Uncategorized

መልካም ግንኙነት

መልካም ግንኙነት ,wilesofthedevil, Mekane Yesus in Scotland, salvation, prayer, resist,

እግዚአብሄር ሰው ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል::

እኔም ሰው ነኝ፡፡ እግዚአብሄር ሰው ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ይህ የሰውና የእግዚአብሄር ግንኙነት ፍላጎቱ ጥንት የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ለወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ወደ ራሱ አቅርቦ ፈጠረ፡፡ሰውም ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሄር ወስጥ የተፈጠረው ሰው ከፍጥረት ሁሉ የበለጠ ትልቅና ግዙፍ ስለሆነ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ግን ገና ሰውን ለመፍጠር ሲታቀድ፣ በእግዚአብሄር መልከና ምሳሌ ስለተፈጠረ ነው እንጂ፡፡ ከዚህ የምንረዳው መወደዳችን እኛ ከሰራነው ሥራ ሳይሆን፣ ቀድሞውኑ እግዚአብሄር እኛን ሊወድ ስለፈለገ ነው፡፡

እንግዲህ እግዚአብሄር ሰውን ከፈጠረ በኃላ በመልካም ሥፍራ አስቀምጦአቸው ብቻ አልተለያቸውም፡፡ ግን በየጊዜው ይጎበኛቸው ነበረ፡፡ እግዚአብሄር ሰው ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ዘንድ የተወደደ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አንቴም፣ አንቺም በእግዚአብሄር ዘንድ ውድ ነህ/ሽ ማለት ነው፡፡

በሰው ላይ አይኑን የጣለው ፈጣሪው እግዚአብሄር ብቻ አልነበረም

ይሁን እንጂ፣ በሰው ላይ አይኑን የጣለው ፈጣሪው እግዚአብሄር ብቻ አልነበረም፡፡ መላዕክቱም፣ በተለይ ደግሞ ሰይጣን ሰዎችን ትኩረት ሰጥቶአቸው ነበረ፡፡ ከሚወዳቸውም እግዚአብሄር ሊለያቸው ከኤደን ገነት ጀምሮ ብዙ ሙከራዎችን አደረገ፡፡ መልካሙን ግንኙነት ለማበላሸት፡፡ ዛሬም ይህ ቀጥሎአል፡፡እንዲህ ባይሆን “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።” ተብሎ ባልተጻፈልን ነበረ፡፡

እግዚአብሄር ፈቅዶ መልኩን፣ አምሳሉን፣ ፍቅሩን ሠጥቶት የሚመላለስበትን ሰው ከአምላኩ ጋር ለማጣላት ዓላማ ይዞ መሥራት ጀመረ፡፡ ሠይጣን የእግዚአብሄርን ጽድቅና ቅድስና ስለሚያውቅ፣ ሰዎችን በክብርና ታላቅነት ማታለያ የሸፈነውን የሞት መርዝ አቃበላቸው፡፡ ምክሩ በመጀመሪያ ሲሰማ መልካም፣ ለሰዎቹ ኣሳቢ ይመስላል፡፡ እነርሱም እንደ እግዚአብሄር መሆናቸውን የተመኘላቸውም ይመስላል፡፡ የምክሩ ዓላማና ውጤት ግን ራሱ በወደቀበት ውድቀት እነርሱን መጣል ነበረ፡፡ ከአምላክ ጋር የነበራቸውንም ግንኙነት ማበላሸት፡፡ ራሱ ከእግዚአብሄር በተለየበት መለየትም ከእግዚአብሄር ሊለያቸው ፈለገ፡፡ ራሱ ከትልቅ ክብር እንደወደቀ፣ ሰዎችም በእግዚአብሄር ዘንድ ካላቸው ክብርና የተባይነት እንዲወድቁ “ማታለል” የሚመባለውን የጦር መሳሪያ ተጠቀመባቸው፡፡

የመለየት ሥራ ዛሬም ቀጥሎአል

በሄዋን ላይ በጠላት የተጀመረው ያ የመለየት ሥራ ዛሬም ቀጥሎአል፡፡ ያ የጥንት የጦር መሳሪያውም ዛሬም መልኩ በተለያዩ ቀለሞች (በወርቅ፣ በብር፣ በናስ፣ በምግብ፣ በሥልጣን፣ በዝና፣ በደስታ፣ በክብር፣ ወዘተ.) እየተቀባ በብዙዎች እጅና ልብ ገብቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ሰው ከእግዚአብሄር ይልቅ ራሱን፣ ከዘላለሙ ይልቅ ጊዜያዊውን፣ ከሕይወት ይልቅ ሞትን በመታለል አስበልጦ ከፈጣሪው ጋር እየተራራቀ ይገኛል፡፡

እርሱ ባለበት በዚያ መኖር

ውድ አንባቢ ሆይ፣ አንቴ እንዴት ነህ? አንቺስ አህቴ? ለማን ከማን ጋር እየሠራህ/ሽ ነው? የሕይወት ቃል ወይስ ለጥፋትህ/ሽ ታስቦ የቀረበልህ/ሽን የጠላት ሽንገላ ተቀብለሃል/ሻል?

ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ መጥቶ እንደሚወስደን ቃል ገብቶአል፡፡ ከእርሱ ጋር እርሱ ባለበት በዚያ መኖር አትፈልግም?

ፀሎት

“እግዚአብሄር አምላኬ ሆይ፣ ስለምትወደኝ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ፡፡ ክቡር በሆነውን መልክህና ምሳሌህ ስለፈጠርከኝ ተመስገን፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተመላልሰህ በጠበቅህኝ ቦታ ስላላገኘህኝ ዕቅርታ እጠይቅሃለሁ፡፡ ከውድቀተ አንስቶኝ፣ ከጥፋቴም መልሶኝ ሕይወትን ይሰጠኝ ዘንድ ስለእኔ ስለሞቴውና ከሞትም ስለተነሳው ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ አከብርሃለሁ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከወደደኝና ስለእኔ ነፍሱን ከሰጠው ከልጅህ ከኢየሱስ ጋር መኖርን እፈልጋለሁ፡፡ በምህረትህ ተቀበለኝ፡፡ ያወቅሁ እየመሰለኝ ተታልዬ ከገባሁበት ማንኛውም ሁኔታ አንቴ አውጣኝ፡፡ ስሜን በሕይወት መዝገብ ጻፍልኝ፡፡ አንቴ የምትወደው ዓይነት ሰውም ሆኜ መኖር እንዲችል በጸጋህ እርዳኝ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፡፡ አሜን፡፡”

የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።” (ኤፌ 6፡11-12)

የንባብ ከፍሎች፡፡ ዘፍጥረት 2፡9፣ 3፡1-24፣ ዮሓ 1፡12-17፤ 14፡1-6

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *