Sermons

ኢየሩሳሌም እና ኢየሱስ

የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።” (ሉቃ 9፡ 56)

በኢየሩሳሌምና በሰማሪያ መካከል የነበረው አለመግባባት የቆየ ታረክ ነበረ፡፡ በመካከላቸው የነበረው ቅራኔ ሥር ከመስደዱ የተነሳ፣ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ለማለፍና ለማረፍ በፈቀደ ጊዜ የሰማሪያ ሰዎች ኢየሱስን በኢየሩሳሌም አይን ተመለከቱት፡፡ ስለዚህም ልቀበሉት ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡

የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥ በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፦ ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።” (ሉቃ 9፡ 51-56)

ጊዜው፡ ኢየሱስ ወደ ላይ ሊወሰድ እየተዘጋጄ ባለበትና ለኢየሩሳሌም ጉዞው እየተሰናዳ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ከመሄዱ በፊት ግን መልእክተኞችን በፊቱ ወደ ሰማሪያ ሊኮ ነበረ፡፡ በሰማሪያ ማለፍ ስለነበረበት፡፡ ምናልባት ኢየሱስ ተከታዮቹን አስከትሎ ሲመጣ የሰማሪያ ሰዎች ለተቃውሞ እንዳይወጡ፣ ምናልባትም ደግሞ ኢየሱስ በአከባቢያቸው ውስጥ ሲያልፍ እያገለገላቸውም ለማለፍ ሊሆን ይችላል (ማቴ 10፡5)፡፡ የሰማሪያ ሰዎች ግን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳለም አልፎ ሊሄድ እንዳሌ ስለሰሙ፣ ኢየሱስን ለመቀበል ፍቃደኞች አልነበሩም፡፡ ለምን ይሆን? ምክንያቱም ከኢየሩሳሌም ጋር ቅራኔ ነበራቸው፡፡

በኢየሩሳሌምና በሰማሪያ መካከል የነበረው አለመግባባት የቆየ ታረክ ነበረ፡፡ በመካከላቸው የነበረው ቅራኔ ሥር ከመስደዱ የተነሳ፣ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ለማለፍና ለማረፍ በፈቀደ ጊዜ የሰማሪያ ሰዎች ኢየሱስን በኢየሩሳሌም አይን ተመለከቱት፡፡ ስለዚህም ልቀበሉት ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡

በሰማሪያውያኑ እኛ ከኢየሩሳሌም ጋር ምንም ስለሌለን የኢየሩሳሌም ወዳጆች በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም ብለው ተነስተዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች በምንም መልኩ አንፈልጋቸውም፡፡ አናምናቸውም፡፡ ምንም እንዲያደርጉልን አንጠብቃቸውም በማለት አክርረውና አምርረው ተቃውሞአቸዋል፡፡ በሰማሪያውያኑ እምነት አምልኮ ለእግዚብሄር መቅረብ ያለበት በገሪዝም ተራራ ላይ እንጂ በኢየሩሳሌም አይደለም፡፡ ከኢየሩሳሌምና የኢየሩሳሌም ወዳጆች በእነርሱ ዘንድ የተጠሉ ነበሩ፡፡ ሌላው ወርቶ የውሃ መቀጃ እንኳ ልዋዋሱ አይችሉም (ዮሃ 4፡)፡፡

በሁለቱም መካከል የነበረው አለመግባባት እጅግ በጣም የከረረ ከመሆኑ የተነሳ አንዳቸው የሌላቸውን ጥፋት የተመኙ ይመስላሉ፡፡

ይህ የሰማሪያውያን ኢየሱስን በመካከላቸው ለማረፍና ለማለፍ ፈቃድ መንሳት ሁኔታ ከኢየሱስ ይልቅ ዴቀ መዛሙርቱን አስቆጣቸው፡፡ ስለዚህ ምናልባት ቀድሞውኑ ስለሰዎቹ የነበራቸውን ጥላቻና ንቀት ከነበረበት ቀሰቀሰው፡፡

ለጌታ እጅግ የቀኑ ስለመሰላቸውም፣ እነዚያን ሰማሪያውያን ከነሁሉ ነገራቸው ከምድር ገጽ ለማጥፋት ፈቃድ ከኢየሱስ ጠየቁ፡፡ ያውም ከሰማይ በወረደ እሳት፡፡ የሚገረመው፣ ይህቺንማ እኛም ማድረግ እንችላለን ብለው አስበዋልና፣ ከኢየሱስ የጠየቁት ፈቃድን ብቻ ነበረ፡፡ ምናልባት በእነርሱ አስተሳሰብ፣ የማይጠቅሙ ማህበረሰብ ስለነበሩ መኖር አይገባቸውም፡፡

ኢየሱስ ግን ከደቄ መዛሙርቱ ዘንድ የቀረበለትን የማጥፋት የፈቃድ ጥያቄ በሰማ ጊዜ ገሰጻቸው፡፡ “ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤” አላቸው፡፡ ምንም እንኳን ለኢየሱስ የቀኑ ቢመስሉም፣ ደቄ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ተቃውሞ እንጂ ድጋፍ አላገኙም፡፡

ሰዎቹ ፈቃደኞች ስላልነበሩ አልፎአቸው “ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።”

ከዚህ ታሪክ የምንማረው ጥላቻና አለመቀባበል ስር እየሰደደ ሲሄድ ሰዎች ጌታ ዘንድ የመጣላቸውን ታላቅ እድል እንኳ የሰውና ከሰው ስለሚመስላቸው በቀላሉ ያናንቁታል፡፡ ክርስቶስና ቃሉን፣ በረከቱንም ከድርጅት፣ ከቡድን፣ ከጎሳ፣ ከቋንቋ ጋር አያይዘው ስለሚመለከቱ የመልእክቱ ተጠቃሚዎች መሆን ያቅታቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ከዚህ አይነቱ መታወር ይጠብቀን፡፡

በብሉህ ክዳን ታሪኳን የምናነብ የሳባ ንግሥት ረጅም መንገድ ተጉዛ የሰማችውን የሰለሞንን ዝና ለማየት ሲትሄድ፣ በሰማሪያ የነበሩ ሰዎች ደግሞ የነገስታት ንጉስ የሆነው ኢየሱስ በመካከላቸው ለማለፍና ለማረፍ ሲፈቅድ እምቢ ብለው አሳደዱት፡፡ የኢየሩሳሌም ሰዎች ደግሞ ከከተማቸው አውጥተው ሰቀሉት፡፡

በተለይ አሁን ባለንበት ጊዜና ዓለም ይህ የመጻፍ ቅዱስ ክፍል ብዙ ሊያስተምረን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክኒያቱም ያኔ የነበረው የሰዎች አስተሳሰብ ዛሬም ሰፍቶና በዝቶ እንጂ ጠፍቶ ስለማናገኘው ነው፡፡

አይውዳዊያንና የሰማሪያ ሰዎች በመልካም እንዳልተያዩ ሁሉ፣ ዛሬም አንዱ የራሱን ዘር ከሌላው ሰው ዘር አስበልጦ ማየትና ማሳየት፣ የአንዱ ደግሞ ከሌላው ቀልሎ መታየት፣ ከዚህ ጋር በተያያዜ ደግሞ የምንለዋወጣቸው የቃላት ጦርነቶች፣ ከእርስ በርሳችን ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም የሚያርቀን ነው፡፡ የቋንቋ፣ የባህል፣ የመልክ፣ የአኗኗር ልዩነቶች መኖራቸውን መቀበልና ማድነቅ እንዳለ ሆኖ፣ ሰውን ግን እንደ ክቡር ሰው አለማየት ችግሩ የከፋ ነው፡፡

በዚህ በዛሬው የወንጌል ንባብ ክፍላችን ውስጥ ያሉ ሁለቱም ማህበረሰብ የአምልኮ ሥርዓትና ወግ አላቸው፡፡ አንዱ ኢየሩሳሌም የተቀደሰች የአምልኮ ስፍራ ናት ብሎ ሲያምን ሌላው ደግሞ ገሪዝም ተራራ ለአምልኮ የተቀደሰ ብቸኛ ተራራችን ነው ብሎ ያምናል፡፡

ሁሉም ግን አምልኮን ከቦታ ብቻ ጋር አስተሳስረው የእግዚአብሄር ፈቃድን ከማወቅና ማድረግ ግን የነጠሉት ይመስላሉ፡፡ ሁለቱም በተረዱት መንገድ እግዚአብሄርን እንደሚያመልኩ ይናገራሉ፡፡ ይህ በራሱ ክፋት የለውም። ግን ደግሞ አንዱ የሌላው ጠላት ከመሆናቸው የተነሳ፣ አንዱን ርኩስ ራሱን ቅዱስ አድርጎ መቁጠር እና መገፋፋት በግልጽ የሚታይ የእለት ተዕለት ተግባርና ልምምድ ሆኖላቸዋል፡፡ አይውዶቹ ሰማሪያውያኑን ስጸየፉአቸው፣ ሰማሪያውያኑ ደግሞ አይውዶቹን ይጠሉአቸው ነበረ፡፡ ጥላቻውም አይኖቻቸውን ስላሳወሬ፣ በመካከላቸው የሚኖረውና የሚያልፈው ኢየሱስ ተቀባይነት አጣ፡፡

ምናልባት ዛሬ፣ እኛ ከምንከተላቸው የክፋት ልምምድ የተነሳ፣ ሌሎች እግዚአብሄርን ይገፉት ይሆን? ምናልባትም ደግሞ ሌሎች ስላሳዩን ክፋትና ንቀት እኛም ጌታን እየገፋነው ይሆን?

ኢየሱስስ የየትኛውን ወገን ጎራ መውሰድ ነበረበት?

ትውልዱን ስንወስድ ኢየሱስ ከአይሁድ ወገን ነበረ፡፡ አምልኮውንም ስንወስድ እንደ አይሁድ ያመልክ ነበረ፣ ወደ ምኩራባቸውም ይሄድ ነበረ፡፡ ወደ ኢየሩሳለምም ይሄድ ነበረ፡፡ ያደገውም ያንኑን እያደረገ ነበረ፡፡ ስለአይውድነቱም በግልጽ የተናገረባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ኢየሱስ እንደ እግዚአብሄር ልጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ልጅም ራሱን ገልጦአል፡፡ ያ ማለት የማንነትን ማጣት ችግር አላጋጠመውም ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በቀላሉ ኢየሱስን የሚያይና የሚሰማ ሰው ከአይውድ ጎራ ቢመድበው ስህትት አይሆንም፡፡ ይህ ማለት ግን ኢየሱስ ከአይውድ ወገን መወለዱና በመካከላቸው ማደጉ በቀጥታ ሰማሪያውያንን ጠይ ያደርገዋል ማለት አይደለም፡፡ እርሱ ጠንቂቆ ክፉውንና መልካሙን፣ በአባቱም ዘንድ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን ያውቃልና፡፡ ተልዕኮውም ዓለም ሁሉ በእርሱ እንድድን ነው። ኢየሱስ ወደ ሰማሪያውያን ለመሄድ አጋጣሚዎችን ሁሉ ይጠቀም ነበረ፡፡ በዚህም ክፍል የሆነው እንዲሁ ነው፡፡ ኢየሱስ በውሃ ጉድጓዳቸው ጎን ቁጭ ብሎ፣ እነርሱ እንኳ የሚፀየፉአትን ሃጢአተኛ ሴት ያገለግል ነበረ (ዮሃ 4፡6-)፡፡ ልመናቸውንም አክብሮ በመንደራቸውም ቆይቶ ም ያውቃል፡፡ እርሱ እንደሌሎቹ አይጠላቸውም፡፡ ጌታ አንተን/አንቺንም እንደ ሌሎች አይጠላህም/ሽም።

የኢየሩሳሌሞቹም ቢሆን ከሰማሪያዊያን የበለጠ ለኢየሱስ የሚያስደስት የአምልኮ ልምምድ አልነበራቸውም፡፡ ሰማሪያዊያኑ ኢየሱስ እንዲሄድላቸው ስለምኑት ኢየሩሳሌሞቹ ደግሞ ከከተማቸው አውጥተው ሰቅለውታል፡፡ አይውዳዉያኑ አባታችን አብርሃም ነው ስሉ ሳሚራዊያኑ ደግሞ አባታችን ያዕቆብ ነው ይላሉ፡፡ ያዕቆብ የአብርሃም የልጅ ልጅ ነው ።

ኢየሱስ ግን ለሁሉም የሰላምን፣ ከእግዚአብሄር ጋር የሚያስተራሪቅን መልካም ዜና ይዞ ነው የመጣው፡፡ ሳያውቁት የሚያመልኩትን አምላክ፣ ፍቅሩንና ምህረቱን አውቀው በእውነት እና በመንፈስ እንዲያመልኩት ለማድረግ መጣ፡፡ በሰማሪያውያን ባለማወቅ ላይ የተመሰረተ አምልኮ ኢየሱስን አስገፋ፣ በኢየሩሳሌም የነበረው የእውቀት ኣምልኮ ኢየሱስን ለመስቀል አሳልፎ ሰጠው፡፡ እንደ ቃሉ ሁሉም በድሎአልና (ሮሜ 3:23)።

ኢየሱስ ስለወንጌል ተልእኮ ሲናገርም መደረስ አለባቸው ብሎ ለተከታዮቹ ከተናገራቸው ስፍራዎች አንዱ ሰማሪያ ነው፡፡ የሰማሪያ አገልግሎት ይቀጥላል፡፡ እስከዓለም ዳረቻም ይሄዳል። በመጨረሻም ትውልዱ ሁሉ ወንጌልን ይሰማል (ሓሥ1:8)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ይመጣልና ይህ ይሆናል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ገፊዎች ግን በከንቱ ደከሙ፣ ኢየሱስን የመሰለ ትልቅ እድል እንዲያመልጣቸው አደረጉ፡፡

ኢየሱስ አንግቦ የወጣው ዓላማ፤ በእነዚህ በምጣሉ ማህበረሰቦች መካከል ገብቶ ከአንዱ ወግኖ ሌላውን ሊወጋ ሳይሆን፣ ሁሉም ጠፍተዋልና ሁሉንም “በእውነትና በመንፍስ” ወደ ሆነው አምልኮ ለማምጣት ነው፡፡ ሁሉም በድለዋል፣ ሁሉም ግን በክርስቶስ መዳን ይችላሉ፡፡

የሰማሪያ ሰዎች ኢየሱስን መቀበልና ማስተናገድ ያቃታቸው ኢየሩሳሌምን ስለሚጠሉ ወይም ከኢየሩሳሌም ጋር አለመግባባት ስለነበራቸው ነበር፡፡ ኢየሩሳሌምንና ኢየሱስን መለየት አቃታቸው፡፡ እነርሱ የማያምኑትን የሚያምንን ይጠሉ ነበር፡፡ ይገፉም ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርትም በጥላቻው ውስጥ ጠልቀው ገብተው ነበር፡፡ ጥፋትን እስኪመኙላቸው ድረስ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሓይማኖተኞች ወይም አማኞች በሚባሉት መካከል እንግዳ የሆነ ነገር ሲደረግና ሲሳማ ሊያስደነግጠን አይገባም፡፡ ተገቢ ባይሆንም። ጥፋትን ግን በጥፋት ለመመለስ መነሳትም የለብንም፡፡ ኢየሱስ “ወደ ሌላ መንደር” እንደሄዴ፣ ምናልባት ጊዜ መስጠት ሊያስፈልገን ይሆናል፡፡

ዴቀ መዛሙርት የሌሎችን ችግር ለማረም ስነሱ ራሳቸው ግን የተቀበሉትን/የሆነላቸውን መንፈስ እስከመርሳት ደርሰው ነበረ (ገላ 6:1)፡፡ ለዚያም ነው ኢየሱስ የገሰጻቸው፡፡

ኢየሱስን ከመግፋትና ከማስገፋት ልምምድ እግዚአብሄር ይመልሰን፡፡ “ኢየሩሳሌምን” ከኢየሱስ ለይቶ ማየት ለትውልድ ህይወትንና ፈውስን ያስገኛል።

ፀሎት፡- ጌታ ኢየሱስ ሆይ በተገዳዳሪ ሁኔታ ውስጥ ራስህ በማለፍ ለእኛ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ትምህርት ስላስቀረህልን እናመሰግንሃለን፡፡ በአግባቡ ከአንቴ ባለመማራችንና ለገጠሙን ተግዳሮቶች ሁሉ እንደ ፈቃድህ ምላሽ መስጠት ባልቻልንባቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ይቅር በለን፡፡ ደግሞም ነገሮችን፣ ሁኔታዎችን፣ ሰዎችን፣ ድርጅቶችን፣ መሪዎችን አማኞችንም ወይም ሌሎችን ምክኒያት አድርገን አንቴንና ቃልህን እንዳንገፋ እባክህ ሁልጊዜ እርዳን፡፡ ማስተዋልንም ስጠን፡፡ ለቤዛ ቀን የታተምንበትን ቅዱሱን መንፈስህ ሳናሳዝን፣ ነገሮች በመንፈስህ ምሪት፣ በቃል ምሪት፣ በፍቅርና በጸጋህ እንድናደርግ እርዳን። አሜን፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ።

by Teklu

One thought on “ኢየሩሳሌም እና ኢየሱስ

  1. እግዚኣብሄር የሁሉ ብሄር ኣምላክ ነውና እሱ መልካም ሆኖ እንዴት በመልካም ኑሮ መኖርና ህይወታችንን መምራት እንዳለብን ኣሳይቶናል የሚሰማ ከተገኘ
    ይህ መልእክት ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን ሁሉ ጊዜያዊ እና በጣም ኣስፈላጊ ሆኖ ኣግኝቸዋለሁ
    ኣንተንም ወንድም እግዚኣብሄር የኪዳኑ ኣምላኽ ይባርኽህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *