Sermons

በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና

Glasgow evangelical christians, Mekane Yesus in Scotland, UK, United Kingdom, Mekane Yesus, Erithrans and Ethiopians Christian church, Lutheran በማናቸውም ቦታና ሁኔታ ያለው ሰው የተለያዩ የሕይወት ውጣውረዶች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ የዳዊት ሕይወት በማያቋርጥ ሰልፍና ለአደጋ አጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም በየቀኑ በእግዚአብሄር መታመንን፣ መጸለይን፣ ጥንቃቄንና ትጋትን አስተምሮታል፡፡ እግዚአብሄር በመከራ ቀን ልጆቹን የሚሰውርበት “ድንኳን” አለው፣ በድንኳኑም ውስጥ ልዩ “መሸሸጊያ” ክፍል አለው፡፡ Church in Glasgow በድንኳኑ

Godoo isaa keessa na dhokfata

በማናቸውም ቦታና ሁኔታ ያለው ሰው የተለያዩ የሕይወት ውጣውረዶች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ የዳዊት ሕይወት በማያቋርጥ ሰልፍና ለአደጋ አጋላጭ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ሁኔታው በየቀኑ በእግዚአብሄር መታመንን፣ መጸለይን፣ ጥንቃቄንና ትጋትን አስተምሮታል፡፡ እግዚአብሄር በመከራ ቀን ልጆቹን የሚሰውርበት “ድንኳን” አለው፣ በድንኳኑም ውስጥ ልዩ “መሸሸጊያ” ሥፍራ አለው፡፡

 

በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና (መዝ. 27፡5)

በማናቸውም ቦታና ሁኔታ ያለው ሰው የተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች የሰው ተግዳሮት ለጎረበቶቹ የተገለጡና ሰዎች መቸገሩን በቀላሉ አይተውና ሰምተው የሚያዝኑለት ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ በጎረበቶቻቸው ዘንድ “ደልቶታል”፣ ”ተመችቶአታል”፣ ወዘተ. እየተባለ፣ ሰው በግሉ ግን በልቅሶና በጩኼት ተሞልተው እንዲኖሩ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዳዊት ወደ ንግሥና ከመምጣቱ በፊት ምናልባት ረጅሙን ጊዜውን በጎች ማሰማራት ላይ፣ ከአንበሶችና ከድቦች ጋር በየቀኑ መታገል ላይ አሳልፎአል፤ የዘወትር ሥራውም ይህ ሆኖለት ነበረ፡፡ የዳዊት ሕይወት በማያቋርጥ ሰልፍና ለአደጋ አጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ሁኔታዎቹ በየቀኑ በእግዚአብሄር መታመንን፣ መጸለይን፣ ጥንቃቄንና ትጋትን አስተምሮታል፡፡

በተጨማሪም ደግሞ ይህ የትግል ሕይወት (ለጊዜው ዳዊት ባያውቀውም ወይም ባይረዳውም ወይም ባያስተውለውም ወይም ደግሞ መገመት ባይችለውም) ለነጌ የሚያዘጋጀው ነገር ነበረ፡፡

ነጌ የተለየ ቀን ነው፡፡ ነጌ ትላልቅ ጦሪነቶች በፊቱ አሉ (ጎሊያድን መግጠምን ጨምሮ)፡፡ ነገ ከዛሬው ሕይወት ጋር ሊመዛዘን የማይችል ትልቅ ክብርና ንግሥና አለ፡፡ አሁን ተደብቆ ካለበት ጫካ ወጥቶ በሀገሩ ሰዎችና በዙሪያው ባሉት ሀገሮችና ህዝቦቻቸው ዘንድ ሊገለጥ አለ፡፡ ይህ መገለጥ ደግሞ ብዙ ተጨማሪ ጦሪነቶችንና ተግዳሮቶችን ይዞ ሊመጣ አለ፡፡ ዳዊት በወቅቱ ምን ሊሆን እንዳለ አያውቅም ነበረ፡፡ እግዚአብሄር ግን ዳዊትን ለዚህ ሁሉ ሲያዘጋጀው ነበረ፡፡ ዳዊት ግን በወቅቱ በመኖር ያለበትን ሕይወት በእግዚአብሄር በመታምን ይኖር ነበረ፡፡

በመዝ 27፡5 ላይ “በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።” ይላል፡፡

ዳዊት ካሳለፈው ሕይወት ከተማራቸው ነገሮች አንዱ፣ እግዚብሄር በመከራ ቀን ልጆቹን የሚሰውርበት “ድንኳን” እንዳለው፣ በድንኳኑም ውስጥ ልዩ “መሸሸጊያ” ሥፍራ እንዳለው ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ድንኳን በሚድረበዳም፣ በቤተ መንግስትም አለ፡፡ ስለዚህ ለዳዊት ሁልጊዜ በእግዚአብሄር መታመን የድሎቹ ትልቁ ምስጥር ነበረ፡፡ ዳዊት መከራ አይመጣብኝም ብሎ አያስብም፣ ከእኔ ጋር የሚዋጋ አይኖርም ብሎም በከንቱ አይታበይም፣ ነገር ግን መከራው ይዞት እንደማይሄድ እንጂ፡፡ እግዚአብሄር እንደሚረዳው ያምናል፡፡

የመዝ 27ን ጥቂት ክፍሎች ብንመለከት፣ ዳዊትን በየጊዜው ከሚያጋጥሙት ነገሮች ጥቂቶቹን ብንመለከት

  1. ማስፈራራት

    – “የሚያስፈራኝ ማን ነው?” ( ቁ. 1ሀ ና 3) ሲል አልፈራቸውም ማለት እንጂ ሊያስፈራሩኝ የሚሞክሩ የሉም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ በዝተውና ተፈራርቀው ሲመጡ የማስፈራራት አቅማቸው ትልቅ ነው፡፡ ግን መታመኛው በአምላኩ የሆነ ሁሉ ድል አለው፡፡እኛም ምናልባት በየእለታዊ ሕይወታችን ውስጥ በጤና፣ በማሕበራዊ ሕይወት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሌሎች መንገድ ብቅ ብቅ እያሉ የሚያስፈራሩን ነገሮች ይኖሩን ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር መታመንን በሕይወታችን ውስጥ ካጎለበትን፣ እንደ ዳዊት “የሚያስፈራኝ ማን ነው?” ማለት እንችላለን፡፡

  2. ማስደንገጥ (ቁ1ለ)- ማስደንገጥ ሌላው በየጊዜው ዳዊትን የሚያጋጥም ነገር ነበረ፡፡ የማይጠብቃቸውን ነገሮች እያመጡበት በርጊጎ ስፍራውን ለቆ እንዲሄድ ለማድረግ፣ ደንግጦ የያዘውን እንዲለቅ ለማድረግ፣ ወዘተ. ይመጣሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ጊዜ “አምላክህ ወዴት አለ?” በማለት ምንም ቀሪ ረዳት እንደለሌውና ሁሉም እንደተወው በማስመሰል ለማስደንገጥ የሚመጡ እንዳሉ ከመዝሙሮቹ መረዳት እንችላለን፡፡
  3. በክፋት ማስጨነቅ – ክፋትን ማየት አንድ በጣም የሚያም ነገር ነው፡፡ ሰው ሁሉ የራሱ ድካም ቢኖረውም ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትን ሲያይ፣ ክፋት ሲያደርጉበትም መመልከቱ ያሳምመዋል፡፡ ክፋት ሲበዛ፣ ሲሰፋ፣ ለምልሞና አፍርቶ ሲታይ የጻድቁን ሕይወት ያስጨንቃል፡፡ ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ጻድቁ ጽድቁን ትቶ ክፉውን በክፉ ለመመለስ እንዲፈተንም ጭምር ያደርጉታል፡፡ ዳዊት ከእግዚብሄር የተነሳ በክፋት ለማስጨነቅ የወጡበት ሁሉ ተሰናክለው እንደወደቁ ይናገራል (ቁ2)፡፡ (በሃላ በጎሊያድ፣ በሳኦል፣ በአብሰሎምም ላይ የሆኑት ነገሮች አመልካቾች ናቸው)
  4. ከገደብ ያለፈ ጥቃት – “ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ” ይላል፡፡ ዳዊት በዚህ ቦታ የጠላቶቹን ወደ እርሱ መቅረብ ብቻ ሳይሆን ዓላማቸው “ሥጋውን መብላት” እንደ ነበር ይገነዘባል፡፡ ልክ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደ ነበረ፣ አንበሶቹም ሊበሉት ሲቀርቡ እግዚአብሄር መልአኩን ልኮ እንደከለከላቸው፡፡ ጠላቶች እጅግ ሊቀርቡ ይችላሉ ግን እግዚአብሄር ከዚህም ያድናል፡፡ ጠላቶችህ ስለቀረቡ፣ ስለበዙ፣ በክፋትም ስለተነሱ ብቻ አይበሉህም፡፡ እግዚብሄር ተሰናክለው እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ሌላው ከዚህ የዳዊት መዝሙር የምንማረው፣ ነገሮች ሁሉ መልክ እየቀያየሩ እኛን ለማጥቃት ሲፈራረቁብን፣ እኛ ደግሞ የትኩረት አቅጣጫችንን ወደምንታመንበትና ሊያድነን ወደሚችለው እግዚብሄርና ወደ ፈቃዱ መመለስ ነው፡፡ በመከራውም ጊዜ ብሆን፣ ዳዊት መሻቴ ብሎ የሚናገራቸው ነገሮች “በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ” ነው፡፡

በእግዚአብሄር መገኘት ውስጥ በቀጣይነት መኖር ትልቅ የድል ምንጭ ነው፡፡ በሚያስፈራራው፣ በሚያስደነግጠው፣ በክፋት በተነሳውም ሆነ ያለመጠን ቀርቦ በሚያጠቃን ጠላት መካከልም ቢሆን ከእግዚአብሄር አለመለየት፡፡ እግዚአብሄርን በጊዜና በሁኔታ የማይወሰን ወዳጃችንና መታመኛችን ማድረግ፡፡ እርሱን ሁልጊዜ ማየት፣ እርሱን መስማት፣ እርሱን መማከርና እርሱን ከሁሉም ማስበለጥ፡፡ ለዚህ ነው ዳዊት እንዲህ ያለው

“እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።” (ቁ 4)

ለምንድን ነው በተከበበ ሕይወት ውስጥ ሆነን በራሳችን መንገድ የሚደርሱብን መከራና ተጋላጭነት የማንወጣው?

ዳዊት የራሱን ሲናገር፣ “በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።” የእንግሊዘኛውን (ክጄቭ) ወይም የኦሮሚኛውን ትርጉም ብንመለት፣ “በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ይሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ይሸሽገኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ ያደርገኛልና።” የሚል ሓሳብ አለው፡፡

ይህ ማለት ደግሞ በእግዚአብሄር በምንታመንበት ጊዜ ስለትናንትና ታሪክ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄር የማያቋርጥ፣ ሁልጊዜም አስተማማኝ የሆነ የሚታመኑበትን የማዳን አቅምና መንገድ እንዳለው ነው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ሁልጊዜ እንታመን፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *