Sermons

ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር

ሉቃ 2፡41-52 (ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር።”)

ሉቃ 2፡41-52 (ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር።”)

ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ዮሴፍና ማሪያም ከኢየሱስ ጋር የፋስካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ነበር፡፡ የፋስካን በዓል ለማክበር የሚደረገው ጉዞ ቤተሰቡ በየዓመቱ ያደርጉት የነበር ሥርዓት ነበረ፡፡ ይህ ዮሴፍመ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ደግሞ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ እንዲያከብር በእግዚአብሄር የታዘዘ በዓል ስለሆነ፣ ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ነበረ (ዘጸ.23፡14-15)፡፡

እስራኤሎች የፋስካን በዓል የሚከብሩበት ምክንያት፣ እግዚአብሄር በታላቅ ክንዱ እስራኤልን ከግብጽ ምድር ባሪነት እንዴት አድርጎ እንዳወጣቸው ለማስታወስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሕዝቡ ሕይወት ለሚያደርገው መልካም ነገር ሊታወስና ሊመሰግን ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዓሉ የእግዚአብሄርን ታላቅነት ለትውልድ የማስተዋወቂያ አንዱ መንገድ ነው፡፡

ወደ ማሪያምና ዮሴፍ ታሪክ ስንመለስ፣ ኢየሱስን በትልቅ ተዓምር የተቀበሉ፣ የእግዚአብሄር ጸጋ የበዛላቸው ቤተሰብ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ከማንኛውም ሰው የበለጠ ስለኢየሱስ አመጣጥ፣ ማንነትና የመምጣት ዓላማ ከእግዚአብሄር የተነገራቸውና የሚያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከመወለዱ ጀምሮ በኢየሱስ ምክንያት በህይወታቸው የተደረገው ነገር ሁሉና እየተጠባበቁት ያሉት ነገር ኢየሱስን ውድ አድርገው እንዲጠብቁትና እንዲንከባከቡት የሚያደርጋቸው ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ልጅ ደግሞ ለወላጁ ውድ እንደሆነ ግልጽ ነውና ኢየሱስ ለማሪያም እጅግ ውድ እንደሆነ መገመት ከባድ አይደለም፡፡

በዓሉን ፈጽመው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ግን አንድ አስደንጋጭ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ “ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር።” (ቁ 43)

ዙሪያቸውን አይተው ኢየሱስን ከጎናቸው ሲያጡ ወዲያው ማጠያየቅ ቢጀምሩም፣ በይሆናሎች (አሴምፕሽንስ) ወደፊት አንድ ቀን ሄዱ፡፡ እነዚያ አሴፕሽስ ወይም ግምቶች

  1. ከመንገደኞች ጋር ነው
  2. ከዘመዶች ጋር ነው
  3. ከሚያውቁአቸው ሰዎች ጋር ነው የሚሉ ነበር፡፡

በታሪኩ እንደምናነበው ግን አንዱም ግምታቸው ትክክለኛ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም እነዚያን ግምቶች ይዞ ጉዞ መቀጠላቸው ወደባሴ ጭንቀትና ክሳራ መራቸው፡፡ የሦስት ቀን መንከራተትና ፍለጋንም አመጣ፡፡ ወደፊት አድርገው የነበሩትን ጉዞ ሁሉ ወደ ኋላ መለሰው፡፡ ክሳራው ይህ ነበረ፡፡ ኢየሱስ ቀርቶ ነበርና፡፡

ከገመቱበት ቦታ ኢየሱስን ሲያጡ፣ ወደ መጀመሪያው ቦታ፣ ኢየሱስን ትተውት ወደ ሄዱበት መመለስ ግድ ሆነባቸው፡፡ በዚያም ነው ሊያገኙት የቻሉት፡፡ ኢየሱስ ቀርቶ ነበርና፡፡

የብዙዎቻችን ታሪክ

ይህ የማሪያምና የዮሴፍ ታሪክ፣ የብዙዎቻችንን ታሪክ ሊመስል ይችላል፡፡ ኢየሱስ ቀርቶ ነበር፡፡ ኢየሱስን ትተን በራሳችን ሁኔታ ውስጥ፣ በወሬ ሙቀት ውስጥ፣ በጨወታና በመዘናጋት ብዛት ውስጥ ገብተናል፡፡ ኢየሱስ ከጎናችን ሳይኖር ብዙዎቻችን ብዙ ተጓዝን፡፡ አንዳንድ ጊዜም ለብቻችን እየተጓዝን መሆናችንን ባወቅን ጊዜ እንኳ መመለስና ኢየሱስን መፈለግ አልቻልንም፡፡ ብዙዎቹ ግምቶቻችን ከመመለስ ይልቅ በወንጌላዊው፣ በቄሱ/በፓስተሩ፣ በነቢዩ፣ በሐዋሪያው፣ በዘማሪው፣ በሹማግለው፣ በወላጆቻችን ወይም በልጆቻችን ተማምነን ያለኢየሱስ የሆነውን ኑሮአችንን እንድንቀጥል አድርጎናል፡፡ ኢየሱስን የተቀበልነው በዋዛ አልነበረም፡፡ ለዋዛም አይደልም፡፡

ያለ ኢየሱስ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ የምናደርገው ጉዞአችን፤ ድካማችን፣ ትግላችን ሁሉ ከንቱ ነው፡፡

ስለዚህ ቆም ብለን እናስብ፡፡ የቱ ጋ ከእግዚአብሄር እንደተለየን መመርመርና ወደ እግዚአብሄር መመለስ ያስፈልገናል፡፡ መመለስን ትተን ሌሎች ግምቶችን እየደረደርን ያለኢየሱስ የሆነውን ጎዙአችን በቀጠልን መጠን ጭንቀታችንን፣ ድካማችንና ክሳራችንን እያበዛን እንሄዳለን፡፡

ማሪያምና ዮሴፍ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ኢየሱስ “በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት”፡፡ (ቁ46) ኢየሱስ ከአባቱ ቤት ወደትም አልሄደም፡፡

ኢየሱስ ለእኛ ያለእርሱ ሄዶ መንከራተት ተጠያቂ ልሆን አይችልም፡፡

ኢየሱስን ባዩት ጊዜ ማሪያም ኢየሱስ ጥፋተኝነት እንድሰማው ለማድረግ ጥያቄ ጠየቀችው፡፡ “ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን?” በሌላ አገላለጽ የማይገባህን አድርገሃል ማለቷ ነው፡፡ ቀጥላም “እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” አለች፡፡

በዚህ በማሪያም ንግግር ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ስህተቶች አሉበት፡፡

1ኛው ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር መኖሩን ሳያረጋግጡ ጎዞ የጀመሩት እነርሱ ናቸው፡፡ ያለ ኢየሱስ ረጅም ጉዞ በግምት (በይሆናል ብቻ) የተጓዙት እነርሱ ነበሩ፡፡ ትተውት ሄዶአልና ኢየሱስ ቀርቶ ነበር፡፡

2ኛው ማሪያም ሲትናገር ዮሴፍ የኢየሱስ አባት አለመሆኑን እያወቀች፣ “አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” አለች፡፡ ኢየሱስ ያንንም ለማስተካከል “እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው።”

ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ ‹እኔ የእግዚአብሄር ልጅ ስለሆንኩ እኔን ለማግኘት ወደ ሌላ ቦታ ሳይሆን ወደ እግዚአብሄር ቤት መምጣት እንዳለባችሁ ማወቅ ነበረባችሁ› ማለቱ ነው፡፡

በተጨማሪ ደግሞ አባቴ ዮሴፍ አይደለም፣ አባቴ እግዚአብሄር ነው፡ ማለቱ ነው፡፡ እርሱ ራሱ “ራሱን ሊክድ አይችልምና።” (2ጢሞ 2፡13)

የሚገርመው ይህንን ኢየሱስ የተናገረውን እውነት በዚያ የነበሩት ሰዎች (መምህራኖቹን ጨምሮ) አላስተዋሉትም፡፡ (ቁ 50) ኢየሱስ እግዚአብሄር አባቴ ነው ብሎ የተናገረውን ብዙዎች በተለምዶ የሚባል ሃይማኖታዊ ንግግር ወይም ደግሞ የሕፃን ንግግር አድርገውታል፡፡ ስለዚህም ምን ለማለት እንደፈለገ ያስተዋለና ተመጣጣኝ ምላሽ የሠጠ በዚያ አልነበረም፡፡

ዛሬም የኢየሱስን ቃል በሃይማኖት ቤቶች ውስጥ ከለመዱ ንግግሮች ወይም “ኣላዋቂ” ከምንላቸው አገልጋዮች ወይም መስካሪዎች ንግግር ለይተን ካላየን፣ ተመጣጣኝ ምላሽ ለእርሱ መስጠት ያስቸግረናል፡፡ በደንብ ልብ ብለን ከሰማን ግን ቃሉ እውነትና ሕይወት ነው፣ ከስህተት መንገዶቻችንም ወደ ቀናው መንገድ ይመልሰናል፡፡

ማጠቃለያ፡፡

ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ ይህንን መቀበል ለአእምሮ የሚከብድ ቢሆንም እውነት ነውና ሁሉም ሊቀበሉት ይገባል፡፡

ኢየሱስን ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ሌላ ቦታ መንከራተት አግባብብነት የለውም፡፡ እርሱን የሚፈልግ ወደ እግዚአብሄር ቤት መምጣት አለበት፡፡ ኢየሱስ በዚህ ይሁን በዚያም ይሁን ብለን ያስቀመጥናቸውን ግምቶቻችንን ትተን እርሱን ማግኘት ወደምንችልበት እንደቃሉ መሄድ አለብን፡፡ እንደቃሉም ለመሄድ ቆም ብለን እናስብ፣ እንስማውም፤ እርሱን ወደ ተውንበት ቦታ ብንመለስ እናገኘዋለንና፡፡

ያለ ኢየሱስ በመኖራችንና በመሄዳችን ላጋጠሙን ክሳራዎች ሁሉ ጌታን ጥፋተኛ አድርጎ በእርሱ ላይ መናገር ትክክል አይደልም፡፡ ጌታ በጸጋው ይርዳን፡፡

ሉቃስ 2፡

41 ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር። 42 የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ 43 ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። 44 ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ 45 ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 46 ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ 47 የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ።

48 ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። 49 እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። 50 እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

 

በተክሉ

 

ኢየሱስ ቀርቶ ነበር፡፡ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። the child Jesus tarried behind in Jerusalem; and Joseph and his mother knew not of it. ተክሉ፣ መካነ የሱስ በስኮትላነድ፣

 

በተክሉ

 

ኢየሱስ ቀርቶ ነበር፡፡ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። the child Jesus tarried behind in Jerusalem; and Joseph and his mother knew not of it. ተክሉ፣ መካነ የሱስ በስኮትላነድ፣

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *