EventsSermonsTeachingsUncategorized

ትንሳኤ

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ፡፡ ህንን ቀን ስናስታውስና ስናከብር ትልቁ ቁምነገር እግዚአብሄር ለእኛ በግል ስላደረገልን ነገር ማወቅና ማመስገን ስንችል ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ጎልጎታ በሚባል ኮረብታ ላይ በመስቀል ላይ የሞተው እኛን ፍለጋ መጥቶ ነው፡፡ ለመሞትም የፈቀደው እኔና እናንተ እንዳንሞት ስለፈለገ ነው፡፡ ይህንን በዓል ሲናከብር የበዓሉን ዋና የሆነውን ኢየሱስንና ዋጋው የተከፈለላትን ነፍሳችንን ረስተን በተለያዩ ነገሮች መባከን የለብንም፡፡ኢየሱስ ዛሬ ሙት አይደለም፡፡ ኢየሱስ ተነስቶአል፡፡ ኢየሱስ ሁለተኛም ሊሞት አይችልም፡፡ ኢየሱስ “… አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” ብሎአል፡፡(ራእ 1፡17-18)፡፡ጌታ ኢየሱስ ከትንሳኤው ቦኃላ ከተከታዮቹ ከጠየቃቸው ነገሮች የተወሰኑትን ማየት የራሳችንን የትንሳኤው አከባበር ሥርዓታችንን ለመፈተሸ ይረዳናል ብዬ አምናለሁ፡፡

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ፡፡

ይህንን የትንሳኤውን ቀን ስናስታውስና ስናከብር ትልቁ ቁም ነገር እግዚአብሄር ለእኛ በግል ስላደረገልን ነገር ማወቅና ማመስገን ስንችል ነው፡፡ ሌሎችንም እንደእኛው በግል እንደሚወዳቸው ማወቅና መገንዘብም ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ጎልጎታ (ትሪጓመው የራስ ቅል) በሚባል ኮረብታ ላይ በመስቀል ላይ የሞተው እኛን ፍለጋ መጥቶ ነው፡፡ ለመሞትም የፈቀደው እኔና እናንተ እንዳንሞት ስለፈለገ ነው፡፡

መጽሓፉና የአይን እማኞቹም እንደመሰከሩለት ከሞት ሲነሳ ደግሞ የትንሳኤ ተስፋ ለእያንዳንዳችን እንዳለ በማረጋገጥ ነው፡፡ ዛሬ ኢየሱስ ሙት አይደለም፡፡ ኢየሱስ ተነስቶአል፡፡ ኢየሱስ ሁለተኛም ሊሞት አይችልም፡፡ ይህን ደግሞ እርሱ ራሱ ከትንሳኤው ቦኃላ ሲናገር እንዲህ በማለት አረጋግጦልናል፡፡ “… አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” (ራእ 1፡17-18)፡፡

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ በዓል ሲናከብር የበዓሉን ዋና የሆነውን ኢየሱስንና ዋጋዋ የተከፈለላትን ውድቷ ነፍሳችንን ረስተን በተለያዩ ነገሮች መባከን የለብንም፡፡ የሞተልንና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መካከል የተነሳው ጌታችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ምን እንደሚጠብቅ መጠየቅ መልካም ነው፡፡ ይህንን ለማወቅ ደግሞ መጽሓፍ ቅዱሳችንን መፈተሽ አንዱና ዋናው ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሄር የሚናገርበት መንገድ ብዙ ነው፡፡ ቃሉን ማወቅ ግን የጌታን ፈቃድ ከምናውቅበት መንገድ ዋነኛውና መቼም ተዓማንነት ያለው ነው፡፡ ኢየሱስ ተነስቶአል፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው ቦኃላ ወዳኞቹን /ተከታዮቹን ከጠየቃቸው ነገሮች የተወሰኑትን ማየት የራሳችንን የትንሳኤው በዓል አከባበር ሥርዓቶቻችንን ለመፈተሸ ይረዳናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጌታ ምን እንዲናደርግ ይፈልጋል?

1. መጽናናታችንን ይፈልጋል፡፡ መግደላዊት ማሪያም ስለኢየሱስ መሞት እያሰበችና እያስታወሰች ሬሳውም በመቃብሩ ባለመገኘቱ አዝና ታለቅስ ነበረ፡፡ ስለመነሳቱ ገና በትክክል አላወቀችም ፡፡ ቀድሞ ኢየሱስ ከሞት ስለመነሳቱ የተናረውንም ረስታዋለች፡፡ ከትናንት በስቲያ በኢየሱስ ላይ በጭካነ የደረሰው ግፍ አሁን ደግሞ ሬሳውን በመውሰድ የቀጠለ መስሎአታል፡፡ ኢየሱስ ግን ተነስቶአል፡፡ “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት።” (ዮሓ. 20፡15)፡፡ ኢየሱስ ይህንን ያለበት ምክንያት ሕያው ስለሆነ በሙታን መካከል መፈለግ እንደለሌበት ለማመልከትም ነው፡፡ በተጨማሪም ትንሳኤ ስለሆነ ለቅሶ ማብቃት እንዳለበት ለማሳየትም ነው፡፡ እንደተጻፈውና በኢየሱስም እንደተነገረው ቃል ትንሳኤ ሆኖአል፡፡ ኢየሱስና መግደላዊት ማሪያም በአንድ ገጽ ላይ አልነበሩም፡፡ እርሷ በትናቱና ከትናት በስቲያ በነበረው ሁኔታ ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ በብዙም ሓዘን ተጎድታለች፡፡ ኢየሱስ ደግሞ በዚህ ሰዓት በትንሳኤ ጉልበት ተገልጦአልና አሁን ጊዜው የደስታ፣ የድል፣ የሕያውነትና በጽድቅ የመገለጥ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ ነው ከወቅቱ ጋር የማይሄድ ነገር እንዳታደረግ ኢየሱስ የጠየቃት፡፡ በዚያን ወቅት እውነቱን ያወቁ ቅዱሳን መላእክትም በሰማይ እየሆነ ያለውን ሓዘንተኞቹ የሰው ልጆች አውቀው እንድፅናኑ “ስለ ምን ታለቅሻለሽ?” “ሕያውን በሙታንን መካከል የምትፈልጉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ነበረ፡፡

ዛሬም ብዙዎቻችን ከወቅቱ ጋር በማይሄድ የሕይወት ልምምድ ወስጥ ገብተን ራሳችንን በብዙ ሓዘንና ጉስቁልና ጎድተናል፡፡ በትንሳኤው ወቅት የሞትን ሙሾ እናሞሻለን፡፡ ልባችን በደስታ ና በዝማሬ መሞላት በሚገባበት ቀን ሓዘንና መራራነት አሸንፎን ሊሆን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ግን ተነስቶአልና እንድንጽናና ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስ ግን ላዘነች ነፍሳችን “ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” ይላታል፡፡እኔ እንደሆንሁ ሕያው ነኝ፣ አሁን ሥልጣን ተመልሶ በእጄ ገብቶአል፡፡ ሞትም ለዘላልም ተሸንፎአል ይላል (ራእ 1፡17-18)፡፡

2. ሠላም እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ (ዮሃ 20፡19)፡፡ የልብ ሓዘን የሰውን ሰላም ይረብሻል፡፡ ሃጢአት ነግሶ፣ ሃጢአተኛ ፈራጅ ሆኖ በፍርድ ወንበር ሲቀመጥና ጻድቁ ደግሞ ወንጀለኛ ተደርጎ የሞት ፍርድ ሲቀበል ልብን ይሰብራል፡፡ ይህ ብቻ ደግሞ አይደለም፡፡ ምናልባት ኢየሱስ አሳልፎ በሚሠጥበት ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር እንኳ መቆም አልቻሉም፡፡ ሁላቸውም ትተውት ሸሹ፡፡ ስለዚህ ሓፍረትና በደለኝነትም ሊሰማቸው ይችላል፡፡ እውነት ስፍራ አጥቶ ውሸት ደግሞ ተቀባይነት አግኝቶ ስጨበጨብለት እውነቱ የቱ ጋር እንዳለ የሚያውቀውን ያስጨንቀዋል፡፡ ጻድቁና የችግረኞች ወዳጅ የሆነው ኢየሱስ ከመካከላቸው ተወስዶ፣ እንደ ወንጀለኛ የሞት ፍርድ ተበይኖበት እነርሱ እያዩ ያውም በመስቀል ሞት ሲቀጣ ዴቀ መዛሙርቱ ሠላማቸው ተረብሾአል፡፡ ለራሳቸውም የመኖር ዋስትና አጥተዋል፡፡ ስለዚህ በራሳቸው ላይ በር ዘግተው ሲያዝኑ፣ ኢየሱስ በመካከላቸው ተገኝቶ “ሠላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡ሠላም የሌለው ሰው የሥራ ሃላፊነቱን ለመወጣት ይቸገራል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ሠላም ለራቃቸው ዴቀ መዛሙርቱ ሠላምን አወጀላቸው፡፡ ሠላሙን ሰጣቸው፡፡

ዛሬም ኢየሱስ እያንዳንዳችን ሠላም እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ ሠላምንም በእኛ ላይ አውጆአል፡፡ የትንሳኤውን በዓል ስናከብር፣ ኢየሱስ በእኛም እንዲኖር የሚናገረውን ሠላም እንቀበል፡፡ ሠላም ለእናንተ ይሁን፡፡ አሁን እውነቱ ወጥቶአል፡፡ አሁን ሞት ተሸንፎአል፡፡ አሁን ጌታ ይቅር ብሎአችሁኃል፡፡ ሠላም ለእናንተ ይሁን፡፡

3. በግል እንደሚያውቀን እንድናውቅ ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስ በጋራ፣ በብዙ ሰዎች ማካከል፣ ርቆንና እንግዳ ሆኖብን ሳይሆን በግል በእርሱ መታወቃችንን እንድናውቅ ይፈልጋል፡፡ በስማችም ይጠራናል፡፡ ስምህ በኢየሱስ ሲጠራ ስማ፡፡ አንቺም ስምሽ በኢየሱስ ሲጠራ ስሚ፡፡ “ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው” (ዮሃ 20፡16)። ኢየሱስ አሁንም ቢሆን ከሚፈልጉት ሩቅ አይደለም፡፡ በስማቸውም ጠርቶ ሊያጽናናቸው፣ ቀጥሎም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ሊያሳውቃቸው ይፈልጋል፡፡ ከኢየሱስ ትንሳኤ በኋላ መግደላዊት ማሪያም መጽናናትን፣ በግል የመታወቅን ምስክርነትና የትንሳኤን መልእክት የማስተላለፍ ሃላፍነት ተቀበለች፡፡

4. ስለ ትንሳኤው ለሌሎች እንድናሰማ ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስ “… ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።” (ዮሃ 20፡17) ተመልከቱ፣ ምናልባት እኛ ብንሆን “እነዚያን ከሃዲዎች፣ እነዚያን ፈሪዎች፣ ወዘተ. የምንላቸውን ሰዎች፣ ኢየሱስ “ወንድሞቼ” “የአባቴ ልጆች” ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ ኢየሱስ ይህንን ማድረግ የቻለው፣ ችግሩ በመጣ ጊዜ ዴቀ መዛሙርቱ እንደሚያድኑት ስላልጠበቀባቸው ነው፡፡ እንዲያድኑት አልመጣም፡፡ እርሱ ግን ሊያድናቸው፣ ስለእነርሱ ግን ነፍሱ ሊሠጥ እንደመጣ ያውቃል፡፡ እንዲያውም ራሱ ሲያዝ፣ “እኔን ያዙኝ እነዚህ ግን እንዲሄዱ ተውአቸው” ብሎ ነበረ፡፡ ጌታ አንቴን/አንቺን የሚወድህ/ሽ ወይም እኛን የሚወደን እኛ ለእርሱ ከምንውልለት ውሌታ ተነስቶ አይደለም፡፡ ግን እርሱ አስቀድሞ ስለወደደን ውሌታም ስለዋለልን እንጂ፡፡ ስለዚህ ወዳጄ፣ ድካምህን አይተህ፣ የሁኔታን ክብዴት አይተህ ሠላም አይራቅህ፡፡ በኃጢአትና በበደልም ሁልጊዜ ለመኮነን ራስን አሳልፈህ አትስጥ፡፡ ጌታ ይወድሃል፡፡ አንቺንም ይወድሻል፡፡ ወንድሜ፣ እህቴ እያለም ይጠራሃል/ሻል፡፡ ጌታ ግን ከእኛ የሚፈልገው ለሌሎችም ወዳጆቹ መልእክቱን እንድናስተላልፍ ነው፡፡ “ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው።” (ቁ 21)

5. መንፈስ ቅዱስን እንድንቀበል ይፈልጋል። ዮሃ 20፡22 “ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።” ለአንድ ዴቀ መዝሙር (የኢየሱስ ተከታይ) መንፈስ ቅዱስ አስፈላጊው ነው፡፡ ይህንን ስል መንፈስ ቅዱስ እንደ ተጨማሪ ሥጦታ ሳይሆን ዋና እና አስፈላጊ ነው፡፡ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ዴቀ መዛሙርቱን ሲያስተምር መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ እንደሚያስተምራቸው፣ እንሚመራቸው፣ እንደሚያጽናናቸው ተናግሮ ነበረ፡፡ ስለዚህ ዴቀ መዛሙርቱ አሁን ላሉበት አስቸጋሪ ሁኔታም ሆነ ለሚጠብቃቸው ወንጌልን ለዓለም የማደራስ ተልዕኮ የመንፈስ ቅዱስ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም መንፈስ ቅሱስን ሳትቀበሉ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዞአቸዋል (የሓ.ሥ 1፡4)፣ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ እፍ ብሎባቸዋል፡፡ ስለዚህ ከትንሳኤ ቦኋላ ኢየሱስ ወዳጆቹ ትንሳኤውን እንዲያከብሩበት ከሚፈልጋቸው መንገዶች አንዱ መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸውና በእርሱ ቁጥጥር ስር መሆናቸው ነው፡፡ እኛም ዛሬ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ስናከብር መንፈስ ቅዱስን ለመቀበልና በእርሱ ቁጥጥር ስር ዕለት ዕለት ለመሆን መፈለግ አለብን ማለት ነው፡፡

 

ጌታ ኢየሱስ ይባርካችሁ፡፡ መልካም የትንሳኤ በዓል ለሁላችም ይሁን፡፡

በተክሉ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *