Sermons

ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት

የተወደድህ/ሽ አንባቢ ሆይ፣ ኢየሱስ ለጥያቄህ/ሽ ሲመልስ ግን የመቀበሉና የማስተናገዱ ውሳኔ ለአንቴ/ለአንቺ የተተወ ይሆናል፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለምትፈልግ ነፍስ ዛሬም እግዚብሄርን በፍጹም ልብ የመውደድ ጥያቄ ይቀርብላታል፡፡ የእግዚአብሄርንም የጸጋ ሥጦታ በነጻ እንዲቀበል ይጋበዛል፡፡ አንቴም ድነትህን ለመግዛት አትቃጣ፣ ነጻ ነውና አምነህ ተቀበለው፡፡ EECMY, ECMYIS, Mekane Yesus in Scotland, Mekane Yasus, Ethiopian Church in Glasgow, Scotland, Ethiopian Christina Community, Evangelical Church, Lutheran chuch in Glasgow, Scotland. we meet in St George's Tron Church, Church of Scotland, city center. Christian family, infant baptism is also practiced here. Eritrean Christian church from Lutheran chuch of Eritrea. Mark 10:23-31, Glasgow Mekane Yesus, Glasgow Ethiopian Christians, Glasgow Evangelical church, Mekane Yesus

ማር 10፡23-27 ( ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት )

23 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን፦ ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው።

24 ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ፦ ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው።

25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው።

26 እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው፦ እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ።

27 ኢየሱስም ተመለከታቸውና፦ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ።”

በዚህ የወንጌል ክፍል ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን የሚያስደንቅ ቃላት ተናገረ፡፡ “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል?” ብሎ፡፡ ኢየሱስ ለምን እንዲህ አለ? ምንስ ለማለት ፈልጎ ነው?

የክፍሉ አውድ

ከቁ 23 ከፍ ብለን እንደምናነበው፣ አንድ በዕድሜው ወጣት የሆነ ሀብታም ሰው ወደ ኢየሱስ ጥያቄውን ይዞ መጥቶ ነበር፡፡ ሰውየው ይዞት የመጣውን ጥያቄ ስንመረምር፣ ኢየሱስ የሚፈልገው ዓይነት፣ መልሱም በኢየሱስ ዘንድ ያለና ዛሬም እያንዳንዱ የሰው ልጅ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው – ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመግባት፡፡

ሰውየው ምድራዊ ኑሮው የተሟላለት ሰው እንደሆነ ከንግግሩ መረዳት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም፣ በእግዚአብሄር ያምናል፣ የብሉዕ ክዳን ህግን ጠንቅቆ የሚያውቅና እየተለማመደ ያለ ሰው ነበረ፣ በምድር ላይም የተትረፈረፈ ሀብት ነበረው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ሀብቱ የእግዚአብሄር በረከት ምልክት እንደሆነ እርሱም ሆነ በዘመኑ ያለው ማህበረሰብ ይቀበል ነበረ፡፡ ስለዚህ ሰዎችም ሲያዩት፣ እርሱም ደግሞ ራሱን ሲመለከት መልካምና የተባረከ ሰው ነው፡፡

ስለ ጥያቄው

ሆኖም ግን በአይምሮው ውስጥ የሚመላለስ ትልቅ ጥያቄ ተፈጠረበት፡- ‹የዘላለም ሕይወትን እንዴት ልውረስ?› የሚል፡፡ ስለዚህ ነው “የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ኢየሱስን ሊጠይቅ የቻለው፡፡

ይህ ጥያቄ መቼ እንደ ተፈጠረበት አናውቅም፡፡ ምናልባት የረዥም ጊዜ ጥያቄው ነበረ፡፡ መናልባትም ደግሞ ስለኢየሱስ ሲሰማና ኢየሱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ሲሰማ የአስተሳሰብ ስርዓቱ ተዛብቶበትና መሠረት አድርጎት የነበረው የሃይማኖት ርዕዮተ ዓለም ተደርምሶ ስለራሱ የዘላለም ደህንነትን ስጋት ገብቶት ሊሆን ይችላል፡፡ በበኩሌ ሁለተኛው ሃሳብ እውነት ይመስለኛል፡፡

የእግዚአብሄር ቃል መስታዋትነት

ምንም ዓይነት ሃይማኖት ቢኖረውም፣ በየትኛውም ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ሥርዓትና መመዘኛ ከብዶ ቢታይም፣ ሰው ወደ እግዚብሄር ቃልና ሓሳብ ሲመጣ፣ እውነተኛ ማንነቱን ያየዋል፡፡ ይህም ደግሞ ኃጢአተኛ መሆኑን ነው፡፡

ምናልባት ሰዎች ደግነታችንን፣ ንግግራችንን፣ ቸርነታችንን፣ ለሰዎች ያለንን ርህራኤ፣ ክፋትን መጸየፋችንን፣ ወዘተ. አይተው ሊያሞግሱን፣ ሊያከብሩንና ልዩ ፍጥረት አድርገው ሊያዩን ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ደግሞ እኛ ስለራሳችን ባለን አስተሳሰብ ላይ ጫና ሊያመጣ ይችላል፡፡

ወደ እግዚብሄርና ወደ ቃሉ ስንመለስ፣ ስንጠጋና በእርሱ መስተዋት ውስጥ ራሳችንን ስንመለከት ግን በትክክል የሆነውንና ምን እንደምንመስል፤ ነገሮችን ለምንና እንዴት እንደምናደርግም ጭምር በግልጥ እናየዋለን፡፡

ይህ ደግሞ ለንስሃና ለመመለስ እድሉን ይሰጠናል፡፡ በተለይ ደግሞ በራሳችን ላይ ያለንን መታመንና በከንቱ መታበይ ትተን፣ የእግዚአብሄርን ምህረትና ቸርነት እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የተሰጠንን ነጻ ስጦታ ለመቀበል ያዘጋጀናል፡፡

በማርቆስ 10 ውስጥ ታርኩን የሚናነበው ሰውዬ፣ ወደ ኢየሱስ ከቀረበ በኃላ፣ ትልቁንና መሠረታዊውን ጥያቄ ነበር የጠየቀው፡፡

የዘላለም ሕይወት በእግዚአብሄር ቸርነትና ጸጋ የሚገኝ ሥጦታ ነው።

በቁ 21 ላይ እንደምናነበው ኢየሱስም ሰውየውን “ተመልክቶ ወደደው”፡፡ ኢየሱስ የሰውየው ሃብታምነት፣ ወጣትነት፣ ሃይማኖተኝነት ወይም ጥያቄ ይዞ መምጣት ሳይከለክለው “ተመልክቶ ወደደው”፡፡ ይህ ሰው ሕይወት ፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶአል፡፡ ኢየሱስም ወደደው፡፡ ኢየሱስ ማንንም አይጠላም፡፡ ወደ እርሱ የመጡትን ሁሉ በፍቅር ይቀበላል፡፡ ለጥያቄአቸውም ተገቢ መልስን ይሰጣል፡፡

የተወደድህ/ሽ አንባቢ ሆይ፣ ኢየሱስ ለጥያቄህ/ሽ ሲመልስ ግን የመቀበሉና የማስተናገዱ ውሳኔ ለአንቴ/ለአንቺ የተተወ ይሆናል፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለምትፈልግ ነፍስ ዛሬም እግዚአብሄርን በፍጹም ልብ የመውደድ ጥያቄ ይቀርብላታል፡፡ የእግዚአብሄርንም የጸጋ ሥጦታ በነጻ እንዲትቀበል ትጋበዛለች፡፡ አንቴም ድነትህን ለመግዛት አትቃጣ፣ ነጻ ነውና አምነህ ተቀበለው፡፡

ይህ ሀብታም የሆነ ወጣት፣ የዘላለም ሕይወትን በድርግቱ ወይም በሥራው ለመግዛት እንጂ ከኢየሱስ ለመቀበል የመጣ አይመስልም፡፡ ‹እኔ ከእኔ የሚለገውን ሁሉ ለማድረግ ሁለንተናዊ ብቃት አለኝና፣ አንቴ ብቻ ምን በማድርግ የዘላለም ሕይወትን መውረስ እንደሚችል ንግረኝ› እያለ ያለ ይመስላል፡፡ በነጻ ለመቀበል አልመጣም።

የእግዚአብሄር በረከት ጣዖት እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ኢየሱስም ይህንን ሲሰማ፣ በሰውዬው ልብ ውስጥ ትልቅ ዋጋ ተሰጥቶት ያለውን ነገር እንዲሰጥ ጠየቀው፤ ሀብቱን ማለት ነው (ቁ 21)፡፡ ዛሬ እንደሚባል “ገንዝብ ካለ፣በሰማይ መንገድ አለ።” በሚባምል እምነት ውስጥ ይኖራል።

ለሰውየው ሀብቱ የክብሩ ምንጭ፣ የጽድቁ ማሳያ፣ የድምጹ ማጉያ፣ የምቾቱ መሠረት እና የፈቃዱ ሁሉ ማስፈጸሚያ ነበረ፡፡

ምንም እንኳ እግዚአብሄርን የሚፈራና የሚወድ ቢሆንም፣ ሀብቱን ግን አብልጦ ይወደው ነበረ፡፡ በተለይ ደግሞ ለመኖሩ ዋስትና አድርጎ ሀብቱን የተማመነ ይመስላል፡፡ የዘላለም ሕይወትንም የሚፈልገው እንደተጨማሪ ነገር ነበር፡፡

ስለዚህ በእርሱ ዘንድ ዋና የነበረውን ሀብቱን እንዲተውና ምናልባትም ሁለተኛ የሆነውን የእግዚብሄርን መንግስት እንዲያስቀድም በኢየሱስ ሲጠየቅ ነገሩ ከበደው፡፡ ከሀብቱ ጋር ተያይዞ የሚያገኛቸውን ነገሮች ሁሉ መስዋዕት ማድረግ ስለከበደው አዝኖ ለመገብየት የመጣውን የዘላለም ሕይወት ሳይገዛ ባዶ እጁን ተመለሰ፡፡

የእግዚአብሔር መንግሥት ሊቀድም አይገባል።

እስቲ ትንሽ ቆም ብለን እናስብ። የዘላለም ሕይወትን እንደ ዋና ነገር ወይስ እንደ ተጨማሪ ነገር እየፈለግነው ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል “ነገር ግን አስቀውድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ 6፡33)

ኢየሱስ ሰውየው የወሰደውን ሁሳኔ አይቶ ከላይ ያነበብነውን ትምህርት አስተማረ፡፡ “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል?

ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ሲገረሙ፣ ኢየሱስ ተጨማሪና መልእክቱን ግልጽ የሚያደርግበት ማብራሪያ ተጠቅሞ ለማስረዳት እንዲህ አለ ፡ –

ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል”

ስለሰውየው ኢየሱስ “በገንዘብ የሚታመን” ሰው መሆኑን ገለጠ ማለት ነው፡፡

ሰውየውም ሆነ ያኔ የነበረው ማህበረሰብ እንደሚያምነው፣ ሀብታም መሆን የበረከት ምልክት ነው። ሰው ከእግዚአብሄር ይልቅ ከእግዚአብሄር የተሰጠውን በረከት ሲታመን ግን ሕይወት በክፉኛ ትጎዳለች፡፡

እስቲ እያንነዳነዳችን አለኝ የምንለውን፣ እግዚአብሄር ሰጥቶኛል የምንለውን፣ ምናልባትም በሕብረተሰባችን ዘንድ ተቀባይነት ሰጥቶኛል የምንለውን ማንኛውንም ነገር ለጌታ ስንል መተው፣ መስጠት፣ ማስቀመጥ ወይም መጣል ካልቻልን በትልቅ ወጥመድ ውስጥ ገብተናል ማለት ነው፡፡ ጌታ ይርዳን፡፡

ይህ ሁኔታ ያስፈራቸው ደቀ መዛሙርት “እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል?” (ቁ 26) ተባባሉ፡፡ ከጽድቃቸው የተነሳ እግዚአብሄር ባረካቸው ተብሎ የሚታመኑ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር መንግስት መግባት የማይችሉ ከሆነ፣ ታዲያ ማን ሊድን ይችላል ማለታቸው አግባብነት ያለው ጥያቄ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

ኢየሱስ ግን መልሶ “ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና” አላቸው (ቁ. 27) ፡፡

የዘላለም ሕይወትን በሥራ ወይም በገንዘብ ማግኘት ለሰው አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነውና፡፡ የዘላለም ሕይወት ደግሞ ለጻድቃን ብቻ የተዘጋጀ ነው፡፡ በእግዚአብሄር አምኖ እምነቱ እንደጽድቅ ያልተቆጠረለት ሰው (ማለትም ከነኋጢአቱ ለዘላለም የሚኖር ኋጢአተኛ ) አይወርሰውም ማለት ነው፡፡

እግዚአብሄር ግን ኋጢአተኞችን ያጸድቅ ዘንድ ልጁን ላከ፡፡ ስለዚህ ሰው በኢየሱስ በማመን የሚያገኘው ጽድቅ የእግዚአብሄር ሥራ ነው እንጂ የሰው ሥራ ሊሆን አይችልም፡፡ ለእግዚአብሄር ሁሉ ይቻላልና፡፡ “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።” (ኤፈ 2፡8)፡፡ የእኛ ድርሻ ሥጦታውን መቀበልና በሰጭው በእግዚአብሄር መታመን ነው፡፡

ፈቃደኛ ከሆኑ ይህንን ጸሎት አብረን እንጸልይ

ጌታ ኢየሱስ ሆይ እኔን ኋጢአተኛውን ማረኝ፡፡ ባለኝ ሀብት፣ እውቀት፣ ጽድቅና ሃይማኖተኝነት የዘላለም ሕይወትን መግዛት እንደማልችል ከቃልህ ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ በሚያስችለው ጸጋህ በሕይወቴ ላይ ከነገሱትና ጣዖት ከሆኑብኝ ነገሮች ሁሉ አድነኝ፡፡ አስተሳሰቤንና ልቤን ከተቆጣጠሩት ነገሮች ሁሉ አሁኑኑ ገላግለኝ፡፡

እግዚአብሄር ሆይ ስለ ልጅህ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ስትል እርዳኝ፡፡ ሊያድነኝ የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወቴ ጌታና አዳኝ አድርጌ እቀበለዋለሁ፡፡ ኢየሱስ ስለሰዎች ሁሉ ሃጢአት የከፈለውን መስዋዕትነት ለእኔም እንደሆነ አምኜ እቀበላለሁ፡፡ አሜን፡፡

ጌታ ኢየሱስ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *