Sermons

በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል

ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ። እኔም፦ የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አናደምጥም አሉ። አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ። ምድር ሆይ፥ ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ።”

ሉቃ 6፡ 6-11 (በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል)

“6 በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ 7 ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 8 እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው፦ ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። 9 ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። 10 ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። 11 እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ። “

በዚህ ክፍል ውስጥ ያሉትን ተዋናዮች በአጭሩ ለአራት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው አንድ እጁ የሰለለች ሰው፣ በምኩራብ ገብቶ የሚያስተምር መመህር (ኢየሱስ) እና መክሰሻ የሚፈልጉ ጻፎች እና ፈሪሳዊያን እንዲሁም ተመልካቾች/ታዛቢዎች የሆኑት በቦታው የተገኙ ሰዎች (ሕዝብ) ናቸው፡፡

ለአምልኮ ወደ ምኩራብ የሚሄደው ሕዝብ እግዚአብሄርን አምልኮ መግባት ይፈልጋል፡፡ በመካከላቸውን እየተደረገ ያለውን አይቶ ይታዘባልና የሚያየውና የሚሰማው ነገር የተምታታበት ሕዝብ ይመስሉኛል፡፡ በሥራውና በትህርቱ በሚደነቀው ኢየሱስ ደስ ይለዋል፡፡ ደግሞም መሪዎቹ የነበሩ ፈሪሳዊያንና ጻፎች ስለኢየሱስ የሚነግሯቸው ደግሞ ከሚያዩት ተቃራኒ ነበረ፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ የአምልኮውን ቦታና ሥርዓት ስለተቆጣጠሩትና በመህበረሰቡም ዘንድ ባለው ግንኙት “ሥልጣን” እና ተሰምነት ስላላቸው፣ ከእነርሱ ጋር መጣላት ደግሞ ሕዝቡ አይፈልጉም፡፡

ቢሆንም ግን ኢየሱስን ተከትለው ፈውስ ፍለጋ ወደ ምኩራብ የሚመጡ እየበዙ ይገኛሉ፡፡ ኢየሱስም በምኩራብ እየሄደ ማስተማርን ልማዱ አድርጎታል፡፡ ይህ በሕዝብ ዘንድ ትኩረት ያገኜው የኢየሱስ ሥራና ትምህርት ኢየሱስ ወደሚገኝበት ብዙ ሰዎችን እየሰበሰበ ነው፡፡ የኢየሱስ ትምህርም ሆነ ሥራ ሰዎች ከለመዱት ዓይነት ሥርዓት ወጥተው እዲያስቡ፣ እንዲጠይቁና የእግዚብሄርን መንግስት እንዲፈልጉ እያደረገም ጭምር ይገኛል፡፡

በዚህው ልክ፣ የእግዚአብሄርን ቤት የራሳቸው ክብር ማጉያ እና የፈቃዳቸው ማስፈፀሚያ ያደረጉ መሪዎች ደግሞ ኢየሱስን የሚከሱበትን ምክንያትና ምቹ ጊዜ እየፈለጉ ነው፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስም የነበረውን ሁኔታ ሲመዘግብ “መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር” ይላል፡፡

ፈውሱ ቢያንስ በሶስቱ ቡድን ይፈለጋል ማለት ነው፡፡ እጁ የሰለለችበት ሰው ጤነኛ ሰውነት ስለሚፈልግ ለመፈወስ ይጓጓል፡፡ ለታመሙትና ለታሰሩት ግድ ብሎት የመጣው ኢየሱስ ማዳን አላማው ስለሆነ ለመፈወስ ዝግጁ ነው፡፡ ኢየሱስን የሚጠሉት ሰዎች ደግሞ ለክስ ፋይላቸው ግብዓት ይሆንላቸዋልና ኢየሱስ በሰንበት ፈውስ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ አገልግሎቱን ከሰንበት ሥርዓት ጋር በማጋጨት ለክፋታቸው የሚጠቅም መረጃ ይፈልጉነት ነበርና፡፡

ኢየሱስ ግን ሓሳባቸውን አውቆባቸዋል፡፡ ሰው በክፋትም ሆነ በቅንነት ለማድረግ የሚያቅደውን ዕቅድ፣ የሚያስበውን ሓሳብ፣ የሚወጥነውን ውጥን ጌታ አስቀድሞ ያውቀዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሰው ክፋት የእግዚአብሄርን መልካም ዓለማና አገልግሎት ሊያስቀረው አይችልም፡፡ ለእነርሱ ጌታ ራሱ መልስ ይሠጣቸዋል፣ ፈውስን ተጠባቢቃ የመጣችው ነፍስ ግን የተጠማችውን ሳታገኝ አትመለስም፡፡ ጌታ ይራራልና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎቹን ሀሳብ ባወቀ ጊዜ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ ይህ ጥያቄ ለሚጠሉቱ ብቻ ሳይሆን ለሚታዘቡትም ሰዎች የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ ይጠቅማል፡፡

ጥያቄውም፣ “የቱ ተፈቅዶአል” የሚል ነበረ፡፡ “ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው።” (ቁ9). በዚህ ክፍል ውስጥ ያለውን ሐሳብ ብንተነትን በጥቂቱ ቀጥሎ ያሉትን ነገሮች ከኢየሱስ መገንዘብ እንችላለን፡፡

  • በሰንበት መሥራት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሚሠራው ሥራ በጎነትና ነፍስን ማዳን ላይ ያተኮረ መሆን አለበት
  • የክስ አጀንዳችሁን ትታችሁ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታችሁን ተጠቀሙ፡፡ በሰንበት ምን ቢሰራ መልካም እንደሆነም አስተውሉ፡፡ ከጭፍን ሓይማኖተኝነትና የክስ መረጃ ጥማታችሁን ከማርካት ወጥታችሁ እግዚአብሄር የሚደሰትበት ነገር ምንድን ነው? ብላቸው አስቡ፡፡
  • እናንተም እኔም እየሰራን ነው፡፡ ሥራችን ግን በአይነቱ ይለያያል፡፡ እኔ በጎ ሥራና ነፍስ ማዳንን እፈልጋለሁ፡፡ እናንቴ ግን ክፉ ሥራና እኔን የመግደል ዓላማ ይዛችሁ ትከታተሉኛላችሁ፡፡ ግን የተፈቀደው የቱ ነው?
  • ለምን የተፈቀደውን ትታችሁ ወይም የእግዚአብሄርን ፈቃድ/ቃል ወደ ጎን ጥላችሁ በጥላቻና በክፋት ትነዳላችሁ? ማድረግ ያሰባችሁትን ሳታደርጉ በፊት ሂዱና መመሪያችሁን (የሥራ ድርሻችሁን) መርምሩ፡፡ እግዚአብሄር ከእናንቴ ምን ይፈልጋል? ምን እንዲታደርጉ ልኮኦችሁኃል? የተልኮአችሁን መመሪያ ፈትሹና በዚያ መሠረት ሊታደርጉ ያላችሁትን አድርጉ፡፡
  • እኔን ለመወንጀል በአምልኮ ቦታ መገኘት ክፋት ነው፣ ነፍስንም (የራስን ጨምሮ) መግደል ነው፡፡ እግዚአብሄር በእውነትና በመንፈስ የሆነ አምልኮ ይፈልጋል፡፡
  • የእኔን የሥራ ፈቃድ ስትጠይቁ፣ የራሳችሁንም የሥራ ፈቃድ መያዛችሁን አትዘንጉ፡፡

ኢየሱስ እነዚህን ሁሉ ሓሳቦች በውስጡ የያዜ ምክርም ጥያቄም ግሳጸም ያለበትን መልእክት ሲናገር ምላሽ የሰጠው ሰው አልነበረም፡፡ “ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች።”

ተከራካሪ ስለበዛ በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ የእግዚአብሄር ሥራ አይቆምም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ በሌላ ቦታ ሲናገር “አባቴ ሁልጊዜ ይሰራል እኔም እሰራለው” ቢሏል፡፡

ይህ ሁሉ የኢየሱስ ምክርና ጥያቄ ደግሞም የፈውስ ሥራው በዚያ የነበሩትን ሁሉ ማስገረም፣ ማስደንገጥ እንዲሁም ሐሳባቸውን ማስቀየር ነበረበት ብዬ አስባለው፡፡ ቀጥሎ የምናነበው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ “እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ።”

ጻፎችና ፈሪሳዊያን ባደረጉትና ባሰቡት ሓሳብ ላይ ከኢየሱስ አገልግሎት በሃላ ማዘንና ንስሓ መግባት ነበረባቸው፡፡ እነሱን ግን ይባስ ብሎ “ቍጣሞላባቸው”፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ክፋትን አቅዶ የወጣ ሳያደርገው ስለማይመለስ ወዮለት ቢሎ ያስጠነቅቃል፡፡ “በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ኃይል በእጃቸው ነውና ሲነጋ ይፈጽሙታል።” (ሚክ 2፡1)

በሌላ በኩል ደግሞ አለመመለስና ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር መጣላት የጳፎችና የፈርሳዊያን ችግር ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚያም በፊት የነበረ አሁን ባለንበት ዘመንም ጎልቶ የሚታይ የሰው ችግር ነው፡፡

በነቢዩ ኤርሚያስ (6፡16-19) ዘመን እንዲ ነበር የሆነው፡፡ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ። እኔም፦ የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አናደምጥም አሉ። አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ። ምድር ሆይ፥ ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ።”

በዚህም ዘምን በሥህተት ሳይሆን ታስቦበት፣ ታቅዶበትና እየተነገራቸው የእግዚአብሄርን ቃል እምቢ በማለት የሚደረግ ክፋት እንደነበረ ወጤቱ ደግሞ በእግዚአብሄር ላይ ሳይሆን በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር እንዳመጣ እናነባለን፡፡

እስቲ የጌታን ቃል ወደየግል ሕይወታችን እናምጣና ራሳችንን እንይበት፡፡ ምናልባት ብዙ መልካም አጋጣሚና የንስሓ ጊዜ በከንቱ አጥፍተን ይሆናል፡፡ ምናልባት ለአንዳንዶች ደግሞ ይህ የንስሓና የመመለስ ጥሪ የመጨረሻቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እየሄድንበት ባለነው በመንገድ ላይ እንቁምና እንመልከት፣ የቀደመችውንም መንገድ እንጠይቅ፡፡ በክፉ ሃሳቦቻችን ንስሓ እንግባ፣ በጎ ማድረግና ነፍስን ማዳንን እናስብ እንለማመደውም፡፡

ጌታ ኢየሱስ በጸጋው ይርዳን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ፡፡

 

One thought on “በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *