Sermons

ነውር

ኢያሱ 5፡9-12 9 እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ። 10 የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ። 11 ከፋሲካውም በኋላ በነጋው የምድሪቱን ፍሬ የቂጣ እንጎቻ ቆሎም በዚያው ቀን በሉ። 12 በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።

ኢያሱ 5፡9-12 (ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ )

9 እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ። 10 የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ። 11 ከፋሲካውም በኋላ በነጋው የምድሪቱን ፍሬ የቂጣ እንጎቻ ቆሎም በዚያው ቀን በሉ። 12 በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።

በዚህ ክፍል ውስጥ በሕዝቡ ሕይወት ስለተቀየሩት ነገሮች እግዚአብሄር ደስ ብሎት ሲናገር እንሰማለን፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ደስታ ደግሞ ሓሳቡም የተጀመረው በእርሱ በእግዚአብሄር ዘንድ ነበረ፡፡ ሆኖም ግን ሕዝቡ እግዚአብሄር እንዲያደርጉት የጠየቃቸውን በማድረጋቸው ዘመናትን ከቆጠረባቸው ነውር ስላቀቁ እናያለን፡፡ በኃላም በኢሳይያስ ሲናገር “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ” (ኢሳ 1፡19) እንዳለው ከመታዘዝ ልምምድ ቀጥሎ ብዙ ሳይቆይ የተስፋይቱን ምድር ፍሬ መብላት ጀመሩ፡፡

በምድረበዳ ውስጥ መና ማግኘት ትልቅ በረከት ነው፡፡ መልካም በሆነች የተስፋይቱ ምድር (ፍሬና በረከት በሞላች ምድር) እየኖሩ በመና መኖር ግን አለመታደል ነው፡፡ ምክንያቱም በአካል ከምድረ በዳ ወጥቶ ነገር ግን የምድረ በዳን ሕይወት መቀጠል ስለሆነ፡፡ እግዚአብሄር ይህንን ጉስቁልና “ከዛሬ” በኃላ ከሕዝቡ ላይ ሲያስወግደውና ያንን በማድረጉ ደግሞ ደስ ብሎት ሲናገር እናያለን፡፡ “ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ “ ይላልና፡፡

ጌታ በውድ ሕዝቡ ጉስቅልና ደስ አይለውም፡፡ የግብጽ ነውርን ይዞ የሚዞር ሕዝብ ነበሩ፡፡ በክፍሉ ውስጥ እንደሚታየው አገላለጽም ፣ ነውሩ በጫንቃቸው ላይ የከበደና ያስቸገራቸው ይመስላል፡፡ “ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” ይላል እግዚአብሄር፡፡ ሲናየውና ሰዎቹ ሲመለከቱት ቀላል የሚመስል ነገር ነው የተደረገው፣ እግዚአብሄር ሲመለከት ግን “ወደ ፊት ከመራመድ የከለከላቸው፣ በአካል ከምድረ በዳ ወጥተው ግን ውሱን የሆነውን የምድረበዳን ኑሮ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ነገር ነው፡፡ ይህ እግዚአብሄር በሕዝቡ ላይ የተጸየፈው ነገር ብዙዎችን በምድረ በዳ የፈጃቸው፣ የ40 ቀናትን መንገድ ለዘመናት እንዲጓዙት ያደረጋቸው ችግር ነው፡፡ ዛሬ ግን “የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ “ ይላቸዋል እግዚአብሄር፡፡

ይህ የአለመገረዝ ሸክም የአካል መገረዝ አለመገረዝ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብና የአምልኮ ለውጥን ማምጣትም ነው፡፡ እግዚአብሔር “የግብፅን ነውር “ ብሎ የሚጠራው ወደ እስራኤላዊያን ተጋብቶ፣ አሰራራቸውንና አኗኗራቸውን ቃኝቶ፣ በዚያው ልክ ደግሞ በአስተሳሰባቸው ውስጥ ትክክለኛ ተደርጎ (ኖርማላይዝድ ተደርጎ) ተወስዶ የኖረው የግብጻውያን የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡

እስራኤላዊያን በግብጽ በኖሩት ዘመን ልክ በብዙ ነገራቸው ግብፃውያን ሆነዋል፡፡ የሕይወት ልከታቸውም (ስታደርዳቸውም) የግብጻውያን ሕይወት ነው፡፡ ከግብፅ ከመውጣታቸው በፊት ምናልባት የሚመኙት ነገር ቢኖር እንደ ሌሎች ግብጻዊያን ለመኖር ከባርነት መላቀቁ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ካለፈ በኃላ ሲንገመግመው ያ ባርነት ባይኖር ኖሮ ወደ እግዚአብሄር የሚጮሁበትም ነገር የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ ምናልባት እግዚአብሄር ለዘላለም ላያጣቸው ጊዜያዊ ባርነቱን ፈቅዶ ይሆን? ቢያንስ ልዩነት እንዳላቸው፣ የግብጽ አለመሆናቸውን ፣ አምላካቸውም የግብጻውያን ጣኦት አለመሆኑን የሚያውቁበት አንዱ ነገር ነበርና፡፡

ከአለም ጋር ተመቻችታችሁ ለመኖር የፈለጋችሁትን ዓይነት መስዋዕትነት ብትከፍሉ፣ ሂዶ ሂዶ አንድ ቀን እናንተን ማጎሳቆሉ አይቀርም፡፡ የዓለም አይደላቸውምና፡፡ ምናልባት እናንተ “ተቀላቅያለሁ” ብላቸው ማንነታቸውን እስክታጡ ድረስ ብትኖሩበትም፣ አለም ግን የእርሷ እንዳይደላችሁ ጠንቅቃ ስለሚታውቅ ትጠላችኋለች፡፡ በእናንተ ውስጥ ያለውን ዘር፣ በተለይ ደግሞ የተጠራችሁበትን አምላክ አትወደውም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ይህንን ሀሳብ በአድስ ክዳን ውስጥ አጽንቶልናል፡፡ “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።” (ዮሓ.15፡18-19)

ስለዚህ እስራኤላዊያን ምንም እንኳ ከግብፅ ጋር ተላምደውና ተመቻችተው መኖር ቢጀምሩም፣ ግብጽ ግን በሁለም መንገድ ባሪያ አደረገቻቸው፡፡ አስተሳሰባቸው ሳይቀር ማለት ነው፡፡ የአስተሳሰብ ባርነት ደግሞ ከአካላዊ ባሪነት ይበልጣል፡፡ ለዚህም ነው በታቁ የእግዚአብሄር ክንድ ታግዘው ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ አስተሳሰባቸውና አምልኮአቸው ግን በአግባቡ ነጻ እንዳልወጣ እግዚአብሄር አይቶታል፡፡ ከ40 ዓመት ጉዞ በኋላም እግዚአብሄር ከዚያ የማስለቀቅ ሥራን ቀጥሎበታል፡፡

የሚገርመው ነገር ይህ ነጻ የማውጣት ሥራ የተሠራው በምድረ በዳ በተወለደም ትውልድ ላይ ነው፡፡ ሲወለዱ ጀምረው ጉዞ እየተጓዙ የኖሩ፣ የትውልድ ቦታና ሀገር የሌላቸው የተጓዦች ልጆች፡፡ ለእነርሱ ሕይወት ጉዞ ብቻ፣ የሚኖረውም በመና ብቻ ይመስላል፡፡ ሁላቸውም ወላጅ አባትና እናት ያጡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ግን በምድረ በዳ ላይ ስለሞቱባቸው ስለወላጆቻቸው ሲያስታውሱ ስለ ግብጽ መልካምነትና ሙሴና እግዚአብሄር እያንከራተቱአቸው እንደሆነ ሲናገሩና ሲያጉረምርሙ መሞታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እነርሱ እያጉረመረሙ ሞቱ፡፡ ልጆቻቸው ደግሞ “እኔ የእግዚአብሄር ነኝ” የሚሉበትን የግርዛት ምልክት ሳይቀበሉ ጎልማሶች እየሆኑ ነው፡፡ “በመንገድ ሳሉ ስላልገረዙአቸው ሸለፈታሞች ነበሩና” (ቁ 7) ይላል ጸሓፊው፡፡

ስለዚህ ለዚህ “ተጓዥ ትውልድ” የግርዛትን አገልግሎት እንድሠጥ እግዚአብሄር ኢያሱን አዘዘው፡፡ የተገረዙት ቁስላቸው እስኪድን ድረስ በዚያው በገልገላ ሰፈሩና ቆዩ፡፡ ይህ ግርዛት ፋስካን ለመብላት በቂ ስለሚያደርጋቸው (ዘጸ.12፡43-44፣48) በዚያውም የፋስካን በዓል አከበሩ፡፡

ግርዛት በተለይ በአድስ ኪዳን ውስጥ ላለነው ለእኛም ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አለው፡፡ በአካለዊ ብልት ላይ ስለሚደረግ የቆዳ መቆረጥ ሳይሆን፣ በልብ ግርዛት ይገለፃል፡፡ “የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ” (ቆላ 2፡11)፡፡ በብሉይ ኪዳንም ቢሆን እግዚአብሄር በአካላዊ መገረዝ አልረካም፣ ምልክቱን በአካላቸው ላይ በመውሰድ የእግዚአብሄር መሆናቸውን እያስታወሱ ቢሄዱም ጌታ ግን የሚፈልገውም የልባቸውንም መገረዝ ነበረ፡፡ “እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ፡፡” “… ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።” (ዘዳ. 10፡17፤30፡6፤ኤር 4፡4)፡፡

ይህ የግርዛት መንፈሳዊ ትርጉም በአድስ ኪዳን ተጠናክሮና ጎልቶ በእነ ጳውሎስ ተሰበከ፡፡ “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም “ (ሮሜ 2፡28-29)።

እምነት ከግርዛት ይቀድማል፣ ግርዛትም የእምነት ማሳያም ነበረ፡፡ ሓዋሪያው ጳውሎስ ስለዚህ ነገር ሲያብራራ የአብርሃምን ምሳሌ ወስዶ ነበረ፡፡ አብርሃም “ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥ ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው” (ሮሜ 4፡ 11-12)።

 

እንግድህ የብሉይ ኪዳን ሥርዓቶች ብዙውን ጊዜ ሊመጣ ለነበረው አድሱ ክዳን ጥላ ናቸው (1 ቆሮ 10፡11)፡፡ ለምሳሌ የእስራኤሎች ከግብጽ ምድር መውጣት በአድስ ክዳን የአማኞች በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ከሓጢአት ባርነት ነጻ መውጣት አመልካች ነው፡፡ ፋስካችን የሆነው ክርስቶስ፣ በበግ ተመስሎ፣ “ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።” (ገላ 1:4 በተጨማሪም ዮሃ 1:29፤ 1 ቆሮ 5:7፣ ሮሜ 5፡8 አንብቡ)፡፡

በገልገላ ወደሆነው ታሪክ ስንመለስ፣ እስራኤላዊያን ወንዶቻቸው ከተገረዙ በኃላ፣ የፋስካን በዓል አደረጉ፡፡ (እንከን የለለው ጠቦት ታርዶ፣ ለሰባት ቀናት ያልቦካ እንጀራ ተበልቶ – ዘፀ.12፡14-15)፡፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሞት ለፋስካ በሚታረደው በግ ተመስሎአል፡፡ 1 ቆሮ 5፡7ን ስናነብ፣ “እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና” ይላል፡፡

በዚህ በአድሱ ትውልድ ላይ የነበረ ፋስካን የማክበር ክልከላ አሁን ተነስቶላቸዋል፣የግርዛት ስርዓቱን ከፈጸሙ በኃላ፡፡ እግዚአብሄር “ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ” ብሎአልና በዓሉንም አክብረው በጨረሱት በነጋታው

  1. “የምድርቱን ፍሬ በሉ” (ቁ 11)
  2. “መና መውረድ ቆሜ” (ቁ 12)
  3. እግዚአብሄር ፍታቸው ለነበረው ጦሪነት ተዋጊ መልአክ ላከላቸው፡፡(ቁ 13-15)

የዛሬውን መልእክት ለማጠቃለል፣ እግዚአብሄር ሰዎች ወደ መዳን ይመጡ ዘንድ የሚያዛቸው ትዕዛዛቱ ሲፈጸሙ፣ አምነው የሚታዘዙት ሰዎች በሕይወታቸው ዘርፈ ብዙ በረከቶችን መለማመድ ይጀምራሉ፡፡ እግዚአብሄር ሕዝቡ ለስድብና ለማላገጫ የሚያደርጋቸውን ነውር ይዘው ሲዞሩ አይደሰትም፡፡ የልብ አለመገረዝ ሲኖር ሰዎች ሊኖራቸው የነበረውን ክብርና መቀበል የነበረባቸውን በረከት ሳያዩ ይኖራሉ፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ ሳናምን የሚናቀርባቸውንም ማንኛውንም መስዋዕትና አምልኮ ይጸየፋል፡፡ ነውር አለበትና፡፡ በክርስቶስ ግን ነውራችን ተወግዶ በእግዚአብሄር አብ ዘንድ ተቀባይነት እናገኛለን፡፡ እግዚአብሄርም “ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ፡፡” ይላል፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

 

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *