Sermons

የሚያስፈልገው ግን

የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነውMary hath chosen that good part, which shall not be taken away from her

Luke 10:38-42 (የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው።)

38 ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። 39 ለእርስዋም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፥ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች። 40 ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው። 41 ኢየሱስም መልሶ፦ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ 42 የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።

የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡ማርታ በመንደርዋ በቢታኒያ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ለየት ያለ ነገር አድርጋለች፡፡ ምናልባት እንግዶችን መቀበል የሀገሩ ባህል ቢሆንም ማርታ ግን ኢየሱስን በቤትዋ ተቀበለችው፡፡ ማርታ ኢየሱስን ማሳረፍና ማስደሰት ትፈልጋለች፡፡ ኢየሱስ ተጉዞ ሲመጣ በቤትዋ እንዲያርፍና በፍቅር ተቀበለች ማለት ነው፡፡

ዛሬ ማናችንም እንደምናደርገው፣ እንግዶችን ወደ ቤታችን ከተቀበልን በኋላ እነርሱን ለማስተናገድ ሽር ጉድ እንደምንለው እርሷም ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሁም ኢየሱስን ለማየትና ለመስማት አብረውት የገቡትን ሰዎች ለማስተናገድ ብዙ ትደክም ነበር፡፡ በኢየሱስ አገላለጥ ማርታ የምትባለው ይህች ሴት ብዙ ትጨነቅና ትታወክ ነበረች፡፡ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡

ይህንን “ መጨነቅና መታወክ” እንዴት ልንረዳው እንችላለን? ለእንግዶች ሁሉ የሚዳረስ ቦታ፣ ምግብ፣ መጠጥ/ውሃ፣ መመገቢያ እቃ/መጠጫ መኖሩን መዳረሱን ለማረጋገጥ ወዲህ ወዲያ ትላለች፡፡ እንግዶቿን በአግባቡ ለማስተናገድና ለማስደሰት ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ክፉም ስህተትም አይደለም፡፡ በየጊዜው ስለምናደርገው ለእኛም ሊገባን የሚያስቸግር አድስ ነገር ነው ብዬ አላስብም፡፡ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡

እህት ማርታ በጣም ትወተውታለች፣ ሊረዷት የምችሉ እጆችንም በጣም የምትፈልግበት ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም ግን ማርታ በዚያን ጊዜ አንድ እንግዳ የሆነ ነገር አየች፡፡ እህቷ ማሪያም በሚያስደንቅና ጥያቄ በሚፈጥር መልኩ ፈታ ብላ ከእንግዶቹ አንዱ በሆነው በኢየሱስ እግር ስር ቁጭ ብላለች፡፡ ማርታ በማሪያም ድርግት ብትበሳጭም፣ የተቀመጠችው ግን ከማርታ እንግዶች ዋነኛው በሆነውና ሌሎችም በእርሱ ምክንያት በተሰበሰቡት በኢየሱስ እግር ስር ነበርና በቀጥታ ማርታን መቆጣት የቻለች አይመስለኝም፡፡

ስለዚች ታናሽ እህቷ ማርታ ወደ ኢየሱስ ቀርባ እርሱ ማሪያምን እንድልክላት መጠየቅ አሰበች፡፡ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡ ማርታ በማሪያም ተረጋግታ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን የኢየሱስን ችግሯን አለመረዳት የተገረመችም ትመስላለች፡፡ ስለዚህ ለጥያቄ ወደ ኢየሱስ ሲትቀርብ “ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት” አለችው፡፡ ከንግግሯ እንደምንረዳው፣ “ለምን ችግሬን፣ ድካሜን፣ብቸኝነቴን…” አላየህልኝም? “ ማለቷ ነው፡፡ ከዚያም ተቀባይነት ያለውን ነገር እንዲያደርግ ኢየሱስን መከረችሁ፣ ”አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት” በማለት፡፡

የታሪኩ ዘጋቢ ሁኔታውን ሲመዘግብ “ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች” ይላል፡፡ አገልግሎት ሁልጊዜ ድካም አለው፣ ራስን መሥጠት አለበት፣ የራስን መተው አለበት፡፡ ደግሞ ሲበዛ እጅግ አባካኝ፣አድካሚ፣ አስጨናቂ እና አዋኪ ሊሆን ይችላል፡፡የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡

ያ ማርታ ላይ የደረሰው ዛሬ ደግሞ በእኔና በእናንቴ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዲህ ሲሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ከእህቷ እርዳታ አለማግኘቷ በማርታ ላይ ሥራን ብቻ ሳይሆን ምናልባት ተረጋግታ በአንድ ልብ እንዳትሠራ ሳያረጋትም አልቀረም፡፡ ስለተናደደች። የተረሳችና ስለእርሷ የሚያስብ ሌላ እንደሌለ (ኢየሱስን ጨምሮ) አድርጋ ማሰብ ጀምራለች፡፡ እንግዳ ጋብዛ በእንግዶቹ ፊት ደግሞ ከእኅቷ ጋር መጣላትም አያምርባትም፡፡ መፍትሄው እንደምንም ብላ ኢየሱስን ራሱ መጠየቅ ሆኖ አገኘችው፡፡ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡

አውቀንም ቢሆን ሳናውቅ ጥያቄዎቻችን ይዜን ወደ ኢየሱስ መቅረብ መልካም ነው፡፡ እርሱ የመፍትሄ ሃሳብ አለውና፡፡ ትክክለኛ ፈራጅም ነው፡፡ እኛ በፍርዳችን እንሳሳታለን፡፡ እርሱ ግን ሁሌ ትክክል ነው፡፡

ኢየሱስ የማርታን ጥያቄ ሰምቶ ሲመልስ “ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” አላት። ኢየሱስ ምን ማለቱ ነው?

ማርታ እንግዳ ተቀባይ ናት ግን በተሻለ መልኩ እንግዳ መቀበል የሚችልና አቂሙ ያለው ስለሚኖር እንግዳ ተቀባይነቷ ለማርታ ብቻ ሆኖ የሚቀር አይደለም፡፡ ሌሎችም ማርታ ማድረግም፣ ማቅረብም ፈልጋ የምትታወክበት ነገሮች ሁሉ በሌላ ሰው ሊወሰድባት ይችላል፡፡ ግን ደግሞ በቤቷ ያለው ዕድል ምናልባት ሌሎች ሊያገኙት የማይችሉት ነገር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዕድል ተጠቅማ ለራሷና ለሌሎች ሊጠቅም የምችልን ነገር ከኢየሱስ መስማት/መቀበል አለባት የሚል ሃሳብ አለው፡፡

ጥቂቱንና አንዱን ነገር ሳታውቅ ማርታ በብዙ ነገር ትለፋለች ማለት ነው፡፡ የማሪያምን ሁኔታ ሲገልጽ ደግሞ “ምርጫ” አድርጋለች ነው፡፡ ያገኘችውን መልካም ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም፡፡ ይህ የማሪያም ምርጫ አይወሰድባትም፡፡

ማርታ ኢየሱስን ወደ ቤቷ ጋብዛለች፣ ይህ መጋበዝ/መቀበል ለማሪያምና ለሌሎች ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ቁጭ ብለው ከእርሱ ለመስማት ልዩ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ማርታ ራሷ ግን ከአገልግሎት ብዛት የተነሳ ከኢየሱስ የመስማት ዕድል እያገኘች አይደለም፡፡ በተጨማሪም፣ ማርታ የአገልግሎቷን ቀልጣፋነት ለማሻሻል ማሪያም ከተቀመጠችበት የኢየሱስ እግር ተነስታ ወደ እርሷ እንትመጣ ፈልጋለች፣ ጠይቃለችም፡፡ ይህ ፍላጎቷና ጥያቄዋ በኢየሱስ መልስ ሲሰጠው ችግሩ የማሪያም ሳይሆን የማርታ ነበረ፡፡ ማርታ ወደ ማሪያም ቦታ መምጣት እንጂ ማሪያም ወደ ማርታ መሄድ የለባትም በዚያን ግዜ፡፡ ይህንን ሲናነብ ቤተሰብ መተጋገዝና መረዳዳት የለበትም ማለት አይደለም፡፡ የመልእክቱ ዋና ሓሳብ ግን አገልግሎታችን ነፍሳችንን ሊያከሳትና ሊጎዳት አይገባም ነው፡፡ ነፍሳችንን የሚያስፈልጋት ደግሞ ከጌታ መስማት ነው፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ “እኔን ስሙ በሕይወት ትኖራለችሁ” ብሎአል፡፡ “እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡” (ሮሜ 10፡17) “ እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” (1 ጴጥ 2፡1-3)፡፡

ኢየሱስንና ሌሎችን ሰዎች እግዚአብሄር በሰጠን ጸጋ እና አቅም ማገልገል አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ አገልግሎታችን ከጌታችን ራሱ እንዲነጥለን መፍቀድ የለብንም፡፡ ለዚህም እግዚአብሄር ይርዳን፡፡

ኢየሱስ “ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፡፡” ብሎ ሲናገር “እኔን መስማት ለእኔ ምግብና መጠጥ ከመስጠት” ይሻላል ማለቱ ነው፡፡ እግዚአብሄርን መስማት ለእርሱ ከምናቀርበው መስዋዕት ይበልጣል፡፡ ኢየሱስ ራሱ ሲናገር “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ” ብሎ ለተከታዮቹ ሲናገር ግራ ገብቶአቸው ነበር፡፡ እርሱ ግን “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” አላቸው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል ሲሰማና ሲያደርግ ኢየሱስ ከተሰጠው ማንኛውም አገልግሎት የበለጠ ይደሰትበታል ማለት ነው፡፡

እርሱ ሲናገር ልባችን እና ሃሳባችንን ሰጥተን እንድንሰማው ጌታ እያንዳንዳችንን ይርዳን፡፡ እግዚአብሄር ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *