Sermons

ሕይወት በገንዘብ

የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ

የሰው ሕይወት ማለት የገንዘብ ብዛት ማለት አይደለም (ሉቃ 12፡13-21)፡፡

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ እየተናገረ ነበር፣ በድንገት የሰውየው ጥያቄ ብቅ ያለው፡፡ እስቲ ስሙት። “ በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። በሰው ልጅም ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም። ወደ ምኵራቦችና ወደ መኳንንቶችም ወደ ገዢዎችም ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንድትመልሱ ወይም እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።

በመሃል፣ ምናልባት እጅ ያውጣ አያውጣ ባላውቅም አንድ ሰው ድምጹን ከፍ አድርጎ፣ “መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው።

በብሉህ ክዳን ህግጋት መሠረት ታላቅ ልጅ በርስት ውርስ ወቅት እጥፍ ይቀበላል (ዘዳ.21፡16-17)፡፡ ስለዚህ ይህ አበቶታ አቂራቢ የቤተሰቡ ታላቅ ሆኖ ግን ተገቢውን ክፋይ ያላገኜ ወይ ደግሞ ታናሽም ከሆነ የተገባውን ያላገኜ ነበረ፡፡ ስለዚህ ስለመብቱ ነው የጠየቀው፡፡

ሰውየው ምናልባት ያሰበው ወንድሙ ኢየሱስን ሰምቶ እና ፈርቶ የሚገባውን ውርስ እንዲያካፍልለት ነው፡፡ ኢየሱስ ተአምር አድራጊ ስለሆነ፣ መልካም አስተማሪም ስለነበረ፣ በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሞ ገንዘቡን/ንብረቱን ማግኘት ፈልጎአል፡፡

ይህ አይነቱ ባህሪይ በሰዎች መካከል ያኔ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በብዛት አለ፡፡ በእግዚአብሄር ስም አስፈራርቶ የሰውን ገንዘብ መውሰድ፣ ስሙን ለህይወት ሳይሆን ለምድራዊ ትርፍ እና የግል ምኞት ማስፈጸምያ፣ ለሕብረትና እና አንድነት ሳይሆን በሌላው ላይ ሃይል እና ስልጣን ለማግኘት የሚጠቀሙበት እንደማይጠፉ እገምታለሁ፡፡

እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥና ውጪ የሚደረገውን አገልግሎት ሁሉ እየተጠቀሙ፣ ሰዎች የእግዚብሄርን መንግሰት ቃል ሰምተው ልባቸው ‘ምን ላድርግ?’ በሚልበት ጊዜ፣ የራሳቸውን አጀንዳ እያነሱ አገልጋዮችንና ምእመናንን ግራ መጋባት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ሰዎችን የራሳቸው ባለዕዳ ለማድረግ ይጥራሉ። የንስሓ ገቢውን ትኩረት ያድናሉ።

ኢየሱስ ሕይወትን ወይም ስለ እግዚአብሄር መንግስት ሲናገር፣ ሰውዬው ደግሞ ገንዘብን የማግኛ ዘዴ በዚያ ተቀምጦ ያሰላስላል፡፡ ምናልባት በሌላ ሽምግልና ሞክሮ ያልተሳካለትን ዛሬ ብዙ ተሰሚነት እያገኜ ባለው በኢየሱስ ሊሳካለት እንደሚችል አስቦአል፡፡ የኢየሱስ ተልዕኮ አልበገረውም በገንዘብ ፍቅር የሚነዳ ልቡ አሸፍቶታል።

ስለዚህ ሰውዬው ኢየሱስ ባለበት ቦታ መገኘቱ የሚያስደስተው ለምድራዊ ችግሩ መፍቲሄ ሊያመጣ እንደሚችል ስለሚያስብ ብቻ ነው፡፡ የሰውየው ጥያቄ፣ ወደ እግዚአብሄር መንግስት እንገባ ዘንድ በውርስ ምክንያት ከተጣለን ወንድሜ ጋር አስታርቀን እንኳ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ጥያቄ አልነበረውም፡፡ ኢየሱስ እንዳስረዳው፣ ለሰውዬው ሕይወት ማለት ርስት ወይም ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ግን “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው” (ቁ.15)፡፡ ከስግብግብነት ተጠበቁ ማለቱ ነው፡፡ ያላችሁ ይብቃችሁ ማለቱ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ለምንድን ነው የተጠየቀውን ዳኝነት /ሽምግልናው እምቢ ያለው? ኢየሱስ ትኩረቱን ሰጥቶ ይሠራ የነበረው ለመጣለት ተልዕኮ ብቻ ነበረ። ከተልዕኮው የሚያስወጡት ነገሮች ደግሞ በየጊዜውና በየቦታው ያጋጥሙት ነበረ፡፡ ይህኛውም አንዱ ምሳሌ ነው። እርሱ ግን ተልዕኮውን ወደ ጎን ከመተው ይልቅ የሚቀርቡለትን ጥያቄዎችና ተግዳሮቶችን በመልካም እየተጠቀሜ ራሱን በዓላማው ውስጥ ይጠብቅ ተልዕኮውንም ይፈጵም ነበረ (ቁ 14)፡፡

እነ ጴጥሮስም መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኃላ፣ በአማኞች መካከል የተከሰተ ችግር ለመፍታት ስጠየቁ፣ ተልዕኮአቸውን ከመተው ይልቅ ያንን ስራ መስራት ለሚችሉ ሃላፊነቱን ሰጡ፡፡ ከኢየሱስ የተማሩ ነበሩና፡፡ “የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።” አሉ (የሓሥ.6፡ 2-4) ፡፡

እንደ ክርስቲያኖች፣ እንደ አገልጋዮችም፣ ነገሮች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ወይም ከወንጌል ስብከት ጋር ተያይዘው (ውስጥ ሾልከው) ስለተነሱ ብቻ ለሁሉም መልስ መስጠትና መፍትሄ ማበጀት አንችልም፡፡

አንዳንዱን ጻጋው ላላቸው መተው፣ ሌላውን ደግሞ እንደ አጋጣሚ ብቻ ተጠቅመን ተልዕኮአችንን መፈጸም እንዳለብን ከኢየሱስ እንማራለን፡፡

ኢየሱስ የተጠየቀውን ጥያቄ መነሻ አድርጎ ለጠያቂውና ለሌሎች ሰሚዎች ትክክለኛው ባለጠግነት “በእግዚአብሄር ዘንድ ባለጠጋ መሆን” ነው እንጂ ገንዘብና ንብረት ማከማቸት እንዳልሆነ ነገራቸው፡፡ በምድር ላይ የምናከማቸው ገንዘብም ሆነ ንብረት እዚሁ ምድር ላይ ይቀራል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ስንሄድ (ስንሞት) ይዘነው አንሄድም፡፡ ግን በየጊዜው የሚቀርብልንን የእግዚአብሄር ቃልና የደንነት ጥሪ ተቀብለን ለእግዚአብሄር ፈቃድ ራሳችንን ካስገዛን፣ በእግዚአብሄር ዘንድ ባለጠጎች ሆነናል ማለት ነው፡፡ በእርሱ አናፍርም እርሱም አያፍርብንም፡፡

ኢየሱስ በምሳሌው ውስጥ የነገራቸው ባለጠጋ ሰውዬ፣ ባገኘው ነገር ምስጋና አልነበረውም፡፡ ንብረቱ ለነፍሱ የሚበቃ ሀብት መስሎታል፡፡ የሕይወቱን ተስፋ ያደረገው ንብረቱ ብቻ ነበረ፡፡ እግዚአብሄር በህይወቱ ውስጥ ስፍራም ክብርም አልነበረውም ማለት ነው፡፡ ለሌሎች የማካፈልም ሓሳቡ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ነበር ያለው፣ “ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ”፡፡

ሰውዬው ለብዙ ዘመን የሚበቃው መብል አግኝቶአል ለራሱ ግን ብዙ ዘመን አልነበረውም፡፡ ብዙ ዘመን የሚለበስ ልብስ መግዛት ይችላል፣ ግን ብዙ ዘመን የሚኖር ሰውነት የለውም፡፡ ብዙ ዘመንንም በዚያ ንብረቱ መግዛት አልቻለም፡፡ እርሱ የብዙ ዘመን ህልም እያለመና ነፍሱን እያባበለ ነበረ፣ ለካ አንድ ቀንም አልነበረውም፡፡ “እግዚአብሔር ግን፦ አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው።”

ሕይወት እንግዲህ በጎተራ ውስጥ ተከሚሮ ዘመንን የሚያስቆጥር እህል፣ ባንክ ውስጥ ተከማችቶ ልብን የሚያሳብጥ ገንዘብ ወይም አንደኛው በሌላው ላይ ተሰካክቶ እንደሚታይ ግንብም አይደለችም፡፡

ሕይወት ከእግዚአብሄር ናት፡፡ የሕይወት ዋስቲና እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡ ያለ እግዚአብሄር ባለጠጋ መሆን የራስን ዘላለም መጉዳት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ “ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው” ብሎ አስጠንቂቆአልና፡፡

ስለዚህ ጌታን ረስቶ፣ ገንዘብ ብኖረኝ፣ ይህና ያ ቢኖረኝ ደስተኛ እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ከሞኙ ባለጠጋ ጋር አንድ ያደርገናል፡፡ አዎ ሃብት፣ ንብረት፣ ትዳር፣ ጓደኛ፣ ወዘተ. ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ሁሉ ይልቅ ግን እግዚአብሄርን ማወቅና መፍራት በጣም ያስፈልጋል፡፡

ዘመንን የሚሠጥ እግዚአብሄር ነውና ለነፍሳችን እና ለዘመናችን ባለቤት ራስን አሳልፎ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ “ የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ”፡፡

ውድ አንባቢ ሆይ፣ አንቴ/አንቺ ምን አለህ/ሽ? ለነፍስህ ምን ከምረሃል? ለነፍሳችን የሚያስፈልጋት በምድር እያለንም ምድርን ለቀን ስንሄድም ቋሚ ሀብትና ዋስቲና ሊሆናት የሚችለው የእግዚአብሄር ቃልና እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡

ስለዚህ ሳይረፍድብን፣ የሰበሰብነውን ለማናውቀው በትነን ሳንሄድ አሁኑኑ ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም ይኑረን፡፡ ልባችንን እና ሃሳባችንን ወደ ቃሉና ወደ ፈቃዱ እንመልስ፡፡ “ የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ”፡፡

የሰው ሕይወት ማለት የገንዘብ ብዛት ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ፣ በጥንትም ሆነ ዛሬ፣ ዘመዶችን/ወገኖችን ከሚያለያዩ ነገሮችና ብዙ ዓይነት የክፋት እና የአመጻ ሥራዎች እንዲስፋፉ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የገንዘብ ፍቅር ነው፡፡ ስለገንዘብ ብዙ ነገር በሰዎች ሕይወት ይሆናል፡፡ ውሸት፣ ስርቆት፣ ዝርፊያ፣ መጣላት፣ መለያየት፣ መግደል፣ ወዘተ. ስለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ተጠይቆ ሕይወት ማለት የገንዘብ ብዛት ማለት እንዳልሆነ ያስረዳው፡፡

በታሪኩ ውስጥ እንደምንመለከተው፣ ኢየሱስ ስለእግዚአብሄር መንግስት በሚያስተምርበት ጊዜ፣ ከሳሹ ሰውዬ ልቡና ጥያቄው ግን ወደ ገንዘቡ ነበረ፡፡

ሰማያዊ አጀንዳ እየተነገረን፣ ልባችንን ሌላ ነገር እንዲወረውና ቃሉ እንዲያልፈን አናድርግ፡፡ “ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” ተብሎ ተጽፎአልና (ማቴ 6፡33)፡፡

ዘመንን የሚሠጥ እግዚአብሄር ነውና ለነፍሳችን እና ለዘመናችን ባለቤት ራሳችንን አሳልፈን እንስጥ፡፡ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ”፡፡

እግዚአብሄር አምላክ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *