Sermons

ንስሃ በፍሬ

ሉቃ 13፡1-9 ንስሓ በፍሬ ECMYIS ,Evalgelical Church Mekane Yesus, Ethiopian Christian Church in Glasgow, Eritrean Christian Church in Scotland, Evangelical and Lutheran church,cross

ሉቃ 13፡1-9 ንስሃ በፍሬ

1 በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። 2 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? 3 እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ። 4 ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ 5 ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። 6 ይህንም ምሳሌ አለ፦ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። 7 የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፦ እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። 8 እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። 9 ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።

ዛሬም ሆነ ጥንት ሰዎች አስከፊ አደጋ ሲከሰት የአደጋው ሰለባዎችን ኃጢአት መገመት የተለመደ ነው፡፡ እርሱ እንዲህ ስለሆነ፣ እርሷ እንዲህ ስላደረገችኝ፣ እንቲናን እንዲህ ስላደረገው ይህ ሆነበት ይባላል፡፡ ይህ በሰው ታሪክ ውስጥ የቆዬ ልምምድ ሆኖአል፡፡ አደጋ ስከሰት የአደጋው መንስኤ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ መጠየቅና መገመት በራሱ ችግር የለውም፡፡ ችግሩ ግን በመገመቱ ህዴት አብላጫዎቹ ድምዳሜዎቻችን በትክክለኛ መሠረት ላይ የተመሠረቱ አለመሆናቸውና በተለይ ደግሞ ሌላውን አጢፊ ራሳችንን ደግሞ ጻድቅ አድርገን የሚናይባቸው መነጸር ማጥለቃችን ነው፡፡

በዛሬው የወንጌል ክፍል የሚናየው ትምህርት ከዚህ ሃሳብ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያለው ነገር ነው፡፡ኢየሱስ ጲላጦስ በሰዎች ላይ ስለፈጸመው ግፍና በአስከፊ ሁኔታው ስለተገደሉ ሰዎች አወሩለት፡፡ በወረኞቹ አዘጋገብና አስተሳሰብ ኢየሱስ ደስተኛ አልነበረም፡፡ ‹ምን ሓጢአት ቢሠሩ ነው እንዲህ የደረሰባቸው?› የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ኢየሱስ ግን ወረኞቹ የአደጋው ሰለባዎች የበደል ብዛት የችግሩ መንስኤ አድርገው የሚያስቡበትን አስተሳሰባቸውን ውድቅ አደረገባቸው፡፡

ይህም ማለት፣ ለምሳሌ፣ በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ማርች 10፣ 2019 በብሾፍቱ በደረሰው የአውሮፕላን መከስከስ ምክንያት ስናዝንና ለአጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ወዳጆችና ቤተሰቦች መጽናናት ስንጸልይ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ያም ከሆነ በኃላ በደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል በደረሰው አደገኛ ጎርፍ (ሳይክሎን እዳእ) ብዙ ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን አጥተው ስንመለከት አጅግ በጣም አሳዝነናል፡፡ አሁንም ቢሆን ከአደጋው ለተረፉትና ለተጎጂዎች ወዳጅ ዘመድ፣ ጓደኞች መጽናናትን መለመን አለብን፡፡ ትልቅ ጉዳት ነውና፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በዚህ ቦታና ጊዜ ዘርዝሬ የማልጨሪሳቸው የክራይስት ቸርች (ንውዚላንድ) የሽብር ተግባርን ጨምሮ ብዙ አስከፊና አሳዛኝ ወሬዎች በዚህ ወር ብቻ ተደምጠዋል፡፡

እንዲህ አይነቱን ነገር ስናይና ስንሰማ እኛ ምን አይነት ድምዳሜ ላይ እንደርስ ይሆን? ለምንስ እነዚህ ሰዎች? እነርሱ በዘመናችን ካሉት ሰዎች ሁሉ ኃጢአታቸው በልጦ የበዛ ነው ብለን እናስብ ይሆን?

ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ነው ያለው (ያውም አጽንኦቱን ለማሳየት በመድገም) “ … አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።” (ቁ 4-5)

ኢየሱስ “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ” ሲል ምን ማለቱ ነው?

1.      ሁላችሁም ኃጢአተኞች ናችሁ፡፡

(ሮሜ 3፡23፣ 6፡23) እነርሱም ሆነ እናንተ ዘጋቢዎቹ ኃጢአት አልባ አይደላችሁም፡፡ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከእናንተ የተሻሉ ሓጢአተኞች ስለሆኑ አደጋው አልደረሰባቸውም፡፡ እናንተ ደግሞ የተረፋችሁት፣ አደጋ ያልደረሰባችሁ የተሻላችሁ ጻድቃን ስለሆናችሁ በሕይወት አልኖራችሁም፡፡ ነገር ግን

2.      በአስቸኳይ “ንስሃ ግቡ”፡፡

የሚጠቅማችሁ የሌሎችን ሓጢአት መተንተን አይደለም፡፡ ግን ንስሃ መግባት ያስፈልጋችሁኋል፡፡

ጌታ ኢየሱስ በዚህ ክፍል ውስጥ ንስሓ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት ይንን ምሳሌ ተጠቅሞአል፡፡

“ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም።   የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፦ እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” (ቁ 6-9)፡፡

የበለስቱን ፍሬ ለማግኘት ሰውየው ራሱ መጣ (መልእክተኞችን አይደልም የላከው)፣ ብያንስ ለፍሬ ፍለጋ ብቻ ሦስት ዓመት ተመላለሰ፡ ይህ የአመት ብዛት እንጂ ፍሬ ለማግኘት የመጣበት ጊዜ ቁጥር አይደለም፡፡

ስለዚህ ይህች በለስ ፍሬ ካፈራች፣ ሰውየው የሚጠብቅባትን ሆና ተገኝታለች ማለት ነው፡፡ ይህ ነው ንስሓ መግባት ማለት ነው፡- ያለ ፍሬ መቆምን ትታ ፍሬ አዝላ መቆም፡፡ ያንን ማድረግ እንዲትችል ደግሞ ተጨማሪ የምህረት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ አገልግሎቶችንም እንዲታገኝ በሠራተኛው ታቅዶላታል፡፡

በሕይወት ኖረን፣ ተጨማሪ የእግዚአብሄር ቃል፣ ተጨማሪ የእግዚአብሄር መልካምነት፣ የእግዚአብሄር ጥበቃ፣ መልካም ፍሬ ለማፍራት ይረዱን ዘንድ የተቀበልናቸው የጸጋ ሥጦታዎችና ተጨማሪ አገልግሎቶች ሁሉ በአሁንና በሚመጣው ዓመት መካከል ፍሬ አፍርተን እንድንገኝ ነው፡፡

የእርሻው ባለበት በሚቀጥለው አመት ሲመጣ ፍሬ ካልተገኘባት በለስቱ መቆረጧ ነው፡፡

ለእኛ “የሚቀጥለው ዓመት” የተባለው መቼ ይሆን? ከተሠጠን የጸጋና የእንክብካቤ ዘመን ምን ያክሉን አሳልፈን ይሆን? ፍሬስ ይታይብን ይሆንን?

ምን አይነት ፍሬስ ይሁን እግዚአብሄር ከአንቴ / ከአንቺ/ ከእኔ /ከእኛ የሚጠብቀው? ከበለስቱ የወይን ወይም የማንጎ ፍሬ አልተጠበቀባትም፣ የበለስ ፍሬ እንጂ፡፡ በለስ ስለሆነች፡፡ እግዚአብሄር ያልሆነውንና ያልሠጠንን ከእኛ አይጠብቅም፡፡ እንደ ሌላ ሰው ሆነን ስላልተገኘንም አይፈርድብንም፡፡ ነገር ግን በሆነውና በተሠጠን ልክ ደግሞ ተገቢ ፍሬ አፍርተን እንድንገኝ ይፈልጋል፡፡

በክርስቶስ በኩል ጽድቅን ከተቀበሉት አማኞችም ያንን የጽድቅ ፍሬ እያፈሩ እንድኖሩ ይፈልግባቸዋል፡፡ እግዚአብሄር በልጁ በኢየሱስ ከማያምኑት በእርሱ የማመንን ይፈልጋል፡፡ በልጁ አምነው ካሉት ደግሞ እንደ እግዚአብሄር ልጆች የመኖርን ፍሬ ይፈልጋል፡፡

ንስሓ በፍሬ ይታወቃል፡፡ ኢየሱስ ደጋግሞ “ንስሃ ባትገቡ…” ብሎ አስጠንቅቆአል፡፡ ሐዋያው ጳውሎስም “እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።”(የሓ.ሥ 17፡30-31)፡፡ ሰው ሁሉ ንስሃ መግባትና ወደ እግዚአብሄር መመለስ አለበት፡፡

የተሠጣቸውን የንስሃ ጊዜ ለሚንቁ (ለማይጠቀሙበት) ሰዎች ሓዋሪያው እንዲህ ብሎ ነበረ “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።”( ሮሜ 2፡4-5)፡፡

በዚህም ቶሎ ንስሓ ግባ እንጂ ጊዜህን በከንቱ አታጥፋ እያለ ነው፡፡ ኢየሱስም መልካም ፍሬ በማያደርጉት ላይ የእግዚአብሄር ቁጣ ሊገለጥ አለና “ንስሃ ባትገቡ እንድሁ ትጠፋላችሁ” ብሎአል፡፡

ይህ ማስጠንቀቂያም ግሳጸም ነው፡፡ ጌታ “እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ።” ይላልና (ራዕ 3፡19)፡፡

 

3.      የእግዚአብሄር ምህረት ያስፈልጋችሁኃል

የእግዚአብሄር ምህረት ያልተቀበለ ኃጢአተኛ ሁሉ ጥፋት ይጠብቀዋል፡፡ ጥፋት አይደርስብኝም፣ ከሌሎቹ እሻላለሁ ብሎ የሚያስብና ራሱን የሚያመጻድቅ ሁሉ ተሳስቶአል፡፡ የእግዚአብሄር ምህረት ማግኛ መንገዱ ደግሞ በንስሓ መመለስ ነው፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ በግልጽ ንስሃ ባለመግባት የሚመጣ የእግዚአብሄር ቁጣ እንዳለ ያስተምረናል (ሮሜ 1፡8፣ ቆላ 3፡6፣)፡፡

እንግዲህ ከዚህ ከፍል ተምረን በእግዚብሄር ፊት ራሳችንን መመልከት መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ“ (ኤፌ 5፥9)፡፡

 ጌታ ይባርካችሁ

 

በተክሉ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *