎኛል” ነበር ያለው፡፡

ዛሬም የእግዚአብሄር ቃል ሲነገረን ቶሎ ብለን ካለንበት ሁኔታ መውጣት አለብን፡፡ የከፋ ነገር ሊኖር ሲለምችል፡፡ ቃሉን የሚነግሩን ሰዎች ምናልባት ከእኛ ያነሱ አላዋቂዎች ቢመስሉንም (ቃሉ እጅግ እውነተኛና የተረጋገጠው ስለሆነ) አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለብን፡፡ ኢየሱስ እንደ ተናገረ ሆኖአል፡፡

የእግዚአብሄር ቃልን እውነተኝነት ከሚናረጋግጥበት መንገድ አንዱ የኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ነው፡፡ ይህ እኛ የሚያስተላልፊልን ዘርፈ ብዙ መልእክት አለው፡፡

ታዲያ ስለኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ስናስብ

  1. እግዚአብሄር እንደሚወደንና ለበደላችን ቤዛ እንዲሆን ልጁን እንደላክ ማወቅ እንችላለን፡፡
  2. የኢየሱስ ቃልና አስተምሮት በሙሉ ትክክል እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡
  3. ኢየሱስ አደርጋለሁ ወይም ደግሞ ይሆናል ብሎ ከተናገራቸው ነገሮች አብዛኞቹ ከሆኑ፣ በመጨረሻ ዘመን እንደሚሆኑ ከተነጋራቸውም አብዛኞቹ እየሆኑ ካሉ፣ እኛም ቆም ብለን በንስሓና በመመለስ ፍታችንን ወደ እግዚአብሄር ማዞር አለብን፡፡
  4. ሊመጣ ካለው ጸጸት አምልጠው ሊገለጥ ያለውን ክብር ይወርሱ ዘንድ ለሰዎች ሁሉ የእውነትን ቃል ያውም የጌታችንን ቃል መናገር ያስፈልገናል፡፡
  5. “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” (ሓ.ሥ 1፡8-11)፡፡
  6. ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ብሎአል፡፡ ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።… እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሃ 14፡1-3፣6)

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *