Sermons

መፍትሄ አለው

It is important to listen to Jesus when it comes to godly life. Whatever comes on our way, Jesus has the answer. ECMYIS, EVANGELICAL CHUCH MEKANE Yesus in Scotland. An evangelical Christian church in Glasgow city, Scotland, United Kingdom. Ethiopian and Ertrian Christian church, Sunday service in Amharic. የዮሐንስ ወንጌል 2 1 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ 2 ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። 3 የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። 4 ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። 5 እናቱም ለአገልጋዮቹ፦ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። 6 አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። 7 ኢየሱስም፦ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። 8 አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። 9 አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፦ 10 ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። 11 ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።

ኢየሱስ መፍትሄ አለው

የመልእክት ከፍል ዮሃ 2፡1-11 “Do whatever he tells you.” John 2:5 NIV

ቁ1. “በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች”

የገሊላ ቃና ከናዝሬት (ማለትም ዮሴፍና ማሪያም ከሚኖሩበት መንደር- ሉቃ 2፡39) በስተ ሰሜን ስምንት ወይም ዘጠኝ ማይልስ ገደማ ርቃ የሚትገኝ አከባቢ ናት፡፡ ሌሎች ቃና በመባል የሚታወቁ ቦታዎች ስላሉ (ኢያሱ 19፡28)፣ ከእርሱ ለመለየት የገሊላ ቃና ተብሎ ይጠራል፡፡ ይሄኛው ቃና የነ ናትናኤል ትውልድ ቦታ እንደነበር ይነገራል፡፡

ቁ2 “ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።” ደቀ መዛሙርት የሚባሉት ከኢየሱስ ለመማር ሌሎች ስራዎቻቸውን ትተው የተከተሉት ሰዎች ናቸው፡፡ መጽሓፍ ቅዱሳችንን ስናጠና፣ እነዚህ ገብቶአቸው ጌታን የተከተሉ ሰዎች እንደሆኑ አንመለከትም፡፡ ግን ጥሪ ደርሶአቸው ነው፡፡ ቃል ተነግሮአቸው ነው የተከተሉት፡፡ ጥሪ ሲመጣ በአንድ ጊዜ ነው ጥሪው የሚፈልገውን ሕይወት መኖሪና የጥሪውን ምንነትም ሆነ ዓላማ መረዳት ግን በህዴትና በጊዜ የሚመጣ ነው፡፡

ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ አብረውት እየሄዱም ጥያቄ፣ ጥርጣሬ፣ ስጋት፤ ወዘተ. እንደ ነበራቸው ከመጽሓፍ ቅዱስ መማር እንችላለን፡፡ እውቀታቸው፣ እምነታቸው፣ መረዳታቸውም ያደገ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ያላወቁት፣ ያልተረዱት፣ የሚተራጠሩበት ነገሮች ነበራቸው ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ ግን ዛሬ (በቃና) ብዙዎቻቸውን ሊረዳ ይፈልጋል፡፡ ምን አድርጎ? ወደ ሰርግ ቤት አብሮአቸው ሂዶ፡፡ ከኢየሱስ ጋር ተኮኖ የሚከድበት የትኛውም ቦታ፣ የሚገባበት የትኛውም ሁኔታ ለጥቅማችን ይውላል፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡

በዛሬው (በቃናው) ሰርግ ቤት እንጀራና የወይን ጠጅ ሳይሆን እምነትን ጠግቦ የሚመለሱ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡ እንዴት እንዴሆነ በስተኋላ እንመጣበታለን፡፡ ለግዜው ኢየሱስና ደቀመዛሙረቱ ለሰርጉ እንደታደሙ አስተውለን እንለፍ፡፡

የጌታችን የኢየሱስ እናት የሆነችው ማሪያምም በቃና በተደረገው በዚህ ሠርግ ላይ ተገኝታ ነበረች፡፡

ቁ 3 “የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው።”

ከተናገረችው ነገር ተነስተን ስንገምት ምናልባት ከሙሽራው ጋር የዝምድና ወይም የጓደኝነት ትስስር ሳይኖራት አልቀረም ማለት ይቻላል፡፡ እንደ እንግዳ ሳይሆን የጓዳቸውን ችግር ትናገር ነበርና፡፡ ካልሆነም ደግሞ ምናልባት በዚያን ጊዜ ሴቶች ይቀመጡት የነበረው ቦታ ጋኖቹ ወደ ተቀመጡበት መደዳ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ችግር እንደ ነበረ አውቃ ወሬውን ወደ ኢየሱስ ያመጣች እርሷ ነበረች፡፡

ማሪያም እምነትና መታዘዝ ያላት ሴት ነች፡፡ በዚህ ቦታ፣ እንዴት እንደሚሆን ባይገባትም፣ ያልተለመደ ሥራን ልጇም ጌታዋም ከሆነው ኢየሱስ ትጠብቃለች፡፡ ኢየሱስ ብዙ ተዓምራትን ከሠራ በሃላ ቢሆን ለምሳሌ 500ሺህ ሰዎችን ከመገበ ቦሃላ ቢሆን ለማመን አያስቸግርም ነበር፡፡ ማሪያም ግን በማይመስል ሁኔታ ውስጥም ቢሆን እግዚአብሄርን መስማትና መታዘዝ እንደሚያዋጣ በሕይወቷ የተለማመደች ትመስላለች፡፡ የእምነት ሰው ያልተለመደ ነገርንም ጌታ እንዲያደርግለት ይጠብቃል፡፡

ኢየሱስ በዚያው አከባቢ ያደገና አገልግሎት እየጀመረ ያለ ቢሆንም ሌሎች ሰዎች ትኩረት የሰጡት አይመስልም፡፡ ማሪያም ግን ታውቀው ነበር፡፡

ለትንሽም ለትልቅም እግዚአብሄርን የሚትታመን ሴት ነበረች ማለት ይችላል፡፡

ከዚህን በፊት በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበ ኢየሱስ በገሃድ ያደረገው ተአምር ባይኖርም (ቁ11 ተመልከቱ)፣ ማሪያም ግን በዚህ ለሙሽራው ሃፍረት በሆነበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱን ገልጦ እንዲረዳው ፈለገች፡፡

“የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ” ማሪያም ወደ ኢየሱስ ሄዴች፡፡ ከጌታ ውጪ ለሰው ልጅ ችግር መፍትሄ የሚባሉ ብዙ ናቸው፡፡

በሠርጉ ቦታ ላጋጠመው ችግር ምናልባት ወደ ኢየሱስ መሄድ ብቸኛ አማራጭ እንዳልነበረ እገምታለሁ፡፡ ሌሎች መፍትሔ የሚመስሉ ግን በወቅቱና በአግባቡ የቤተሰቡን ጥያቄ የማይመልሱ ነገሮች እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡ ለምሳሌ፣ ለሰዎቹ በወይን ፈንታ ውሃ ማቅረብ፣ ማር በጥብጦ ማቅረብ ወይም ሌሎች በአከባቢው ሊገኝ የሚችል ነገር ማድረግ፣ ወይም ደግሞ ሩቅም ቢሆን ተሂዶ ወይን ተገዝቶ እንዲመጣ ማድረግ አማራጮች ናቸው፡፡

ግን ችግሩን ፈጽመው አይፈቱትም፡፡ አንዳንዶቹ መፍትሄ ተብየዎቹ ደግሞ ችግሩምን ያባብሱታል፡፡ ተስፋም አስጨራሾች ናቸው፡፡ ሰው “ይህንን ሞክረ ነበረ፣ ያንንም አግኝቼ ነበረ፣ ከዚያም ወስጄ ትንሽ ተሽሎኝ ነበረ፣ አሁን በቃ መሄጃ የለኝም” እንዲል የሚያደርጉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ተስፋ መቁረጥ ብዙዎች ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚደርስ እርምጃ እንዲውስዱ አድርጎአቸዋል፡፡

ሌላ ቦታ ወይን ፍለጋ ተሂዶም ቢሆን ምናልባት ግማሽ ጋን፣ ምናልባትም አንድ ጋን ሊገኝ ይችል ይሆናል፣ ያም ሲያልቅ ሌላ ስጋት አለ፡፡

ቀውሶች ሲፈጠሩ፣ የሚበረግጉ ሳይሆን፣ በእምነት አስቀድመው ወደ ጌታ ከዚያም ወደ ሰዎችም የሚሄዱና ለጌታ መታዘዝን የሚያበረታቱ ሰዎች አምልጠው ያስመልጣሉ፡፡

ከውጤቱ እንደምንረዳው የጌታችን እናት ማሪያም የመረጠችው ምርጫ በጣም አዋጭ ነበረ፡፡ ለዚያ ችግር ለዛቂ መፍትሄ ነበረና፡፡ ቀጣይ ስጋት የለውም ሕይወት ለጌታ በእምነት የተሰጠ ሕይወት ነው፡፡ አንደኛው ምርጫዋ ወደ ኢየሱስ መሄድ ነበረ፡፡ ችግሩን ለጌታ መንገር፡፡

ኢየሱስ የሚሠጠው መፍትሄ ዘላቅነት አለው፤ ጥራት አለው፤ አስተማማኝም ነው፡፡

ስለዚህ ደረሰብን ለምንለው ማንኛውም የራሳችም ሆነ የባለንጀራችን ችግር ወደ እርሱ እንህድና ለጌታ እንንገረው፡፡ ለጌታ ስንነግረው ምን እንሰማ ይሆን?

ቁ 4 “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።”

አንዳንዴ እምነታችንን ሊፈትን ጌታ ጥያቄአችንንም ያልተቀበለ ወይም ለጊዜው ዝም ያለን ሊመስል ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የመታዘዝ ልምምድ ውስጥ ሊያስገባን “እንዲህ አድርግ” ሊለን ይችላል፡፡ ግን የእርሱ መልስ ዘግይቶ ቢመጣም የሚያመጣው እርካታ ሌሎች ፈጣን የሚባሉ መፍትሄ መሳዮች ከሚያመጡልን እርካታ በእጅጉ ይልቃል፡፡ እንመን፣ እንጠይቅ፣ ለመታዘዝ እንዘጋጅ፣ ባይመስለንም ለእርሱ እንታዘዝ፡፡ ጌታ ይርዳን፡፡

ኢየሱስም ጊዜዬ አልደረሰም ብሎ ቢናገራትም በኃላ ላይ ለልመናዋ አዎንታዊ ምላሽ ሠጠ፡፡

ዛሬም ስለራሳቸውም ሆነ ስለ ሌሎች በእምነትና በእውነት ለሚለምኑት ሁሉ ጌታ መልስን ይሰጣል፤ ይረዳቸዋልም፡፡ ማሪያም እምነት ፈታኝ ንግግር ብትሰማም፣ በጌታ ችሎታ ላይ አንዳች ጥርጥር አልነበራትም፡፡ ግን ካለ ማመን ሊመጣ የሚችለውን እንቅፋት ለማስወገድ አገልጋዮችን ስለ መታዝ መከረች፡፡

ቁ 5 “እናቱም ለአገልጋዮቹ፦ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው።”

ማሪያም በጌታም ዘንድ በአገልጋዮቹም ዘንድ ተሰምነት ነበራት፡፡

ቁ 6-7 “አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፦ ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም።”

በዚህ ክፍል ውስጥ ለተገለጠው የኢየሱስ ሥራ የአገልጋዮቹ እያንዳንዱን ትዕዛዝ መቀበል ወሳኝ ነበረ፡፡ ጌታን ሰምቶ አለመታዝ በረከታችንን ከማየትና ከመጠቀም ይከለክላል፡፡ አገልጋዮቹ፣ ኢየሱስ ስላዘዛቸው ብቻ በወይን ቢቻ ሊሞላ በተዘጋጀ ጋን ውሃን ሞሉ፡፡ ኢየሱስ ስላዘዛቸው ብቻ ደግሞ በእጃቸው ወደ ጋኑ የጨመሩትን ውሃ በወይን መጠጫ አድርገው ለአሳዳሪው ሰጡ፡፡ የጌታን ድምፅ ሰምቶ መታዘዝ ከለሌ የጌታን ክብር ማየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ኢየሱስ ግን ምንም እንከን የሌለበትን ነገር አደረገ፡፡ ለሥርዓቱ በቆሙትን ስድስት ጋኖች ውስጥ ወይን እንዲገኝ አደረገ፡፡ በሥርዓቱ በኩል ፍጽምና ነበረ፡፡ በጥራትም ቢሆን ኢየሱስ ያስገኘው ምርጥ ወይን ነበረ ፡፡ የጌታ ሥራ በብዛትም ሆነ በጥራት ጥያቄም ችግርም አልነበረውም፡፡

ቁ 9-10 “አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፦ ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።”

ይህ የሠርጉ አሳዳሪ ንግግር ለሙሽው ምንኛ ክብር እንዴሆነ መገመት አያቅተንም፡፡

የሚለምንለት ስለተገኘ፣ ሙሽራው ሳያውቀውና ሳይሰማው በብዙዎች ዘንድ ከበረ፣ ተደናቂም ሆነ፡፡ ሰዎች አያውቁም (አሳዳሪውን ጨምሮ) የሙሽራውን ገመና ሸፍኖ እንዲህ ያከበረው ግን ኢየሱስ ነው፡፡

ኢየሱስ በእኛም ሕይወት ይህንን የሚመስል ብዙ አድርጎአል፡፡ እኛ ሳናውቀው እርሱ ብዙ ተሠርቶልናልና ሳይኖረን እንደሃብታሞች እንታያለን፡፡ የእኛ ትንሽ (ሁለት ዓሳና አምስት እንጄራ) ለብዙዎች ይበቃል፣ ደግሞም ጥራት ያለው በረከታችን መትረፍረፉ ብዙዎች ዘንድ (የቅርቦቻቸን ናቸው የምንላቸውን ጨምሮ) ጥያቄ ይፈጥርባቸዋል፡፡ ያደረገውና ክብሩ የተገባው ግን አምላካችን ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡

“አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፦ …. አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።”

የእኛን ክብርና ስኬት ምስጥር “ደረጃ መዳቢዎቹም” አያውቁትም፡፡ እንዴት እንዲህ ልትሠራ ቻልክ፣ እንዴት እንዲህ ልትኖር ቻልክ፣ እንዴት አስከ አሁን ኖረህ፣ እንዴት… እያሉ ብዙ ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡ ያደረገውና ክብሩ የተገባው ግን አምላካችን ነው፡፡

ከዚህ ሌላ መገንዘብ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡ እኛ ሳናውቀው ለተደረገልን መልካም ነገር ሌሎች በእውነት ወደ ጌታ የቀረቡ ሰዎች እንዳሉ መርሳት የለብንም፡፡ እኛም ደግሞ ስለ ሌሎች ስንቃትት እነርሱ ባያውቁትና ባያመሰግኑም ነገሮቻቸው እንደሚለወጥ እናምናለን፡፡ ለእኛም ለእነርሱም ግን የሚሠራው፣ ተአምር አድራጊው የሆነው ጌታ ነው፡፡

ቁ.9 “ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር

ነገሩ በትክክል ቢመረመር መስካሪዎች አሉ፡፡ ለበረከታችን፣ እኛ ለከበርንበት፣ እኛ ከሓፍረት የተረፍንበት፣ እኛ ከሞት የዳንበት ምክንያቱ ጌታ በልጆቹ ተለምኖ ደርሶልን እንደሆነ የሚመሰክሩ መስካሪዎች አሉ፡፡ እግዚአብሄር በጸሎቶቻቸው ስለረዱን ሰዎች የተባረከ ይሁን፡፡ ፀጋው በዝቶልን ለሌሎች እንዲንጸልይ ስለረዳንም ስሙ ይባረክ፡፡

ቁ.11 “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።”

ይህ ምልክት በመደረጉ የተነኩት ሙሽውና የቃና ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ግን ተከታዮቹ (ደቀ መዛሙርቱ) እምነት አገኙ፡፡ “በእርሱ አመኑ።” እያመነቱ የሚከተሉት፣ እየፈሩ የሚከተሉት፣ በደንብ ሳያውቁት ግን ስለተጠሩ ብቻ የተከተሉት እምነት አገኙ፡፡

ይህ ደግሞ በእግዚአብሄር መንግስት አሠራር ውስጥ አንዱ ተግባር (ማይልስቶን) ነበረ፡፡ ሠርጉም፣ የማሪያም በዚያ መኖርና መለመኗም፣ የአገልግጋዮቹ መታዘዝም ለጌታ መገለጥ ዕቅድ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ጌታ ክፉውን በደግ መለወጥ ይችላል፡፡ ለማዋረድ የመጣውን ነገር የራሱን ክብር ማሳያ ያደርጋል፡፡

እግዚአብሄር የአንዱን ቁሳዊ ባዶነት በመሙላት የሌላውን መንፈሳዊ ባዶነት ይቀይራል፡፡

ጌታ ይባርካችሁ

 

በተክሉ

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *