qophiiSermonsUncategorized

ልባችሁ እንዳይከብድ ተጠንቀቁ

ልባችሁ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ መካነ የሱስ፣ ግላስጎ መካነ የሱስ፣ ስኮትላንድ፣ ዪናይትድ ኪንግደም፣ Lutheran Church in Glasgow, ECMYIS, evangelical Church mekane Yesus in Scotland, Luk 21 25-36 'And there shall be signs in the sun, and in the moon, and in the stars; and upon the earth distress of nations, with perplexity; the sea and the waves roaring; Men's hearts failing them for fear, and for looking after those things which are coming on the earth: for the powers of heaven shall be shaken.

ሉቃ 21፡25-36 (ልባችሁ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡)

25 በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ 26 ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። 27 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28 ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።

29 ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ 30 ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 31 እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። 32 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 33 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። 34 ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ 35 በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። 36 እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።

በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ዘመን ምልክት በመናገር ሰዎች ከራሳቸው የሚጠበቀውን ነገር እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል፡፡
ሰው ብዙውን ጊዜ ነገሮችን ማድረግ ወይም አለማድረግ የሚፈልገው ነገሩ መልካም ወይም ክፉ ስለሆነ ሳይሆን የሚያደርገው ነገር በራሱ ወይም በሌሎች ሕይወት ላይ ሚያመጣውን ተጽኖ በመጠየቅ ነው፡፡
ይህ ማለት፣ ምንም እንኳ እግዚአብሄርን ስለሚገባው ብቻ ማምለክ ቢኖርብንም፣ የብዙዎቻችን አምልኮ ከፍርሃት፣ ከደረሰብንና ሊደርስብን ይችላል ብለን ከምናምናቸው ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በዚህም ቦታ ኢየሱስ ስለመጨረሻው ዘመን ሲናገር ሊመጡ ያሉትን ነገሮች አንድ በአንድ አንስቶ ከተናገረ በሃላ፣ እነዘህ ነገሮች እንዲቀሩ ለማድረግ ዓላማ እንደነበረው ምን ምልከታ አልሰጠም፡፡ በተጨማሪም ደግሞ እነዚህ ምልክቶች እንዳይከናወኑ ለምኑ ሲልም አናየውም፡፡ ይልቁንም፣ ጸልዩ ያለው በዚያ ውስጥ አልፋችሁ፣ በሰው ልጅ ፍት መቆም እንድትችሉ በማለት ነው፡፡  ይህ ምን ማለት ነው?

ከዚህን ክፍል በፊትና ባለው  የኢየሱስ ትምህርትና በሌሎችም የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ እንደምናነበው በመጨሻው ዘመን የሚሆኑ ብዙ ነገሮች ለሰዎች ልጆች አስቸጋሪና አስጨናቂ እንደሆኑ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ደግሞ ከአምላክ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ከራሳቸውም የሚነሱ እንደሆኑ ያሳያሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በሰዎች ልጆች የሚደረጉ ነገሮች ሰዎችን ከአምላክ የሚያርቁና ሰዎች እርስ በርሳቸው ላይ ክፋትን እንደሚፈጽሙ ያሳያል፡፡ ከዚህም የተነሳ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ብቻ ሳይሆን በሰዎችም መካከል ፍቅር እንደሚቀንስ፣ የፍቅር መቀነስ ውጤቱ ደግሞ የጦርነት ወሬዎችና ጦርነቶች በብዛት እንደሚሰሙ ማድረግ፣ ከእነዚህ የተሳ ደግሞ ረሃብ እንደሚሆን ተናግሮአል፡፡

በተጨማሪም ደግሞ ከተፈጥሮ ህደቶች መቃወስ እንደሚጀምሩ ብዙ የመሬት መንቀጥቀጦች እንደሚሆኑ፣ የሰማያት ሃይላትም እንደሚናወጡ ጭምር ኢየሱስ ተናገረ፡፡ እነዚህና ሌሎችም ነገሮች የሰዎችን ኑሮ በሙሉ ችግርና ፍርሃትና ሽብር ውስጥ እንደሚከቱ መገንዘብ አያስቸግርም፡፡
ዛሬ በምድርቱ ዙሪያ የሚታዩ የሽብር ተግባራት፣ የአየር ንብረት ለውጦች፣ ከንግድ፣ ከፖሌትካ፣ ከብሄርተኝነትና ከግሎባላይዘሽን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰጣ ገባዎች፣ የሳይበር ጦሪነቶች እና ሌሎችም ነገሮች በምድሪቱ የሚኖሩትን ሰዎች ሕይወትና ሰላም በብዙ ስጋት ውስጥ ከቶአል፡፡ ሰዎች ሰላምና ደስታ ስርቃቸው በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ብዙ ጉዳቶችን ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ እናንተ ግን ልባችሁ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡

ጌታ ኢየሱስም “ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ” ብሎአል፡፡
ስለዚህ ምን እናድርግ? ወደሚውለው ኢየሱስ ይመልሰናል፡፡
1. ምልክቶቹን እወቁና ሊመጣ ያለውን ነገር ተገንዘሁ፡፡
2. ተዘጋጁ፣ “ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”፡፡ አንዳንድ ሰው የደረሰበትን ጉዳት ሲገልጽ ከዚህ በላይ ምን ይደርስብኛል ብሎ ይናገራል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ሆኖ እና ተነግሮ የማይታወቅ አንድ ትልቅ ቀን እንዳለ አመልክቶአል፡፡ ይህ ቀን ለብዙዎች እንጅግ አሰቃቂ ቀን ሲሆን በሌሎች (በተለይ በጌታ ኢየሱስ አምነው ምህረት በማግኘት እርሱን ለሚጠባበቁት) ደግሞ የልዩ ደስታ ቀን ነው፡፡ ለእነርሱ ብርሃናት ሁሉ ሲጨልሙ ልዩ ብርሃን ይበራላቸዋል፡፡ ሰላም ሁሉ ሲጠፋ ልዩ ሰላም ያገኛቸዋል፡፡ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።” ቁ 28፡፡ ስለዚግጅት ነው፡፡
3. ትጉ፡፡ ተግታችሁ በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ “ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ”
አማኞከች ሊመጣ ያለውን ማስቀረት ባይችሉም፣ ግን “ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ” ማምለጥ እንደሚችሉ ኢየሱስ ተናግሮአል(ቁ 36)፡፡  ልባችሁ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡

ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው በጸሎት ነው፡፡ ጸሎት በብዙ መንገድ ልደረግ ይችላል፡፡ ግን ትርጉሙ አንድና አንድ ነው፡፡ ፀሎት ማለት ከእግዚአብሄር ጋር መነጋር ነው፡፡ ይህ መነጋገር መስማትና ማሰማት አለበት፡፡ ማዳመጥና መናገር፡፡ መጠየቅና መመለስ፡፡  እግዚአብሄር ሊሆን ያለውን በሙሉ ቀድሞ የሚያውቅ ብቸኛ አምላክ ነው፡፡

ስለዚህ ከእርሱ ጋር ወዳጅነትን የሚመርጥና ከእርሱ ጋር የሚነጋገር ሰው ደግሞ መቼ ምን ማድረግ እንደሚገበው ከእርሱ መማር ይችላል፡፡  ስለዚህ ነው “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።” ያለው፡፡
ሌለው በዛሬው ክፍል ውስጥ የምንመለከተው ነገር፣  በዚያ በመጨረሻው ዘመን የብዙዎች ልብ እንደሚከብድባቸው ነው፡፡ ልብ አክባጆች ተብሎ በዚህ ክፍል የተጠቀሱት ውስጥ፣ የመጠጥ ብዛት፣ ስካርና ስለ ትዳር ማሰብ ናቸው፡፡ እነዚህ ሶስቱ ነገሮች በጋራ ያላቸው ባህሪይ ብኖር፣ የሰውን ጊዜ፣ ሙሉ ልብና አእምሮ መውሰዳቸው ነው፡፡ እነዚህን አንድ በእንድ ምን ማለት እንደሆኑ እንያቸ(ቁ 34)፡፡

መጠጥ – የአምልኮን መልክ ይቀይራል፡፡ ካህኑ አሮንና ልጆቹ ወደ በቴ መቅደስ ለአምልኮና ለአገልግሎት ሲገቡ እንዳይጠጡ በእግዚአብሄር ተከልክሎአል፡፡ “እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል” (ዘለዋ 10፡8-9)፡፡

ከመጠጥ ብዛት ስለመጠንቀቅ የተሠጠው ማሳሰቢያ ስለወይንና ስለሌሎች የመጠጥ ዓይነቶች ብቻ የተነገረ አይመስልም፡፡ ሰው የተለያዪ መጠጦችን የሚጠጣው እርካታ ለማግኘት ነው፡፡ ለመዝናናት ነው፡፡ ስለዚህ እርከታ አገኝበታለው በሚል ሰበብ የሚረጉ ማናቸው ልብን የሚያከብዱ ነገሮች ጥንቃቄ ያሻሉ፡፡ እርካታ ልናገኝባቸው ስናግበሰብስ አእምኖአችንና ልቦታችንን ያከበዱብን ነገሮች ምን ይሆኑ? ጌታ ኢየሱስ ከእነዚህም እንድንጠነቀቅ ይፈልጋል፡፡ ልባችሁ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡

ስካር – ስካር ከመጠጥ ቀጥሎ የሚመጣ የሰው አእምሮአዊና አካላዊ ሁኔታን ይገልጣል፡፡ መጽሓፍ ቅዱስ ሲናገር “ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል” ይላል (ሆሴ 4፡11-12)፡፡ “wine take away the heart”/ “old wine and new, which take away the understanding of my people.”

የሠከረ ሰው መጀመሪያ ራሱን መቆጣጠር ይሳነዋል፡፡ አፉ ያመልጠዋል፣ ንግግሩ ይቀየራል፣ ቋንቋው ይደበላለቅበታል፡፡ ከሥርዓቶችና ከኖረሞች የወጡ ነገሮችን መናገር፣ ማድረግ ለእርሱ ይቀላል፡፡ ለመሄድ ሲነሳ (ከቻለው ማለት ነው) እግሮቹ አይታዘዙለትም፣ ቀጭን መንገድም አይበቃውና ለብዙ መሰናከል፣ መውደቅና መቁሰል ይጋለጣል፡፡

በሌላ መልኩ ስናየው ደግሞ በመጽሓፍ ቅዱስ የተለጠው ስካር ከወይን የተነሳ ስለሚመጣ ስካር ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ በጽድቅ ጎዳና በእግዚአብሄር ፈቃድና ሕግ እንዳይሄድ አድርገው የሚያንገደግዱ ነገሮችን ሁሉ ያጠቃልላል እንጂ፡፡ ዛሬ የሰውን ልጅ ያሰከረ ብዙ ነገር አለ፡፡ ካሉበት ስካር የተነሳ አንዳንዶች ተኝተዋል፣ አንዳንዶች ወድቀዋል፣ አንዳንዶች መንገድ ስተዋል፣ ብዙዎች በብዙ ቁስል ተጎድተዋል፣ የብዙዎች ሰላም፣ ደስታ፣ ተስፋ፣ የአምልኮ ሕይወት፣ በእግዚአብሄር ጸጋ የተሰጣቸው  በረከቶች በሌባው በዲያብሎስ ተወስዶባቸዋል፡፡

ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ  በመጠጥ ብዛት ወይም በስካር እያላችሁ “ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ብሎ አስጠነቀቀ፡፡
ስለትዳር ማሰብ (cares of this life)- ይህ የኑሮ ጭንቀትን፣ ዓለማዊ ሃሳብን ያመለክታል፡፡ ጭንቀት ልብን ከሚያከብዱ ነገሮች አንዱ ነው፡፡  ሰው በእግዚአብሄር መታመን ሲያቅተው ነገሮችን ሁሉ በራሱ መጀመሪና መጨረስ ስለሚሞክር፣ በራሱ ዓቅም ልሠሩ ወደማይችሉ ነገሮች ስደርስ በብዙ ጭንቀርትና አላስፈላጊ የሕይወት ጎዞዎች ወስጥ ይገባል፡፡

ይህ ደግሞ በኢየሱስ ትምህርት ውስጥ እንደተገለጠው፣ የእግዚአብሄርን ቃል እንዳያፈራ በማድረግ ሰው ገለባ የሆነ ሕይወት ብቻ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በማቴ13፡22 “በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል።”  ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በዚህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ እያላችሁ “ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ብሎ አስጠነቀቀ፡፡

ሐዋሪያውም ጳውሎስ፣ “ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።” (ፊልጵ 4፡6)

“ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።” (ሉቃ 21፡ 34-36)
ጌታ ይባርካች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *