SermonsUncategorized

ኢየሱስ ሥራውን ቀጠለ

I must work the works of him that sent me, while it is day: the night cometh, when no man can work. “ ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች ”Evangelical Church Mekane Yesus in Scotland, ECMYIS, Glasgow, Uk. Amharic service

የወንጌል ክፍል፡ ሉቃ 13፡ 31-35

31 በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው፦ ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት። 32 እንዲህም አላቸው፦ ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ፦ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት። 33 ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም ልሄድ ያስፈልገኛል። 34 ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም። 35 እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁም፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።

በዚህ ክፍል እንደምናነበው፣ ጌታ እየሱስ ብዙ የሚሠራቸው ሥራዎች ነበሩት፡፡ በተለይ ደግሞ አጋንንትን ማውጣት እና በሽተኞችን መፈወስ (ቁ.32)፡፡ ይህ ማለት የታሰሩትንና ጤናቸውን ያጡትን የሰዎችን ልጆች ነጻ ማውጣት በቀረችው ጊዜ መፈጸም የሚፈልጋቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህንን ዓላማውን ትቶ እንዲሄድና ከሄሮድስ የመግደል ዕቅድ እንዲያመልጥ ስመክሩት እንመለከታለን፡፡“ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው፦ ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት።” (ቁ 31)

ጌታ እየሱስ ግን በእግዚአብሄር በአባቱ ጥበቃ ይታመን ስለነበረ፣ ሊያስፈራሩበት የሚሞክሩት ሞት ደግሞ የመጣበት ስለሆነ፣ ያለፍርሃት አገልግሎቱን እስከ መጨረሻዋ ሰዓት እንደሚቀጥል ሲነግራቸው እንመለከታለን፡፡ ኢየሱስ ሥራውን ቀጠለ ፡፡

ሰው ሆነን እያለን ነገሮችን የምንፈራቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሞት ጋር ግንኙነት ስለአላቸው ነው፡፡ ሰው ክፉ ይደርስብኛል ከዚያም እሞታለሁ ብሎ ባይፈራ፣ ጨለማን፣ በሽታን፣ ድኅነትን፣ ወዘተ. አይቶ አይጨነቅም ነበረ፡፡ የሰውን ልጅ በሚያስፈራራው ሞት፣ ኢየሱስንም (ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም ስለመጣ) ያስራሩበት ዘንድ ይሞክሩ ነበር፡፡ ግን ኢየሱስ ሥራውን ቀጠለ ፡፡

ያለጊዜውና ያለአባቱ ፈቃድ አንዳችም በእርሱ ላይ ሊሆን እንደማይችልም እንደነበረም ያውቃል፡፡ ይህ እውነት ለኢየሱስ ብቻ የሠራ እውነት አይደለም ነገር ግን እርሱን ለምንከተል ሁሉ ደግሞ እንጂ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር፣ “አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ…” (ሉቃ 12፡7) ብሏልና፡፡ ያለ እግዚአብሄር እውቀትና ፈቃድ አንዳችም ነገር አይሆንብንም፡፡

እንግዲህ ኢየሱስን እየመከሩት የነበሩትን ሰዎች አቀራረብ ስንመለከት፣ ከበጎነትና ነፍሱን ለማዳን ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ እንደመከሩት መገመት እንችላለን፡፡ እነርሱ ያላወቁት ነገር ቢኖር ግን የኢየሱስ የህይወት ጉዞና ዓላማ ምን እንደሆነ ነው፡፡

ስለዚህም እነርሱ በጎ ነው ብሎ የመከሩት ምክር ኢየሱስ ሊቀበለው የማችል ምክር ሆኖ ተገኘ፡፡ ለምን? ኢየሱስ መሞቱ የማይቀር ሆኖ እያለ፣ ሽሽቱ ግን በነበረው ጥቂት ጊዜ ተሠርቶ ማለቅ የሚገባቸው ሥራዎችን እንዳይጨርስ ያደርገዋል፡፡ ያ ማለት ደግሞ፣ አጋንንትና በሽታ በሰዎች ላይ ቀጥለው ይሠለጥናሉ ማለት ነው፡፡ እየሱስ በሰዎች ነጻ መውጣት ያምን ስለነበረ፣ በተነገረውም መልእክት ሳይናወጥ ሥራውን ቀጠለ ፡፡

እኛም ዛሬ በሕይወታችን ብዙ በጎ የሚመስሉ ነገሮች (ምክሮች) ነገር ግን እግዚአብሄር በእኛ ሕይወት ሊሠራ ካለው ነገር ወደኃላ የሚጎትቱን ሓሳቦች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሄር በእኛ ሕይወት ያለውን አላማ በግልጽ መረዳትና ያንን እስከምንፈጽም ድረስ ምንም ነገር ፈርተን ስፍራችንን ሳንለቅ በእግዚአብሄር ጥበቃ ታምነን ሕይወታችንና አገልግሎታችንን መቀጠል እንዳለብን ከጌታ ኢየሱስ እንማራለን፡፡

ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ የነበረውን ተልዕኮ (ሚሽን) ጨርሶ ከመሄዱ በፊት የተወሰነ ወይም ጥቂት ጊዜ እንደነበረው ያውቅ ነበረ፣ ይናገርም ነበረ፡፡ “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” (ዮሓ 9፡4) ብሎአልና። ኢየሱስ ሰው ሊሠራበት የማይችልበት “ሌሊት” ይመጣል ሲል ሰው ሌሊቱ ሳይመጣ የተሠጠውን የቤት ሥራ በርትቶ መጨረስ እንዳለበት ለማሳሰብም ነው፡፡

ይህ “ሌሊት” የሚባለው ሞት ብቻ አይደለም፤ ሰው በሕይወትም እያለ ነገሮችን ማድረግ የሚያቅትበት ጊዜ አለውና፡፡ መሥራት፣ መናገር፣ ማየት፣ መስማት፣ መብላት፣ መሄድ፣ ማንበብ፣ መጻፍ፣ ወዘተ. ከተለያዩ ነገሮች የተነሳ የሚወሰንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡ በመሆኑም ጊዜ እያለ (ሌሊቱ ሳይመጣ) የተሰጠንን ሃላፊነት መወጣት ከእያንዳንዳችን ይፈለጋል፡፡ እግዚአብሄር ይርዳን፡፡

ስለዚህ ዘመናችን የተቆጠረች መሆኗን በመረዳት በዚህ ትንሽ ጊዜ ውስጥ እግዚአብሄር በሕይወታችን ያለውን አላማ ለማከናወን መትጋት አለብን፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ ከእኛ የሚፈልጋቸው ነገሮች ብዙ ወይም ውስብስብ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የጌታን መልክ በሚያሳይ ሕይወት በመኖር፣ እግዚአብሄር ለኛ ያሣየውን ፍቅርና በጎነት በወገኖች እንዲሁም በማያምኑቱ ፊት ማሳየት አለብን፡፡ በመልካም ሕይወትም ምሳሌ በመሆን ልንኖር ይገባናል፡፡ በዓላማችንም እንጽና፡፡ ኢየሱስ ሥራውን ቀጠለ እንጂ ወሬዎች ትቶ እንዲሸሽ ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡

ሰዎችና ሁኔታዎች ከተጠራንበት ጥሪና በተሠጠን ጊዜ ውስጥ መሠራት ካለበት ሥራ በራሳቸው ግምት በጎ ነው ወደሚሉት ሲጠሩን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ሆነን መፈተሸና ራሳችንን መጠበቅ እንድንችል እግዚአብሄር ይርዳን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

(በእህት አይዳ (ሊሊ) ብርሃኔ የቀረበ)

(17/03/2019, ECMYIS, Glasgow )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *