SermonsTeachingsUncategorized

ለድሆች ወንጌል

“ለድሆች ወንጌልን እሰብክ” ድህነት የገንዘብ እጦት ችግር ብቻ እንዳይደል ከዚህ እንገነዘባለን፡፡ ለደሃ ትልቁ የሚያስፈልገው ደግሞ ወንጌል ነው፡፡ ከወንጌል ሰው ሕይወትን ይጠግባል፣ ሠላምን ይጠግባል፣ እረፍትን፣ ደስታን፣ ፍቅርን፣ ተስፋን፣ ወዘተ. ይጠግባል፡፡ECMYIS, mekane Yesus Scotland, Mekane Yesus in SCotland, Glasgow Mekane Yesus, Makane yesus is Glasgow, Mekana Yasuus, Lutheran Church Glasgow, Amharic Service, Oromo, Tigrigna, Christian church in Glasgow, Evangelical Christian church, Salvation,Ethiopinan church glasgow, Erthrian and Ethiopian Christian Church, sermons, Sunday service, Jesus Christ saves. he came to Nazareth, where he had been brought up: and, as his custom was, he went into the synagogue on the sabbath day, and stood up for to read.18 The Spirit of the Lord is upon me, because he hath anointed me to preach the gospel to the poor; he hath sent me to heal the brokenhearted, to preach deliverance to the captives, and recovering of sight to the blind, to set at liberty them that are bruised,19 To preach the acceptable year of the Lord.

የዛሬው የ ወንጌል ክፍል፡ ሉቃ 4፡14-21

ቁ 14 “ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ።”

ኢየሱስ እየተመለሰ ያለው፣ ከፈተና ሜዳ ነበረ፡፡ 40 ቀናት ከፆሜና ከጸለዬ በኃላ ፈታኝ እንደመጣ መጽሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ እነዚህ ፈተናዎች ለዘመናት ተሠርቶባቸው ውጤታማ ሆነው የተገኙ፣ ብዙዎች በእነረሱ የወደቁ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ሰይጣን በሌሎች ላይ (ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ) ከተጠቀማቸው ብዙ ዓይነት ፈተናዎች ምርጦቹንና ጣዮች መሆናቸው የተረጋገጠላቸውን ለኢየሱስ አቀረበ፡፡ ኢየሱስ ግን ፈተናውን ሁሉ በእግዚብሄር ቃል መልስ ሠጠበት፡፡ ለራሱ መናገር እየቻለ፣ ግን እኛ ከእርሱ እንድንማርና ፈተና በገጠመን ጊዜ ረዳት የሌለን አድርገን ራሳችንን እንዳንቆጥር የተጻፈውን ቃል ተጠቀመ፡፡

ከሰይጣን ለኢየሱስ የቀረቡትን ፈተናዎች አጠር አድርጎ ለማንሳት ያክል

  1. ኢየሱስ በተራቤ ጊዜ በቀላሉ እንጄራ መብያ መንገድን አሳየው (ቁ 3-4)፡፡ ሰው ሲራብ የሚሆውን ነገር የተራቤ ሰው ብቻ ያውቀዋል፡፡ የሚበላ ይገኝ እንጂ ምግቡ የተገኘው በማናቸውም መንገድ ይሁን (ዘርፎም፣ ገድሎም፣ ሰርቆም፣ ለምኖም) ብቻ መብላት ይፈልጋል፡፡

የመብል ነገር ብዙ ታላላቅ ሰዎችን ጥሎአል፡፡ ኢየሱስ እንደኤሳው ከሞትኩ በሃላ ብኩርና ምን ያደርግልኛል አላለም፡፡

ኢየሱስ ግን የሰው የመኖር ዋስትና እንጀራ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሄር ቃልም እንደሆነ በመናገር መለሰለት፡፡ እንጀራ ተጨማሪ ነገር ነው አለው፡፡ ለኢየሱስ መኖር ማለት ከአንድ ቀን ወደ ሁለተኛው ቀን መሻገር ብቻ ሳይሆን፣ ለዘላም ከእግዚብሄርም ጋር መኖር ነው፡፡

ስለዚህ በኢየሱስ አገላለጥ፣ ያለእርሱ ሕይወት አይኖረኝም የሚባል ከዘላለም ጥፋት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው፣ አምነው ለሚቀበሉት ሁሉ የዳግም ልዴት እድል የሚሰጠውና እግዚአብሄርን ከመበደል ከሚመጣ ኩነነ የሚያድነው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል የጠላትንም ፈተና ማሸነፊያ ነው፡፡

2. ሌላው ፈተና፣ ኢየሱስ በጭር መንገድ “ሀብትን፣ ሥልጣንና ክብርን” የሚያገኝበትን መንገድ አሳየው (ቁ 5-7)፡፡ ይህ ፈተና በአዳምና በሔዋን ላይ ሰርቶ ነበር፡፡ ከኤደንም የወጡትበት በዚህ ፈታና ነው፡፡

በታሪክም ስንመለከት ሥልጣንና ክብር ለማግኘት ዘመዶቻቸውንና በተሰቦቻቸውን ሁሉ እስከመግደል የደፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ አቤሰሎም በዳዊት ላይ የተነሳው፣ የዳዊት ልጆች ና ሰለሞን ልጆችም እርስ በርሳቸው እስከመገዳደል የደረሱት ለዚህሁ ነው፡፡ በዓለም ታሪክም ብዙ ተመሳሳይ ነገር እናነባለን፡፡

ስለዚህ እንደ ሰይጣን አነጋገር ሥልጣንና ክብር ለማግኘት የእግዚአብሄር ቃል መጠበቅ፣ መጾምና መጸለይ፣ የራስን ጥሪ በታማኝነት መወጣት ሳይሆን ወድቆ ለእርሱ መስገድ መስገድ ነው ፡፡ ይህም ውሸት ነው፡፡ አለምና ሞላዋ የእግዚአብሄር ናትና፡፡ ግን ሰይጣን ራሱ የወደቀበትን፣ ሌሎችንም የጣለበትን ይህንን ፈተና ሲጠቀም ኢየሱስን ከአባቱ ጋር ለማጣላት አስቦ ይሆናል፡፡

  1. ሌላው ፈተና የራስን ፍላጎት (ጊዜያዊ ደስታ) ለማሟላት እግዚአብሄርን መፈታተን፡፡ ያለ አግባብ ለመኖር የእግዚአብሄን ቃል መከታ ማድረግ፡፡ ይህም ከእስራኤላዊያን ብዙዎች ከግብጽ ወጥተው በምድረ በዳ ላይ ያለቁበት ፈተና ነው፡፡

 

እንግዲህ የእነዚህ ሁሉ ፈታናዎች ጥንካሬ ያለው ልብንና ሓሳብን በእውነትና በመንፈስ ከሆነው አምልኮ አውጥቶ፣ አምልኮን ለራስ ጥቅምና ፍላጎት መሟያ፣ ለስልጣንና ለክብር እንዲሁም ለራሳችን የቅንጦት ጥማት ማርኪያ ወደማድረግ መውሰድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሄር ላይ ማመጽ ይባላል፡፡ እግዚአብሄር እነዚህን ሁሉ ይጸየፋቸዋል፡፡ ኢየሱስ ግን በአባቱ ላይ ከማመጽ መራብን፣ ደሃ እና አቅም የሌለው መስሎ መታየትን መረጠ፡፡ ኢየሱስ እነዚህ ፈተናዎች በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃል አሸንፎአቸዋል፡፡

ዛሬም ቢሆን የእግዚአብሄርን ቃል መጠቀም፣ ለሕይወታችን ነጻነት፣ ድልና ስኬት ሃይልና ጥበብ ይሠጠናል፡፡ የጌታ ቃል በልቡ የተሰውረ ሰው ከብዙ መሰናክሎች ይድናል፡፡ ዳዊት ሲናገር፣ “አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርኩ” ይላል (መዝ 119፡11)፡፡

ሰው ሳይራብ የሚቀርብለትን ጥሩ ምግብ መናቅ ይችላል፣ ሳይዋረድ የክብር ግብዣ አያስደንቀውም፡፡ ግንሰው ሲራብ ፈተናው እጅግ ከባድ ይሆንበታል፡፡ እየሱስም ምጹም ሰው ሆኖ ነበርን ፈተናው ቀላል አልነበረም፡፡

ማንም ሰው ከብዙ ጾምና ፈተና በሃላ እየተንገዳገደ፣ እየፈራ፣ እየተደናገጠ ሊመላለስ ይችላል፡፡ ኢየሱስ ግን ከፈታናው ሜዳ፣ ሲመለስ በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ነበረ (ቁ14)፡፡ ሠይጣን “እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ” የሚለውንም እያወቀ፣ በእርሱ የነበረው የአሻናፍነት ቃልና መንፈስ ሃይልን አግኝቶ ነበረ፡፡ ሰውነቱ የዛሌ፣ የተጎዳቆለም ሊሆን ይችላል፣ ግን የመንፈስ ቅዱስ ሃይል በሙላት በእርሱ ላይ ነበረ፣ ውስጡም በቃሉና በሃይሉ የተሞላ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ “ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ

በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው የእግዚአብሄር ቃል ሙላትና የመንፈስ ቅዱስ ሐይል ሙላት በሕይወቱ ይገለጡ ነበረ፡፡ አንዱን ከሌላው መነጠል አይቻልምና፡፡ ይህ ደግሞ ኢየሱስን እየገለጠው መጣ፡፡

ቁ 15 እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።

ምኵራብ ብዙ ሺህ ሰው የተሰበሰበበት ቦታ አይደለም፡፡ ምኵራብ እግዚብሄርን የሚፈልጉና የሚያመልኩ ጥቅት ሰዎች በየሰፈራቸው ተገናኝተው መጽሓፉን የሚያነቡበት እና የሚያመልኩበት ቦታ ነው፡፡

በቃልና በመንፈስ ቅዱስ ሃይል እየተመላለሰ ያለው ኢየሱስ “በምኵራባቸው ያስተምር”፡፡ ለዓለም ሁሉ የሚሆን መልእክት የነበረው ኢየሱስ ጥቅት ሰዎች ጋር አገልግሎቱን ጀመረ፡፡ ከጥቂት መጀመር ሁሌም የእግዚአብሄር ባህሪህ ነው፡፡ ምድርን በሰዎች ለመሙላት ሲነሳ፣ መጀመሪያ አንድ ሰው ፈጠረ፡፡ በዓለም ያሉትን ሁሉ ሓጢአተኞች ለማዳን ሲያቅድ፣ አብራም የሚባል አንድ ሰው ጠራ፡፡ በእርሱ ላይ ያመጹ የእስራኤልን መንግስትና ህዝብ ወደ ራሱ ለመመለስ አንድ ኤሊያስን ተጠቀሜ፡፡ ኢየሱስም በዓለም ያሉትን የሰው ዘር ሁሉ ለማዳን ሲመጣ ጥቅት ደቀ መዛሙርትን ጠራ፡፡ በምኵራብም ሂዶ ያስተምር ነበረ፡፡

በኢዮብ ውስጥ (8፡7) “ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል።” ይላል፡፡

ኢየሱስ ሲያስተምር ሰዎች “ያመሰግኑት” ነበረ፡፡ ሰዎች በቀላሉ ወደ ምስጋና አይደርሱም፡፡ ብዙ ጊዜ ከማመስገን ይልቅ ድክመትን ፈልጎ መክሰስ ቀላል ስለሆነ፡፡ ኢየሱስ ግን በምኵራቡ ተገኝቶ ሲያስተምራቸው ለሰዎች የምስጋና ምክንያት ነበረ፡፡ እነዚህ ከናዝሬት ውጪ ባለች ምኵራ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በናዝሬትስ ሰዎች ምን ይሉ ይሆን?

ቁ 16 “ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ።

ኢየሱስ ወደ ምኵራብ የመሄድ ልማድ ነበረው፡፡ ጥቂቶችም ቢሆኑ ተሰብስበው ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር መገኘትን ልማዱ አድርጎት ነበረ፡፡ ከልጅነቱም ጀምሮ በበተመቅደስ መገኘት እንደሚያስደስተውና የአባቱ ቤት እንደሆነ እንደሚናገር እናነባለን፡፡

ታዲያ ዛሬ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ወይም ወገኖች ተሰብሰበው ወደሚያመልኩት ቦታ መሄድን የሚያናንቁት ለምን ይሁን? ለምንስ ወደ ወገኖች ስብስብ ላለመሄድ ቤቴ ማምለክ እችላለሁ፣ ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎችን ብቻ በመጠቀም ማምለክ እችላለሁ እንላለን? ኢየሱስ ራሱ ምኵራብ መሄድ ልማዱ አድርጎት ነበረ፡፡

እግዚአብሄር በግል እንደሚመለክ በጋራ ደግሞ አማኞች ሊመለክ ይፈልጋል፡፡ ዛሬ የፈለገ ሁኔታ ቢመቻችልና ጥሩ አገልግሎት ማግኘት ብነችልም፣ ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ከነበረው ግንኙነት የበለጠ ግንኙነት ከእግዚአብሄር ማድረግ አንችልም፡፡ እኛ ወደ አብ መቅረብ የተሰጠን ራሱ በእርሱ ስለሆነ፡፡ ኢየሱስ እነዚህ በብዙ ችግሮች፣ በብዙ ጉስቁልና፣ እስርና በብዙ ግራ መጋባት ውስጥ የነበሩ የምኵራብ ሰዎች ጋር ይገኝ፣ ያገለግላቸውም ነበረ፡፡

እነርሱ ማንነቱን እንኳ አያውቁትም ነበር፣ የሚገባውንም ክብር ሰጥተውት አቀባበልም አላደረጉለትም፡፡ እርሱ ግን በመካከላቸው መገኘትን ልማዱ አድርጎ ነበረ፡፡ በተጻፈው የእግዚአብሄር ቃልም ወደ መረዳት ሊያመጣቸው ያስተምራቸው መጽሓፍትን ያነብላች ነበረ፡፡

17-19 የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።”

ይህ ኢየሱስ ያነበበው ክፍል ገና እርሱ ከመወለዱ በፊት ከ700 ዓመታት ቀድሞ ስለእርሱ ተጽፎ የነበረ ትንቢት ነው፡፡ ነገሮች ከመሆናቸው በፊት ያቀደውና የተናገረው እግዚአብሄር ታማኝ ስለሆነ ጊዜው ደርሶ ትንቢቱ ፊጻሜ እንዳገኘ ኢየሱስ ተናገራቸው፡፡ ቢዘገይም እግዚአብሄር ያለው ይሆናል፡፡

በዚህ ክፍል ውስጥ አንድ የምንማረው ነገር፣ ኢየሱስ ለምን እንደመጣ ዓላማውን ከእግዚአብሄር ቃልና ፈቃድ አንጻር ጠንቅቆ ያውቅ ነበረ፡፡ ይህ እውቀት ደግሞ ፈተናዎችን እንዲያሸንፍም ረድቶታል፣ መከራን ሁሉ በትእግስት እንዲቀበልም አድርጎታል፡፡

ሰይጣን ኢየሱስን ሊፈትን ፈልጎት የነበረው፣ ኢየሱስ በአግባቡ ተልዕኮውን እንዳይፈጽም ለማድረግና በአቋራጭ መንገድ የሚገኝን ክብርና ሀብት በማሳየት እርሱም ቢሆን ወደ እርሱ(ሰይጣን) ጊዛት እንዲገባ ነበረ፡፡ ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ያውቅ ነበርና በእርሱ ቃል ሰይጣንን አሸነፈው፡፡

ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳያውቅ ሲቀር በቀላሉ በነገሮች ይታለላል፡፡ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል” የሚለው ቃል ይህንን ያረጋግጥልናል፡፡

ኢየሱስ ራሱ ደግሞ ለሰዱቃውያን ሲናገር፣ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን?” አላቸው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ማወቅና ያወቅነው ቃል ደግሞ በእምነት ከሕይወታችን ጋር ሲዋሃድ (ዕብ 4፡2) የሚፈጥረው ነገር በማናቸውም መንገድና ሁኔታ የሚመጣብንን ፈተና ለማሸነፍ ይረዳናል ፡፡

የጌታ መንፈስ በሰዎች ላይ የሚመጣው የግል ሀብትና ክብር ሊሠጣቸው ሳይሆን እነዚህ እየሱስ በዚህ ምድር ሊያደርጋቸው የመጣውን አገልግሎት ሊያስቀጥል ነው፡፡

  • ለድሆች ወንጌልን እሰብክ

ድህነት የገንዘብ እጦት ችግር ብቻ እንዳይደል ከዚህ እንገነዘባለን፡፡ ለደሃ ትልቁ የሚያስፈልገው ደግሞ ወንጌል ነው፡፡ ወንጌል ከድህነት ወደ ሁለንተናዊ በረከት ያመጣል፡፡ በወንጌል መርገም ይሻራል፣ በወንጌል ብቸኝነት ይገፈፋል፣ በወንጌል ብዙ አይነት ረሃብ ይርቃል፡፡ ከወንጌል ሰው ሕይወትን ይጠግባል፣ በረከትን፣ ሠላምን ይጠግባል፣ እረፍትን፣ ደስታን፣ ፍቅርን፣ ተስፋን፣ ወዘተ. ይጠግባል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የመጣበትን ምክንያት ከእግዚአብሄር ቃል አንጻር ሲናገር ለድሆች ወንጌልን ለመስበክ ነው ይለዋል፡፡ የእኛ ጥሪ፣ አገልግሎት፣ የኑሮ ዓለማ ምን ይሁን?

  • “ለታሰሩትም መፈታትን

ሰዎች ከእግዚብሄር ፈቃድ ወጥተው ሲኖሩ በብዙ እስራት ውስጥ ራሳቸውን ያገኛሉ፡፡ በኋጢአትና በሠይጣን እስራት ተሸንፎ በብዙ ጉዳት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከታሰሩበት እስራት ነጻ መውጣት የሚችሉት በወንጌል ቃል አምነው ልባቸውን ወደ እግዚአብሄር ሲመልሱ ብቻ ነው፡፡

ኢየሱስ በእግዚብሄር መንፈስ ሃይል የተገለጠው እነዚህን ዓይነቶቹን ሰዎች፣ እኔንና እናንተን ጨምሮ ማለት ነው፣ ነጻ ለማውጣት ነው፡፡

ዛሬም ሰዎች በመንፈሱ ሓይል ሰዎችን ሲያስነሳ የታሰሩ ሰዎች ነጻ እንዲወጡም ነው፡፡ ወንጌል ሰባኪዎች፣ መስካሪዎች፣ ዘማሪዎች፣ መሪዎች፣ በተለያየ መልኩ እግዚአብሄርን የሚያገለግሉ ሰዎች ተልኮአቸው ወንጌልን ማድረስ፣ መልእከታቸውም ለታሰሩት መፈታት እንዳለ ማወጅ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች ከችግራቸው መውጫ መንገድ እንዳለ ወይም ከእስራታቸውም መፈታት እንደሚችሉ ስለማያውቁ፣ እስር ቦታቸውንና ያሰራቸውን ሁኔታዎች አመቻችተው በዚያ መኖርን የእለት ተዕለት ተግባራቸው አድርገው ይኖራሉ፡፡

ስለዚህ ኢየሱስም ለማድረግ እንደመጣው፣ በኢየሱስ አምነው በእርሱ መንፈስ የሚመሩ ሰዎች “መፈታት” እና ነጻነት አለ የሚል መልእክታቸውን ለሁሉም ማሰማት አለባቸው፡፡

  • “ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ

ሰላም መልካምም እየመሰላቸው ወደ ሲሆል ከሚሄዱ ሰዎች የበለጠ ዕውር የለም፡፡ እግዚአብሄር የለም እያሉ ሰማይንና ምድርን የሞላውን እግዚብሄርን በመካድ ሕይወት ውስጥ ከሚኖሩ የበለጠ እውር ማን ነው? እግዚአብሄርን አገለግላለሁ፣ አመልካለሁ እያለ ግን በሠይጣን አገዛዝ ሥር ከሚኖር የበለጠ ዕውር ማን ነው? በአጠቃላይ የሕይወት መንገድ በአጠገቡ እያለ፣ በሞት ጎዳና ከሚራመድ ሰው የበለጠ እውር ማን ነው? ኢየሱስ የመጣው ለእነዚህ ሁሉ ነው፡፡ ለእውሮች ማየትን ለመስበክ፡፡

የዓይን ብርሃን ዋነኛ ጥቅሙ እያዩና እየለዩ ለመመላለስ ነው፡፡ የዓይን ብርሃን የራስን መንገድና አከባቢ እያጠኑ በመልካሙ ለመደሰት ከክፉ ግን ለመራቅ ነው፡፡

ዛሬም ወንጌልን ለሌሎች የምንሰብከው ሰዎች እውነት፣ ሕይወትና መንገድ የሆነው ኢየሱስ እያለ (ዮሃ. 14 ፡ 6) ሰዎች በሞትና በጥፋት መንገድ እንዳይሄዱ ነው፡፡ እውሮች ማየት እንዲችሉ ዓይንን ወደሚከፍት አምላክ ዘወር እንዲሉ እንመሰክራለን፡፡ ኢየሱስ ያድናል፡፡

ቁ 20 “መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር።

ኢየሱስ የኢሳይያስ ትንቢት ያለበትን መጽሓፍ (ጥቅል) ካነበበ በሃላ በምኵራብ ያሉ ሰዎች ዓይናቸውን ከእርሱ መንቀል አልቻሉም፡፡ ኢየሱስ መጽሓፉን ሲያነበበው እንደ ተለመዱ አንባቢዎች አልነበረም፣ ግን ከሕይወቱ ጋር የሚገናን፣ የሚዛመድ፣ ሕይወትም ወደ ሰሚዎች የሚያበራበት ሁኔታ ነበረ፡፡ ኢየሱስ ሥርዓቱን ለመፈጸም ብቻ አላነበበውም፡፡ ግን መልእክቱን፣ ተልዕኮውን፣ የትንቢት ፊጻሜም መድረሱን ለማረጋገጥ አነበበ እንጂ፡፡

በጨለማ ያሉት ሰዎች ብርሃን ማየት እንደሚፈልጉ፣ በብርድና በቅዝቃዘ ተጎድተው ያሉ የሙቀትን ስሜት እንደሚለዩና ወደ ሙቀቱ ለመጠጋት እንደሚመኙ፣ ይህ ኢየሱስ ያነበበው ክፍልና ኢየሱስ በውስጣቸው ያለውን ቅዝቃዜ ለመድረስ፣ ባሉበት ጨለማ ውስጥ ሆነው የብርሃን ጭላንጭል እንዲያዩ ስላረጋቸው ማንነቱን ለመመለየት ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበረ፡፡ ይህንን የተለየ ልምምዳቸውን ነው ሃኪሙና ጸሓፊው ሉቃስ በቁ 20 ላይ ለመግለጽ የሞከረው፡፡

ለካ በመካከላቸው የነበረው፣ እነርሱ ተራ አድርገው ያዩት የነበረው ኢየሱስ የእግዚአብሄር መንፈስና ቅባት ያለበት፣ ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረ ትንቢታዊ መልእክት ያለው፣ ሰዎቹም ላሉበት ድህነት፣ እስራትና እውርነት መፍትሄ ያለው ኢየሱስ ነው፡፡

መገንዘብ ያለብን ኢየሱስ በምኵራቡ ለነበሩ ሰዎች ለየት ብሎ መታየቱን ነው፡፡ ከፈሪሳዊያን፣ ከጸሃፍት፣ ከመጽሓፍት አዋቂዎች፣ ከምኩራብ መሪዎችም ይለይ ነበረ፡፡ እስከዛሬ ግን በእነርሱ ዘንድ አልታወቀም ነበረ፡፡ እስከዛሬ ሲያዩአቸው፣ ሲያገለግሉአቸው፣ ሲያነቡላቸው የነበሩ ሰዎች ያላሳዩአቸውን መገለጥ አምጥቶላቸዋል፡፡ ማንም ደፍሮ በሕዝቡ ፊት የማያነበውን ክፍል ቀልባቸውን በሚስብ መልኩ አነበበው፡፡ ግን ምን እየሆነ ነበር ያለው?

ቁ 21 “እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር።

ሰዎቹ በመደነቅ በትኩር ሲመለከቱት፣ ኢየሱስ ምን እየሆነ እንዳለ ተናገራቸው፡-“ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ”፡፡

የትንቢቱ ቃል ፍጻሜ ዛሬ ሕያው ሆኖ በመካከላችሁ ስላሌ፣ ማየት፣ መዳሰስ፣ ማረጋገጥ ትችላላችሁ ማለቱ ነው፡፡ መቀበል አለመቀበሉ የእነርሱ ምርጫ ነው፣ ግን እውነቱ በመካከላቸው እግዚአብሄር ሥራውን እየሰራ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ይፈጸማል፡፡ በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው የእግዚአብሄር ዓላማና ፈቃድ፣ እንደሚሆን የተነገረው ትንቢትም ሳይፈጸም አይቀርም፡፡

ኢየሱስ ወደዚህ መድር ሲመጣ፣ ሲያገለግል፣ ሲሰቀልና ሲሞት በሶስተኛም ቀን ከሙታን መካከል ሲነሳም የትንቢት ፊጻሜ ነበረ፡፡ ደግሞም ተመልሶ እንደሚመጣ ተጽፎአል፡፡ ያም አንድ ቀን በድንገት ይፈጸማል፡፡

ኢየሱስ በምኵራቡ ተገኝቶ መጽሃፉን ሲያነብና ትንቢቱ እንደ ተፈጸሜ ሲነግራቸው ሰዎቹ ያንን ቀን ከሌላ የሰንበት ቀን ያልተለየ ተራ ቀን አድርገው የተለመደ አምልኮአቸው ለማድረግ በተሰበሰቡበት ነበረ፡፡ እነርሱ ሳያስቡት በመካከላቸው በሆነውና ኢየሱስ በተናገረው ነገር ሰዎቹ በጣም ተገረሙ፡፡

ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ ዳግም ሲመጣም እንዲሁ ይሆናል፡፡ ማንም ባልጠበቀበት፣ ተራ በሚባል ቀን፣ በምንም ከሌሎች ሰዓታት በማይለይ ሰዓት፣ ደቂቃና ሰከንድ ውስጥ በድንገት ዐለምን በሞላ የሚያስገርም፣ የሚያስደነግጥ፣ ለሰዎች ሁሉ ለዘላለሙ ኑሮአችው አድስ ምዕራፍ መጀመሪያ የሚሆን ነገር ይሆናል፡፡ ኢየሱስ በሰማያት መላእክት ታጅቦ በክብር ይመጣል፡፡ የተጻፈውም ትንቢት ይፈጸማል ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡

ጌታ ይባርካችሁ፡፡

በተክሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *