SermonsTeachings

መዳን በኢየሱስ

መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

የሐሥ 16፡16-34 ( መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡)

በዚህ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ያለውን ታርክ ለመረዳት በአጨሩ የጳውሎስን አገልግሎት በመቃኘት እንጀመር፡፡

ሓዋሪያው ጳውሎስ በጌታ ሃይልና ተዓምር ሕይወቱ ከአሳዳጅነት ወደ ሰባኪነት ከተለወጠ በኃላ የወንጌል አገልግሎትን ሥራው አድርጎ በየሀገሩ፣ በየመንደሩም እየዞሬ ማስተማር ጀመረ፡፡ እርሱ በሄዴበት ሁሉ ከሰዎች ጋር፣ በተለይ ደግሞ ከአይውዳውያን ጋር ኢየሱስ ራሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመነጋገር ወደ እምነት ሊያመጣቸው ይሠራ ነበረ፡

በዚህ ታሪክ ውስጥም ጳውሎስ ከስላስና ከሉቃስ (የታሪኩ ፀሓፊ) ጋር በፊልጵስዩስ ከተማ ውስጥ ያልፍ ነበረ፡፡ ጳውሎስና ጓደኞቹ በዚህ መንደር ውስጥ ሲያልፉ የመጀመሪያቸው አልነበረም (ቁ 18)፡፡ በመንገዱ ሲመላለሱ ዘወትር የሚያጋጥማቸውና እነርሱም ዝም ብለው እና ያልሰሙ መስለው ያለፉት ጩሄት ነበረ፡፡

የሚሰማው ድምጽ “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው” የሚል ነበረ፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

አንድ በሰውም በክፉ መንፈስም በባሪነት የተያዘች ሴት ልጅ ነበረች፡፡ በታሪኩ ውስት “ገረድ” ተብላ ተጠቅሳለች፡፡ ስሟም ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ምናልባትም ሰዎች በሥራዋ ብቻ ያውቋታል፡፡ በምዋርተኝነት መንፈስ የተያዘችና በጥንቆላዋ (በምዋርቷ) ለጌቶቿ ብዙ ትርፍ ታስገኝ የነበረች ሴት ናት፡፡ በታሪኩ ውስጥ እንደተገለጠው፣ “ጌቶች” እንጂ አንድ ጌታ ብቻ አልነበራትም፡፡ ከዚህም ሕይወቷ ምስቅልቅሉ የወጣ ሴት መሆኗን መገንዘብ አያቅተንም፡፡ የሚታደርገው ነገር፣ ለጥቅቶች የገቢ ምንጭ ሆኖላቸዋል፡፡

ያቺ ሴት (ገረድ) ፈልጋ ወይም ደግሞ በርሷ ላይ ያለው መንፈስ ፈልጎ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ ሁሌ እነሉቃስ በዚያ ሲያልፉ፣ እየተከታተለቻቸው ትመሰክርላቸውና ሰዎች እነጳውሎስን እንዲሰሙ ትመክራቸው ነበረ፡፡ “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው” ትላለች፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነውና፡፡

በእኔ አመለካከት፣ ይህቺ ሴት ነጻነትን የሚትናፍቅ፣ ራሷ ያለችበትና የሚትሠራቸው ለሰዎች መዳን ጠቃሚ እንዳልሆነ የገባት ትመስላለች፡፡

ብዙ ጊዜ በእስራት ያሉ ሰዎች እስራታቸው ክፉ እንደሆነ የማያውቁ አድርገን ማየት ስህተት ነው፡፡ ምናልባት የማያውቁት ሌላ አማራጭ እንዳለና ከዚያም መውጣት እቻላቸው እንደሆን ነው፡፡

ገረድቱ ሁሌ እየተከታተለች ሲትመሰክርላቸውና ሰዎችን ወደ እነጳውሎስ ሲትጠቁም፣ ምናልባት ለራሷ የሚትናፍቀው ነጻነት እንዳለና፣ እርሷ ግን ባሪያ ስነበረች (የራሷ) ስላልሆነች ያንን ምርጫም ማድረግ ስለማትችል ሰዎችን ለመርዳት ይሆናል፡፡ ወይ ደግሞ ለእርሷ ማግኜት የተነሳናትን ምኞቷን ለመናገርም ሊሆን ይችላል፡፡ እርሷ ከሚትናገረው ትንቢት (ምዋርት) ይልቅ እነጳውሎስ የሚሰብኩት ስብከት ለመዳን ጠቃሚ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እነርሱም የሚላኩለት ጌታ እርሷ ከሚታገለግላቸው ጌቶችና ከምዋሪት መንፈስ የሚሻል እንደሆነም ጠቁማለች፡፡ “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው” እያለች፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

የዚህች ገረድ ሕይወት ዛሬም ብዙዎች የሚኖሩት ሕይወት ይመስላል፡፡ እውነቱን እያወቁ፣ ነገር ግን ካሉበት የተለያዩ እስራቶች የተነሳ ራሳቸው ወደ እግዚአብሄር ማቅረብ አይችሉም፡፡ ወይም ብቃቱና ሃይሉ እንደሌላቸው ያምናሉ፡፡ ራሳቸውን ማጋለጥ ካልፈለጉ እንጂ፣ ሲጠየቁ የኢየሱስ መንገድ የእውነት መንገድ እንደሆነ መናገር ይችላሉ፡፡

ይህንን ለሌሎች የሚነግሩትን እውነት ግን ለራሳቸው ለመቀበል ያሉበት እስራትና ባሪነት (የሃጢአት፣ የዝና፣ የገንዘብ፣ የሰዎች፣ የሰይጣን፣ ወዘተ.) ይከለክላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ‹እኔማ ከዚህ በኃላ ተስፋ የለኝም› ይላሉ፡፡ ሌሎቹም ‹እኔንማ እግዚአብሄር ራሱ የሚቀበለኝ አይመስለኝም› ይላሉ፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች፣ ሌሎቹን ወደ ቤተክርስቲያን ሊከው ራሳቸው በችግራቸው ውስጥ ለመቆየት ቤት ይቀራሉ፡፡

አንድ ጊዜ በቦሌ ቡልቡላ ወስጥ ከአንድ ወንድም ጋር (ኢዮብ) ወንገልን ለመመስከር ስንዞር ለአንድ አባት ስለኢየሱስ ነገርናቸው፡፡ ሰውየውም በኦሮሚፋ ነበር ያዋሩንና፣ “አን እጆሌ ባባየቲን ቃባ፣ ኦቱ እሳን ካና ናፍ ባራኒ አካማን ጋማዳ” ስተረጉመው (እጅግ መልከ መልካም የሆኑ ልጆች አሉኝ፡፡ እነርሱ ይህንን ቢያውቁልኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር) አሉ፡፡ ለራሳቸው ግን እንደማያስፈልጋቸው ነገሩን፡፡ ሌሎቹን ወደ ክርስቶስ ሊከው ራሳቸው በችግራቸው ውስጥ ለመቆየት ቤት ይቀራሉ፡፡

ቢሆንም ግን እግዚአብሄር እንደዚህ አይነቶቹን ሰዎች እነርሱ ስለራቸው እንደ ደመደሙት ሳይሆን እነርሱንም ነጻ ማውጣት ይፈልጋል፡፡ ሰዎችም ዝም ቢሉአቸው፣ እነርሱም ራሳቸውን ቢንቁም፣ ባሪያ ያደረጓቸውም ቢበረቱባቸውም እንኳ እግዚአብሄር ግን ቀንበራቸውን የሚሰብርበት ቀን ቀጥሮአል፡፡ አንቴ/አንቺም በዚህ ዓይነት ሕይወት ካለህ/ሽ ጌታ እንደሚመጣልህ/ሽ ጠብቅ/ቂ፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

ይህችን ገረድ ጳውሎስ ለምን ሲያልፋት እንደነበረ አላውቅም፡፡ ምናልባት፣ ስደት ተነስቶ ሊሠሩ የመጡትን ሳይሰሩ እንዳይገድሉአቸው ፈርቶ ይሆናል፡፡ ምናልባትም፣ ይህቺ ለአጋንንት ራሷን ያስገዛችና ከአጋንንት ጋር መሆኗ የገንዘብ መገኛ ምንጭ የሆነው ሴት ለመላቀቅ ፈቃደኛ አደለችም ቢሎ አስቦም ይሆናል፡፡ ምናልባትም ደግሞ፣ እየተከታተለች የሚትጮህባቸው፣ በእነርሱ ላይ ሰዎችን ለማነሳሳት የታሰቤ ነው ብሎ ትቶአትም ይሆናል፡፡ ሴቲቱ ግን እነርሱ በመንደሩ ባለፉ ቁጥር ተከታትላ እነርሱን የማጋለጥ ሥራዋን ከማከናወን አልቦዘነችም፡፡

ይህ ነው እንግዲህ ጳውሎስን ያስቸገረው፡፡ ስለዚህ በእርሷ ሆኖ የሚሠራውን ክፉ መንፈስ በኢየሱስ ስም ገሰፀው፡፡ “ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም “በዚያም ሰዓት ወጣ”።

ይህ ለባሪያይቱ ትልቅ እረፍት ነው፡፡ በመንፈሱ እየታለሉ ወደእርሷ ይሄዱ የነበሩትም የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ጉልበት አዩ፡፡

እኛ አማኞች አንዳንድ ጊዜ እኛንም ሆነ ሌሎችን ከእስራት የሚፈታውን የጌታችን የኢየሱስን ስም በእምነት ባለመጥራታችን ችግሮችና ባሪነቶች ረጅም እድሜ ያገኛሉ፡፡ ጌታ ይቅር ይበለን፡፡

ጳውሎስ በኢየሱስ ስም በማዘዙ፣ አሁን ትልቅ ለውጥ በአከባቢው ሆነ፡፡ የታሰረች ነጻ ወጣች፣ በጥንቆላ የበለጠጉ ተስፋቸው ጠፋ፣ ሰዎች የእግዚአብሄርን ክብር አዩ፣ እነ ጳውሎስ የተበቃዮች ሰለባ ሆኑ፡፡ ጌታ ግን በዚህም ውስጥም ሥራ አለው፡፡

ገረድቱ ነጻ ወጣች፡፡ ለአሳዳሪዎቿ ግን የሴቲቱ ነጻነት አሉታዊነቱ በግልጽ ታይቶአቸዋል፡፡ የገንዘባቸው ምንጭ ደረቀ፡፡ በባሪነት፣ በጭቆና፣ በብዝበዛ፣ በስግብግበነትና በራስ ወዳድነት ያገኙት የነበረው ገንዘብ ዛሬ ነጥፎአል፡፡ ስለዚህም ለበቀል በእነ ጳውሎስ ላይ ተነሱ፡፡ “ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው”

እነዚህ ሰዎች ክሳቸውን በወንጌል መልእክተኞች ላይ ሲያቀርቡ፣ ‹የገንዘባችን ምንጭ ቀረ፣ ድሮ ገንዘብ ሲናገኝበት የነበረው መንገድ ዛሬ ተዘጋብን› ብለው አይደለም፡፡ ይህንን ቢሉ ብዙ ተባባሪ አያገኙም ነበር፡፡ ነገር ግን የዘረኝነትን፣ የሰላም መረበሽን፣ የባሕል መቃወስን፣ በአጠቃላይ ችግሩን የሀገር ጉዳይ አድርገው የክስ አጀንዳቸውን አቀረቡ፡፡ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ” አሉ፡፡

እውነቱን ያላወቀው ሕዝብ ተሰብስበው እነጳውሎስን ማጥቃትና መጉዳት ጀመሩ፡፡ ሀገረ ገዦቹም ተባበሩአቸው፡፡ ስለዚህ ገረፉአቸው፣ መቱአቸው፣ አቆሰሉአቸው፣ ወደ እርስ ቤትም አስገቡአቸው፡፡ ይህም ሳይበቃቸው፣ በእስርቤት እንኳ ልዪ ጥበቃና ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው አዘዙ፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ በውስጤኛው እስር ቤት ታሰሩ፣ እግሮቻቸውም በግንድ ተጣብቆ ተጠረቁ፡፡

ከታሰሩ በኃላ፣ በእስሩ በቆዩ መጠን ሕመማቸውና ስቃያቸው እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡ እነርሱ ግን እኩለ ሌሊቱ ሲመጣ፣ ምናልባትም ሲቃዪ አላስተኛቸው ሲል፣ በዜማ እግዚአብሄርን ያመሰግኑ ነበረ፡፡ ይዘምሩለት ነበር ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ያዳምጡአቸው ነበረ፡፡ የእነርሱ ምስጋና ግን የህመም ማስታገሻ ብቻ ሆኖ እነርሱንና ሌሎችን አላገለገለም፡፡ ግን የእግዚአብሄር ሓይል በአከባቢው እንዲገለጥ አደረገ፡፡ ምድር መናወጥ ጀመረች፡፡ በሮች መከፈት ጀመሩ፣ እስራቶችም ተፈቱ፡፡ እግዚአብሄር በግንድ መካከል የታሰሩ እግሮቻቸው እረፍት እንዲያገኙ፣ በሰንሰለት የታሰሩ እጆቻቸውም እንዲፈቱ አደረገ፡፡ የእነርሱን ብቻ ሳይሆን በእስርቤቱ የታሰሩ ሁሉ ነጻነት ተሰማቸው፡፡ እነጳውሎስ የመሰከሩለት፣ የተገረፉለትና የታሰሩለት፣ ታስረውም እያሉ የዘመሩለት ጌታ ሕያውና በሁሉም ላይ ስልጣን ያለው መሆኑ ታወቀ፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

የእስርቤቱ ጠባቂ፣ እጅግ ፈራ፣ በሆነው ነገር የሞት ድባብ ሸፈነው፡፡ ‘እስረኞቹ አመለጡ ማለት ለእኔ ከሞት ማምለጥ አይቻልም’ ብሎ አሰበ፡፡ የእግዚአብሄርን መንገድ ለሰዎች የሚናገሩትን ጻድቃን ያልማሩ ሰዎች፣ እርሱን ደግሞ ቁጭ ብለው ስለሁኔታው እንደማይረዱለት አሰበ፡፡ ስለዚህ እነርሱ መጥተው ከሚገድሉኝ ብሎ፣ ራሱን ለማጥፋት ተነሳ፡፡

ጳውሎስ ግን ከዚህ ምስክን ዘበኛ ሞት ለማንም ተርፍ እንደማይገኝ ያውቅ ነበረ፡፡ ለእርሱም የክርስቶስ ፍቅር ሙሉ እንደሆነ አወቀ፡፡ ስለዚህ ራሱን እንዳይጎዳ፣ ድምጹን ከፍ አድርጎ አስጠነቀቀው፡፡ ያመለጠ እስረኛም እንዳልነበረ ነገረው፡፡

ጠባቂው መብራት አስመጥቶ ሲመለከታቸው፣ እንደ ትናንቱ ወንጀለኞች አድርጎአቸው ሳይሆን፣ የመዳንን ምስጥር የሚያውቁ፣ መንገዱንም የሚያሳዩ፣ ተሹመው እንደምንቀሳቀሱ ጌቶች አድርጎ ቀረባቸው፡፡ ለመዳንም ምን ማድረግ እንደሚገው እንዲመክሩት ጠየቃቸው፡፡ ”ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ኣላቸው።

ጳውሎስና ስላስም የትናንቱን ቁስል፣ እስራት፣ ልዩ ቁጥጥር አላስታወሱበትም፡፡ እርሱም ቤተሰዎቹም፣ በጌታ በኢየሱስ በማመን እንደምድኑ መከሩት፡፡ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” አሉት። የእግዚአብሄርንም ቃል ለእርሱና ለቤተሰቡ ነገሩአቸው፡፡ እርሱና በቤቱ ያሉ ሁሉ፣ ከአዋቂ እስከ ሕጻን፣ ከባለቤት እስከ ባሮች፣ ሁሉም ተጠመቁ፡፡ ሰዉየውም በቤቱ ቁስላቸውን አጠበላቸው፡፡ ”በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ”፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ትኩረት ልንሠጣቸው የሚገቡን እውነቶች አሉ፡፡

  1. እግዚአብሄር ወደ ሰዎች መንገድን ማውጣት ስለሚፈልግ ሁኔታዎችን ይፈቅዳል፡፡ በሰውና በአጋንንት ባሪያ የተደረገች ገረድ ነጻ እንድትወጣ እነጳውሎስ ለብዙ ቀናት በአንድ መንገድ መመላለስ ነበረባቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‘ለምን ሁሌ በዚህ አይነት ሕይወት እኖራለው፣ በዚህ መንገድ እመላለሳለሁ?’ እንላለን፡፡ ጌታ ግን ምክኒያት አለው፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡ ምናልባት እኛ ልንወስዳቸው የሚገቡንን እርምጃዎች ባለመውሰዳችን ፈቀቅ ማለት አቅቶን ይሆናል፡፡ የእስር ቤት ጠባቂውና እስረኞቹ እነጳውሎስ በዚያ ባይገኙ የወንጌልን ቃል የመስማትና የመዳን ዕድላቸው ጠባብ ነበረ፡፡ እርሱና ቤተ ሰዎቹ ይድኑ ዘንድ ጳውሎስና ስላስ ወይኒ መጣል ነበረባቸው፡፡
  2. የክርስቶስ ስም ነገሮችን መቀየር ይችላል፡፡ ስሙ የታሰሩትን ይፈታል፡፡ በክፋት መናፍስት ላይም ጉልበት አለው፡፡ ስለዚህ በአክብሮትና በእምነት መጠቀም ሁሌም ያስፈልጋል፡፡
  3. ጥቅት የራሳቸውን ጥቅም ፈላጊዎች በውሸት አጀንዳ/ክስ ሕዝብን ከጎራቸው ቢያሰልፉ መገረም የለብንም፡፡ ብቻ እኛ ለእግዚአብሄር ታማኞች መሆን አለብን፡፡ እግዚአብሄር ራሱ እውነቱን ለማውጣት ይመጣልና፡፡ በተለይ ዛሬ ባለንበት ዘመን ጻድቁ ወንጀለኛ፣ ወንጀለኛውም ጻድቅ ተደርጎ የሚገለጥበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ተስፋ ሳንቆርጥ፣ በእግዚአብሄር መታመናችንን መቀጠል ያስፈልገናል፡፡
  4. የእግዚአብሄር ጸጋ በመከራ ውስጥም ሆኖ ለመዘመር ጉልበት ይሰጣል፡፡ በእርሱ ጸጋና ፍላጎት የሚደረግ ዝማሬ ደግሞ ምድርን ያናውጣል፣ እስራቶችንም ይፈታል፡፡ ጌታንም በበለጠ ያስከብረዋል፡፡
  5. መዳን በክርስቶስ እንጂ በሌላ በማንም የለም፡፡ ይህንን እውነት ሁሌም ማስታወስ፣ ለሚጠይቁን መናገር፣ አድሉ ባገኘንበት በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ መመስከር ይገባናል፡፡
  6. እግዚአብሄር ሰዎችን ሁሉ ይቀበላል፡፡ ታናናሾችን፣ ታላላቆችን፣ ባሮችን፣ ጌቶችንም፡፡ ስለዚህ ወንጌልን ለሰዎች ሁሉ ለማድረስ መስራት የእያንዳንዳችን ኃላፍነት ነው፡፡ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው፡፡

ጌታ በጸጋው ይርዳን፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *