Sermons

ለራሳችሁ ተጠንቀቁ

ለራሳችሁ ተጠንቀቁ

ማር 13 1-13 (ለራሳችሁ ተጠንቀቁ)

ኢየሱስ ከመቅደስ እየወጣ እያለ፣ አንድ ሰው ኢየሱስ የመቅደሱን የግንባታ ድንጋይ አንድመለከትና እንድደነቅ ፈልጎ አሳየው፡፡ “መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ” አለው(ቁ1)፡፡

ሰውየውንና ሌሎችንም ሰዎች የሚያስገርመው፣ ሕንፃው እንዴት ተደርጎ ተውቦ እንደተገነባ ማየት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን የዛሬውን የግንባታ ሁኔታ ሳይሆን የሕንፃውን መጨረሻ ይመለከት ነበር፡፡ አሁን ታላቅ ግን ሳይቆይ ትቢያ እንደሚሆን፡፡ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አላቸው፡፡

ከዚህን በፊት ኢየሱስ ይህኑን መቅደስ በተመለከተ ያደረገውና የተናገረው ነገር ነበረ (ማር 11፡15-17)፡፡ ውስጡ በሚነግዱና በሚለውጡ ሰዎች የተሞላ፣ የጸሎት ቤት መሆኑ ቀርቶ የሌቦች ዋሻ እንደሆነ ተናግሮአል፡፡ ከዚህም የተነሳ ጅራፍ አበጅቶ ገርፎ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚነግዱትን አስወጥቶ ነበረ፡፡ ቤተ መቅደስን አግባቢነት በሌለው መልኩ ይጠቀሙበት ነበርና፡፡

ስለዚህ  ይህንን ጥያቄ (የሕንጻዎችን ግንባታ በተመለከተ) ሲጠየቅ፣ የዚህ መቅደስ ውስጡና ውጩ ለኢየሱስ አድስ አልነበረም፡፡ ግንባታው በደንምብ አምሮና ተውቦ ተገንብቶአል፤ ውስጡ ግን የረከሰና ለተሰራለት ዓላማ መዋል ያቃተው ሆኖአል፡፡ ኢየሱስም ሕንጻዎቹ በውጪ በሚታየው ውበት ብቻ ተደንቆ አንደማይቀጥሉና አንድ ቀን እንደሚፈርሱ ተናገረ፡፡

ኢየሱስ ይህንን ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ይሰሙት ነበርና ትንቢቱ መቼ እንደሚፈጸም ጠየቁት፡፡ ሲጠይቁት ግን በአደባባይ ማድረግ ስላልፈለጉ ወይም ስለፈሩ፣ ለብቻው ነበር ያናገሩት፡፡  ከጥያቄአቸው እንደምንረዳው ኢየሱስ ስለ ቤተመቅደሱ መፍረስ የተናረውን ከዓለም መጨረሻ ጋር አምታተው ነበር፡፡ በዚህ ክፍል ግን ኢየሱስ ስለማምታታቸው አልወቀሳቸውም ወይም ደግሞ ያንን ልዩነቱን ማብራራቱ ላይ ረጅም ጊዜ ሲወስድ አንመለከትም፡፡ ይልቁንስ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ፣ ሊሆን ያለውን አጠቃላይ ሁኔታና እነርሱ ደግሞ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ተናገራቸው፡፡

የኢየሱስ ዓላማ የእውቀት ፍላጎታቸውን ማርካት ሳይሆን፣ በሕይወታቸው ሊከሰት ካለው ነገር ጀምሮ በዓለም ላይ ሊሆን ላለው ነገር ምን ዓይነት ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባቸው ተናገረ፡፡

ዛሬም ቢሆን የእግዚአብሄርን ቃል ስንሰማም ሆነ ሁኔታዎችን ስንመለከት ከማወቅ ፍላጎት የተነሳ ብዙ ነገር እንጠይቃለን፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ‹እኔ ምን ላድርግ፣ ለእኔ ይህ መልዕክት ምን ማለት ነው› ብለን ከራሳችን ጋር አናዛምድም፡፡

በዚህ ቦታ ኢየሱስ መውሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄ ዳጋግሞ ሲያስጠነቅቃቸው እንመለከታለን፡፡

በተለይ ኢየሱስ እንዳያስቱአችሁ፣ አትፍሩ፣ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፣ አትጨነቁ የሚሉትን ቁልፍ ቃላት በዚህ ክፍል ተናግሮአል፡፡

ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። (ቁ.5)

“ብዙዎች፦ እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። “ ይህ ማለት ሓሰተኛ ክርስቶሶች ይነሳሉ ማለት ነው፡፡ በእኔ ስም ብዙዎችን ያስታሉ፡፡ ብዙዎችንም ያስከትላሉ፡፡

ዛሬም ባለንበት ዓለም በብዙ ሀገራት ክርስቶስ ነኝ እያሉ የተነሱ ብዙዎች አሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ክርስቶስ ማለት የተቀባ ማለት ነው፡፡ ብዙዎች ደግሞ ቀጥታ የግርኩን ስያሜ ባይጠቃሙም፣ በየአከባቢው ባለው ቋንቋ እየተጠቀሙ  “እኔ የተቀባው ነኝ” በምል ስም ሰዎችን ከእውነተኛው ክርስቶስና ከቃሉ የሚመልሱ አሉ፡፡

ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ አላቸው፡፡ ውሸተኛ መሆኑ የሚታወቅ ሰው መጥቶ አድስ ነገር ቢነግረን እንደማንሰማው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን አሳች የሚባለው፣ ራሱን እየለወጠ፣ ንግግሩን፣ አድራሻውን፣ ጉርብትናውን፣ አጋርነቱንና ስሙን እየለዋወጠ እውነት በመምሰል የሚገለጠው ነው፡፡

በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ

ሌላው ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ “ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ” የሚል ነው (ቁ 7)፡፡ ኢየሱስ ይህንን በሚናገርበት ጊዜም ሆነ ከዚያን በፊት በምድርቱ ዙሪያ ላይ ጦርነቶች  ነበሩ፡፡ ግን ኢየሱስ ማለት የፈለገው የጦሪና የጦሪነት ስፋትና ብዛት ከተለመደው ውጪ ሆኖ ይሰማል፡፡ አንዳነዶቹ ጦሪነቶች በራሳቸው የዓለም መጨረሻ ሆነው የሚቀርቡበት ጊዜ አሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ከተሰተፉበት ሕዝቦችና ብዛት እንዲሁም ከሚጠቀሙበት የጦሪነት መሳሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ይህንን በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ ብሎ ነበር የተናገረው፡፡ ምክንያቱም “ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው።” የዓለም መጨረሻ “አብ የወሰነው ቀንና ሰዓት ነው” እንጂ የዓለም ነገስታት በወሰኑበት ሰዓት አይሆንም (ማቴ 24፡36)፡፡ ስለዚህ “አትደንግጡ!” ይላል ጌታ ኢየሱስ፡፡

ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዳይደነግጡ የሚያስጠነቅቀው በምድር ላይ የሚሆኑ ነገሮች ቀላል ስለሆኑና አማኞችን ስለማይነኩ አይደለም፡፡ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል” ብሎአልና፡፡ በዚህ የተዘረዘሩትን ችግሮች ስንመለከት ብዙ ማለት ብቻልም፣ ኢየሱስ ማለት የፈለገው ግን እነዚህም እያሉ ዓለም ትቀጥላለች፡፡ “አብ እስከ ወሰነው ሰዓት” ችግሮች ይህችን ዓለም ፈጽሞ ወደ አለመኖር ሊያመጧት አይችሉም፡፡ ሆኖም ግን “እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።” መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ቀድሞ የሚሄዱና የሚያስደነግጡ ናቸው፡፡ እናንተ ግን አትደንግጡ፤ ይልቁንስ ሌላ ማድረግ የሚባችሁ አለ፡፡ “ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና (ማቴ 24፡44)።” እንዴት?

ለራሳችሁ ተጠንቀቁ

ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ወይም በኢየሩሳለም ወይም ደግሞ በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱ ነገሮችን ሰምተው እንዲደነቁ ወይም እንዲፈሩ አልፈለገም፡፡ ለራሳቸው መዘጋጀትና መጠንቀቅ እንዳለባቸው ግን መከራቸው፡፡ “እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።” (ቁ.9)

ይህ ማስጠንቀቅያ የኢየሱስ ተከታዮች በሚደርስባቸው ማንኛውም ነገርና በደረሱበት ማንኛውም ቦታ መልእክት ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው፣ የተቀበሉትን ወንጌል ከመስበክ ወደ ኋላ እንዳይመለሱና መልእክተኞች መሆናቸውን እንዳይዘናጉ የሚያሳስብ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮቻቸው ወይም መከራዎቻቸው በሌላው ጊዜ ወደማይደርሱበት ( አክሰስ ወደማያገኙበት)  መድረሻ /አክሰስ ማግኛ መንገዶች ናቸው፡፡ “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” ብሎአልና፡፡

ነገስታትና የህዝብ ታላላቆች ወደ አገልግሎታቸው መጥተው ካልሰሙ እነርሱ ደግሞ በክስም ቢሆን ሲሄዱ እውነቱን መናገር አለባቸው፡፡ የሓዋሪያው ጳውሎስ አገልግሎት ይህን በደንብ እንድንገነዘብ ይረዳናል፡፡(የሓ.ሥ 26)

ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ

“ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።” ይህ ማሳሰቢያ የኢየሱስ ተከታዮች ሁልጊዜ በራሳቸው ሳይሆን በጌታ መታመን አንዳለባቸው መስገንዘቢያ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዳለ፣ መንፈስ ቅዱስም እንደሚመራቸውና መናገር ያለባቸውን እንደሚያቃብላቸው ያረጋግጥላቸዋል፡፡ ዛሬም ሰዎችና ሁኔታዎች ወደማንፈልጋቸው ቦታ ሲወስዱን መታመን ያለብን በእግዚብሄርና በመንፈሱ መሆን አለበት፡፡

እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናጽ ያስፈልጋችኃል

ስደት መልኩን እየቀያየረ ልደርስባችሁ ይችላል፡፡ የሩቁ ስትሉ ከቤተሰብ፣ ከመንግስት ስትሉ ከበተሃይማኖት፣ ከሌሎች ሓይማኖቶች ስትሉ ከራሳችሁ በወንድሞች ስለ ስሜ መጠላት ይመጣበችሁኃል፡፡

“ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” (ቁ 12-13)።

በዚህ ክፍልና በሌሎችመ የመጽሓፍ ቅደስ ክፍሎች አንደምንመለከተው የክርስቲናችም ሆነ የአገልግሎታችን ዋና ዓላማ የራሳችንና የሌሎችም መዳን ነው፡፡ ስለዚህ የሚሆነው ማንኛም ነገር በዘላለማችን ላይ አሉታዊ ተጽኖ እንዳያመጣ መጠንቀቅ ነው፡፡ ነፍሳችንን መጉዳት የለብም፡፡ ከመከራ ለማምለጥ ክርስቶስንና ትምህርቱን ክደው ዘላለምን ደግሞ ከእርሱ ጋር ማሳለፍ አይቻልም፡፡ “በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል (ሉቃ 9፡26።” ስለዚህ በየደረስንበትና በሚደርስብን በማናቸውም ሁኔታ ከጌታ ጋር መቀጠላችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ጌታ በጸጋው ይርዳን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ  

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *